1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከአዲስ አበባው ቦምብ ፍንዳታ ጋር በተያያዘ 9 የጸጥታ ሹማምንት ታሰሩ

ቅዳሜ፣ ሰኔ 16 2010

የኢትዮጵያ መንግሥት በአዲስ አበባ ከተፈጸመው የቦምብ ጥቃት ጋር በተያያዘ ዘጠኝ የጸጥታ ሹማምንት እና ስድስት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን አስታወቀ። ከ4 እስከ አምስት ሚሊዮን የሚገመቱ ተሳታፊዎች በታደሙበት መርኃ-ግብር ላይ በተጸመው ጥቃት አንድ ሰው ሲሞት 165 ቆስለዋል።

https://p.dw.com/p/309r7
Äthiopien Addis Abeba  Verletzte nach Bombenexplosion
ምስል Ahmed

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነርን ጨምሮ ዘጠኝ የፌዴራል እና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አመራሮች እና አባላት በቁጥጥር ሥር ዋሉ። ብሔራዊው የቴሌቭዥን ጣቢያ የመንግሥት ኮምዩንኬሽን ጉዳዮች ምኒስትር አቶ አሕመድ ሽዴን ጠቅሶ እንደዘገበው ዘጠኙ የጸጥታ ኃላፊዎች እና አባላት በቁጥጥር ሥር የዋሉት ዛሬ በመስቀል አደባባይ በተካሔደው ሰላማዊ ሰልፍ ከደረሰው ጥቃት ጋር በተያያዘ ነው። 

አቶ አሕመድ ሽዴ "ሌሎችም ክፍተት ያሳዩ አካላት እየተጣራ በቁጥጥር ሥር እንደሚውሉ" መናገራቸውን የቴሌቭዥን ጣቢያው ዘግቧል። የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን በበኩሉ በመስቀል አደባባይ ጠቅላይ ምኒስትር አብይ አሕመድን ለመደገፍ በተጠራው ሰልፍ ላይ ጥቃት ፈጽመዋል ተብለው የተጠረጠሩ ስድስት ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን አስታውቋል።

ባለፈው ሳምንት የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ጄኔራል ሆነው የተሾሙት አቶ ዘይኑ ጀማል "እስካሁን ድረስ ስድስት ተጠርጣሪዎች በእጃችን ገብተዋል። ሌሎችም ተጠርጣሪዎች ይኖራሉ ብለን እንገምታለን። ፖሊስ እና ሌሎች የጸጥታ ኃይሎች ክትትል እያደረጉ ነው" ሲሉ አብራርተዋል። አቶ ዘይኑ ከ4 እስከ 5 ሚሊዮን የሚገመት ሕዝብ በተሳተፈበት መርኃ-ግብር ላይ "የተወረወረው አንድ የእጅ ቦንብ ነው" ሲሉ ተናግረዋል። 

በጥቃቱ 165 ሰዎች በቦምብ ፍንጣሪ እና "በድንጋጤ በመረጋገጥ" ጉዳት እንደደረሰባቸው አቶ ዘይኑ ገልጸዋል። አቶ ዘይኑ እንዳሉት አንድ ሰው ሲሞት፤ 15 ሰዎች ደግሞ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል።  የጤና ጥበቃ ምኒስትሩ ዶክተር አሚን አማን በትዊተር ገፃቸው ባሰፈሩት መረጃ  እስከ ምሽቱ ሶስት ሰዓት ድረስ በጥቁር አንበሳ፣ ቤተዛታ፣ ጋንዲ፣ ዘውዲቱ፣ አቤት እና ቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታሎች 156 የቆሰሉ ሰዎች እገዛ ተደርጎላቸዋል።በዶክተር አሚን መረጃ መሰረት አንድ ሰው የሞተው በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሲሆን ከቆሰሉት መካከል ስምንት የከፋ ጉዳት ደርሷባቸዋል። ሃምሳው ደግሞ አልጋ ይዘዋል፤ አምስቱ የሕክምና እገዛ ተደርጎላቸው ወደየቤታቸው ሔደዋል። ጠቅላይ ምኒስትር አብይ አሕመድ እና ምክትላቸው አቶ ደመቀ መኮንን በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ተገኝተው የቆሰሉ ዜጎችን ጎብኝተዋል። 

Äthiopien Kundgebung Premierminister Abiy Ahmed in Addis Ababa | Explosion
ምስል Oromo Media Network

"ለውጥን እንደግፍ፣ ዴሞክራሲን እናበርታ" በሚል መፈክር በመስቀል አደባባይ በተካሔደው የድጋፍ ሰልፍ ላይ ጥቃት መፈጸሙ የተሰማው ጠቅላይ ምኒስትሩ ንግግራቸውን ጨርሰው ከተቀመጡ በኋላ ነበር። የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አርማ ያለበትና በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን የተሰራጨ ምስል እንዳሳየው ከሆነ ጠቅላይ ምኒስትር አብይ ንግግራቸውን አጠናቀው በተቀመጡበት የፍንዳታ ድምፅ ሲሰማ ጠባቂዎቻቸው አስነስተው ወስደዋቸዋል። 

