1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

መመለስ ወይስ መቅረት?

ዓርብ፣ ሚያዝያ 13 2009

የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚያዚያ 10 ቀን 2009 ዓ ም ባወጣው የፕረስ መግለጫ መሰረት በሳውዲ ዓረቢያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በሰላማዊ መንገድ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ አበረታቷል። በሳውዲ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ግን ምን ያህል ለመመለስ ፍቃደኛ ናቸው?

https://p.dw.com/p/2bf4k
Saudi Arabien Riad Abschiebung Äthiopier
ምስል DW/S. Shiberu

ከሳውዲ ይውጡ የተባሉ ኢትዮጵያውያን

ከአራት አመታት በፊት ሳዑዲ አረቢያ «ሕገ-ወጥ» ያለቻቸውን የውጭ አገር ሰዎች ስታባርር ኢትዮጵያውያንን ያስቆጣ በደል ተፈጸመ። ያኔ ከሳዑዲ አረቢያ ወደ አገራቸው የተጠረዙ ኢትዮጵያውያን አዲስ አበባ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ በእስር ቤት በቂ ምግብ አለማግኘታቸውን፤ድብደባ እና እንግልት እንደገጠማቸው ተናግረዋል። ኢትዮጵያውያኑ ራሳቸውን ለመጠበቅ ከሳዑዲ አረቢያ የጸጥታ ኃይሎች ጋር እስከ መጋጨትም ደርሰው ነበር። በድርጊቱ የተቆጡ ኢትዮጵያውያን አዲስ አበባ በሚገኘው የሳዑዲ አረቢያ ኤምባሲ የተቃውሞ ሰልፍ እስከማድረግም ደርሰዋል። 
በሳዑዲ አረቢያ የሚኖሩ በተለይም ሕጋዊ ሰነድ በእጃቸው ያልያዙ ኢትዮጵያውያን አሁንም ተመሳሳይ ፈተና ከፊታቸው ተደቅኗል። የሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት ሕገወጥ ያላቸው የውጭ ሃገራት ዜጎች ያለምንም እንግልት እና ቅጣት ሀገሩን ለቀው እንዲወጡ የ90 ቀናት የምህረት ጊዜ መስጠቱ ይታወቃል። ይህ የጊዜ ገደብ ሰኔ 20 ቀን 2009 ዓ.ም ያበቃል።

Äthiopien - Demonstration in Addis Abeba
ኢትዮጵያውያን አዲስ አበባ በሚገኘው የሳዑዲ አረቢያ ኤምባሲ (2013)ምስል DW
Saudi Arabien Arbeiter kehren nach Äthiopien zurück
ኢትዮጵያውያን ተመላሾችምስል DW/S. Shiberu

አዋጁ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ ሀገሪቱ ህገወጥ ያለቻቸውን የውጭ ሀገር ዜጎች ይመለከታል። ሀገሪቱ የተሻለ ሥራ እና ገቢ የሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን ከሚያመሩባቸው የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት አንዷ ናት። በዚያ ያሉት ኢትዮጵያውያን ግን ሁሉም ሕጋዊ አይደሉም። የሳዑዲ አረቢያ መንግሥትን አዋጅ ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግሥት የጉዞ ሰነድ ያወጡ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ወደ ሀገራቸው መግባት ከሚጠበቅባቸው ቁጥር አንፃር አሁንም በጣም ዝቅተኛ መሆኑን ገልጿል።  ኢትዮጵያውያኑ ለምን ወደ ሀገራቸው ለመመለስ አልፈቀዱም? የተወሰኑትን ጠይቀናል። የሰጡንን አስተያየት ከድምፅ ዘገባው ያገኙታል።
ልደት አበበ
አርያም ተክሌ