1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከሶማሌ ክልል በርካቶች ተፈናቀሉ

ሐሙስ፣ መስከረም 4 2010

በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች ሠላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሰዉ ግድያ፤ድብደባ እና ማሰቃየት እየተባባሰ መምጣቱ ተነገረ። ከሶማሌ ክልል ርዕሰ ከተማ ከጅግጅጋ እና ከተለያዩ አካባቢዎች የተፈናቀሉ የኦሮሞ ተወላጆች በክልሉ አሰቃቂ ግድያ እየተፈጸመ ነው ሲሉ ተናግረዋል። የሶማሌ ክልል በበኩሉ 50 ገደማ ሶማሌዎች አወዳይ ከተማ ዉስጥ ተገድለዋል ሲል ወንጅሏል።

https://p.dw.com/p/2k0BV
Äthiopien Stadt Jijiga
ምስል DW/T. Waldyes

ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለዋል የሚሉ ውንጀላዎች ተሰምተዋል

በምሥራቅ ኢትዮጵያ የድንበር ግዛት ይገባኛል ሰበብ በሶማሌ እና በኦሮሚያ ክልልሎች የቀሰቀሰው ግጭት ወደ ከፋ ቀውስ እያመራ ይመስላል።የሁለቱ ክልሎች ባለሥልጣናት አንዱ የሌላዉን ጎሳ በአሰቃቂ ሁኔታ ገድሏል፤ ደብድቧል፤ አፈናቅሏል በማለት መወነጃጀል ይዘዋል። ከጅግጅጋ ከተማ ተፈናቅለው ጭናክሰን በሚገኙ ትምህርት ቤቶች እና የቀድሞ የጦር ሰፈር የተጠለሉ የአይን እማኞች ሐብት ንብረታቸውን ተቀምተው መባረራቸውን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። "ጅጅጋ ላይ ከስንት ህዝብ ውስጥ ነው አላህ ያተረፈን" የሚሉት እንስት በጭናክሰን ጊዜያዊ መጠለያ ካረፉ ተፈናቃዮች መካከል አንዷ ናቸው። "በለሊት መጥተው ብዙ አመት የሰራንውን ንብረት ተረከቡን።" የሚሉት ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ እንስት ድብደባ እንደተፈጸመባቸው ተናግረዋል።

ከጅግጅጋ ከተማ በደቦ ጥቃት ሊፈጸምባቸው ሲሞከር በመከላከያ ሰራዊት እርዳታ መውጣታቸውን የሚናገረው ወጣት በጭናክሰን ከተጠለሉት አንዱ ነዉ። "ትናንት እና ከትናንት ወዲያ ብዙ ሰው ተገድሏል፤ተገርፏል። እኛ አሁን ነፍሳችንን ለማዳን አምልጠን ወደዚህ መጥተናል። ቁጥሩ የማይታወቅ ሰው ነው የሞተው።"  ባዶ እጃቸውን በ20 የደረቅ ጭነት ማመላለሻዎች ተጭነው ወደ ጭናክሰን መጓዛቸውን ተናግሯል።

ከቶጎውጫሌ፤ከቀሪበያህ እና ከጅግጅጋ የተፈናቀሉ ሰዎችን የተቀበሉት የጭናክሰን ነዋሪ ስማቸውን ለመናገር የደኅንነት ሥጋት ተጭኗቸዋል።

ጉዳት የደረሰባቸውን ወደ ጭናክሰን የጤና ጣቢያ በማመላለስ የተጠመዱት የአይን እማኝ የታዘቡትን ለመናገር እምባ ይተናነቃቸዋል። "መንግሥት አለ ወይ?" ሲሉም ይጠይቃሉ።

በሶማሌ ክልል ይኖሩ የነበሩ የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች ተፈናቅለው የተጠለሉት ጭናክሰን ብቻ አይደለም። የተኩስ ድምፅ በሚሰማባት ጉርሱም በርካታ ተፈናቃዮች መድረሳቸውን የአካባቢው ገበሬ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

Äthiopien Stadt Jijiga
ምስል DW/T. Waldyes

"ጠዋት ከ12 ሰዓት ጀምሮ እስካሁን ብዙ የጦር መሳሪያ እየተተኮሰ ነው። በደበሌ እና በቆቦ ሰዎች እየተመቱ ይገኛሉ። አሁን ከጅግጅጋ የተባረሩ ብዙ ሰዎች እዚህ ይገኛሉ። ብዙ ሰዎችን ገርፈው፤ገንዘባቸውን ዘርፈው ነው ያባረሯቸው። ከውጫሌ የመጡም እዚህ ይገኛሉ። ከጅግጅጋ ከነልጆቻቸው የተፈናቀሉም በዚህ አሉ።"

በዚህ ዘገባ ላይ የሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትን ምላሽ ለማካተት ያደረግንው ጥረት አልተሳካም። የፕሬዝዳንቱ ቢሮ የስልክ ጥሪያችንን ቢመልስም ምላሽ ነፍጎናል። የክልሉ መንግሥት መስከረም 2 ቀን በአወዳይ ከተማ የተገደሉ ሶማሌዎች የቀብር ሥነ-ሥርዓት ለመፈጸም በዝግጅት ላይ መሆኑን አስታውቋል። በአወዳይ የተገደሉ ሰዎች ቁጥር እስካሁን በትክክል አይታወቅም። የሶማሌ ክልል የመንግሥት ኮምዩንኬሽን ቢሮ በፌስ ቡክ ገጹ ግን "ከ50 በላይ የሆኑ ንጹሀን ዜጎች በአሰቃቂ ሁኔታ" በአወዳይ ከተማ ተገድለዋል የሚል ፅሁፍ አስፍሯል። በጅግጅጋ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ዮኒስ ኑር እንደሚሉት ለበርካታ አመታት በአወዳይ ከተማ በጫት ንግድ ሥራ ይተዳደሩ የነበሩ ከ30 በላይ ሰዎች መሞታቸውን ሰምተዋል።

የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የኮምዩንኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ በግል የፌስ ቡክ ገፃቸው ባሰፈሩት ሐተታ ግን በአወዳይ ተቃውሞ ወቅት የተገደሉት 18 ሰዎች መሆናቸውን ገልጠዋል። አቶ ዮኒስ ኑር በጅግጅጋ ከተማ የኦሮሞ ብሔር አባላትን ለይቶ የተፈጸመ ጥቃት አላየሁም ሲሉ ተናግረዋል።

እሸቴ በቀለ

ኂሩት መለሰ