ጠቅላይ ምኒስትሩ ጥቃቱ ከተፈጸመ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ በብሔራዊው የቴሌቭዥን ጣቢያ ቀርበው በሰጡት መግለጫ ጥቃቱ "በተጠና" እና "በታቀደ" መልኩ የተፈጸመ ነው ብለዋል። የጥቃቱ ፈፃሚዎች "ሙያን ታግዘው ይኸን ደማቅ ሥነ-ሥርዓት ለማደፍረስ፤ ለማበላሸት፤ የሰው ሕይወት ለመቅጠፍ፤ ደም ለማፍሰስ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል" ሲሉ አክለዋል።
የመርኃ-ግብሩ አዘጋጆች ጥቃቱ በጠቅላይ ምኒስትሩ ላይ ያነጣጠረ እንደነበር ተናግረዋል። ከአዘጋጆቹ አንዱ የሆኑት አቶ ስዩም ተሾመ ለጀርመን ዜና አገልግሎት እንደተናገሩት ከተጠርጣሪዎቹ አንዱ የሆነ ግለሰብ ቦምቡን ጠቅላይ ምኒስትሩ ወደተቀመጡበት ለመወርወር ቢሞክርም በተሳታፊዎች ጣልቃ ገብነት ሳይሳካለት ቀርቷል። የምሥራቅ አፍሪቃ የጸጥታ ጉዳዮች ተንታኙ አቶ ሐሌሉያ እንደሚሉት የጥቃቱ ፈፃሚ ማንነት ገና በፖሊስ ምርመራ የሚጣራ ቢሆንም በገዢው ግንባር መካከል ያለውን ያለመተማመን ያሰፋዋል። "ከፍንዳታው ተከትሎ መግለጫ የሰጡ የኦሕዴድ ከፍተኛ ሹማምንቶች ይኸ ነገር ጠቅላይ ምኒስትሩን ለመግደል የተደረገ ነገር ነው ሲሉ ተሰምተዋል። ይህ በኢሕአዴግ አራቱ አባል ፓርቲዎች መካከል ያለው በተለይ ደግሞ በሕወሓት እና ኦሕዴድ መካከል ያለው አለመተማመን እና ልዩነት እየሰፋ እንደመጣ የሚያሳይ ምልክት ይመስለኛል" ሲሉ አቶ ሐሌሉያ ገልጸዋል። 

Äthiopien Addis Abeba  Verletzte nach Bombenexplosion
ምስል Ahmed

የኦህዴድ ሹማምንት "ይኸ ተቋም፣ ይኸ ፓርቲ" ብለው ጣት የጠቆሙበት አለመኖሩን የጸጥታ ጉዳዮች ተንታኙ ተናግረዋል። "ከዚህ በፊት እንዲህ አይነት የቦምብ ጥቃቶች ወይም የአሸባሪ ጥቃቶች ብሎ መንግሥት የሚፈርጃቸው ነገሮች ሲከሰቱ ብዙ ጊዜ ጣት የሚጠቆመው በግንቦት ሰባት፤ በኦነግ፤ በኦብነግ ወይ ደግሞ ኤርትራ ላይ ነበር" የሚሉት ተንታኙ እነዚህ ኃይሎች የመንግስትን የለውጥ እንቅስቃሴ በመደገፋቸው በዚህም ምክንያት የቀድሞ አካሄድ እንደማያዋጣ አስረድተዋል። 

ከጥቂት ቀናት በፊት ነፍጥ መጣሉን ያስታወቀው አርበኞች ግንቦት ሰባት ጥቃቱን አውግዞ "ድርጊቱ ተጣርቶ የጥቃቱ ፈፃሚዎች ለፍርድ እንዲቀርቡ" ባወጣው መግለጫ ጠይቋል። የኬንያ፣ የጅቡቲ፣ የሶማሊያ መሪዎች እና የሱዳን ውጭ ጉዳይ ምኒስትር የቦምብ ጥቃቱን አውግዘዋል።

አዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ በመስቀል አደባባይ በደረሰው ፍንዳታ ሰለባ ለሆኑ ዜጎች ሐዘኑን ገልጿል። ኤምባሲው "ኢትዮጵያ ትርጉም ያለው የፖለቲካ እና የኤኮኖሚ ማሻሻያዎች እያደረገች ባለችበት ወቅት ኹከት ቦታ የለውም" ብሏል። በኢትዮጵያ የአውሮጳ ኅብረት ተልዕኮ በበኩሉ ጥቃቱን "የፈሪ ተግባር" ሲል ኮንኖታል።

እሸቴ በቀለ

ተስፋለም ወልደየስ