1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከግዙፉ ፌስቡክ ያፈተለኩ የግል መረጃዎች አወዛግበዋል

ዓርብ፣ መጋቢት 14 2010

ፌስቡክ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ደንበኞቹ ያለፍላጎታቸው የግል መረጃቸው ለፖለቲካ ጥቅም መዋላቸው በዓለም ዙሪያ ቁጣ ቀስቅሷል። ፌስቡክንም በ2 ቀን ብቻ 50 ቢሊዮን ዶላር የገበያ ዋጋ አሳጥቶታል። የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጥሰትን የሚመለከተው፦ «HRes128» የተሰኘው ረቂቅ ሠነድ በዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት ድምጽ ሊሰጥበት ቀጠሮ ተይዞለታል።

https://p.dw.com/p/2uoHG
Facebook Event
ምስል picture-alliance/AP Photo/N. Berger

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

በዚህ ሳምንት የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ላይ እንደ ወትሮው ለብቻው ጎልቶ የወጣ ርእስ አልነበረም። ኾኖም በተናጠል መነጋገሪያ የነበሩ ርእስ ጉዳዮችን ቃኝተናል። በኢትዮጵያ የመንግሥት ሥልጣን የተቆጣጠሩ አካላትን ተጠያቂ የሚያደርገው የሰብአዊ መብቶች ጉዳይ በአሜሪካን ሀገር የምክር ቤት አባላት ከሁለት ሳምንት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ድምጽ እንዲሰጥበት ተወስኗል።  የጠቅላይ ሚንሥትር ምርጫ ጉዳይ እና የኢሕአዴግ የምክር ቤት ስብሰባ ላይ አስተያየቶች ተሰጥተዋል። እንዲሁም ፌስቡክ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ደንበኞቹን መረጃ ያለ ዕውቅናቸው ለሌሎች በተለይ ለፖለቲከኞች አሳልፎ መስጠቱ በዓለም ዙሪያ ቆጣ ቀስቅሷል። ለዛሬ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ትኩረት የሰጠናቸው ርእሰ ጉዳዮቹ ናቸው።

ለወትሮ አንዳች የመነጋገሪያ ርእስ የማይታጣባቸው የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በዚህ ሳምንት ደብዝዘው ብለው ነው የታዩት። ይኽን የታዘበችው መቅደስ ጂ በትዊተር ገጿ፦«ወሬ አለቀብን መሰለኝ ዝምምምምም ተባባልን እስቲ ደሞ ቅላይ ንስትሩ ሳውቁንና ንሽ እንንጫጫ ጭር ሲል አንወድም» የሚል መልእክት አስነብባለች።

በኢትዮጵያ ቀጣዩ ጠቅላይ ሚንስትር ማን ይኾናል የሚለው ጥያቄ በዚህ ሳምንትም ተጨማሪ መላ ምት የተሰጠበት ጉዳይ ነበር። ሁሉም የየራሱን ግምት በሚመስለው መንገድ ሲሰጥም ታይቷል። ይኹንና ግን አስተያየቱ ባለፈው ጠቅላይ ሚንሥትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ሥልጣን እንደሚለቁ ባሳወቁበት ወቅት እንደ ነበረው አይነት አይደለም።

Facebook und Twitter Symbolbild
ምስል picture-alliance/dpa/F.-P. Tschauner

መጪው ጠቅላይ ሚንሥትር ከኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳዮች አንጻር ብርቱ ፈተና እንደሚገጥመው አስተያየቶች ተሰንዝረዋል። ተስፍ በሚል የትዊተር አድራሻ፦ «ለአዲሱ ጠቅላይ ሚንስትራችን፣ መልካም የፈተና ጊዜ ይሁንልዎ» የሚል መልእክት ተጽፏል። 

በአውሮጳ ኅብረት የኢትዮጵያ ተልዕኮ የተሰኘ የትዊተር ገጽ ሐሙስ ዕለት ባስነበበው መልእክቱ፦ «የኢሕአዴግ ምክር ቤት ስብሰባ በዚህ ሐሙስ ሦስተኛ ቀኑን ይዟል» ብሏል።  የጠቅላይ ሚንሥትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እና የምክትል ጠቅላይ ሚንሥትር ደመቀ መኮንን ፎቶግራፍን አያይዞ አቅርቧል።

HRes128 የተሰኘው ረቂቅ ሰነድ በዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት ድምጽ ሊሰጥበት እንደኾነ ይፋ መኾኑ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቅሷል። ከአንድ ዓመት ግድም በፊት በዩናትድ ስቴትስ ኮንግሬስ 115ኛው ቀዳሚ ስብሰባ ላይ የተዋወቀው ይኽ ረቂቅ ሠነድ የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት አያያዝን ይዳስሳል። 

ረቂቅ ሠነዱ ከብዙ በጥቂቱ ቀጣዮቹን ጉዳዮች አጥብቆ ይቃወማል። በኢትዮጵያ ከመጠን ያለፈ ኃይል በመጠቀም ሰላማዊ ሰልፈኞችን ገድለዋል ያላቸውን የመንግሥት ጸጥታ ኃይላት ርምጃ አጥብቆ ያወግዛል። መጠን ያለፈ የኃይል ርምጃ እና ግድያ ፈጻሚዎች ላይ ግልጽ እና ምሉዕ የሆነ ነጻ ምርመራ እንዲደረግ ያሳስባል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲነሳ ይጠይቃል። እንዲሁም ፖለቲከኞች እና ጋዜጠኞች መታሰራቸውን ይኮንናል።

የምክር ቤቱ አባል ማይክ ኮፍማን የኢትዮጵያ ጉዳይን የሚመለከተው ረቂቅ ሠነድ ምክር ቤቱ ድምጽ እንዲሰጥበት መወሰኑ እንዳስደሰታቸው በትዊተር ገጻቸው ገልጸዋል። ሠነዱ ለውሳኔ እንዲመራ ለወራት በትጋት ተሳትፈዋል ያሏቸውንም በሙሉ አመስግነዋል።  «በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች እንዲከበሩ ብሎም ሁሉን አሳታፊ አስተዳደር እንዲኖር የሚደረገው ትግል ይቀጥላል» ብለዋል በትዊተር መልእክታቸው። 

የምክር ቤት አባሉ ማይክ ኮፍማን ድረ-ገጻቸው ላይ ባወጡት መግለጫ ላይ ደግሞ «HRes128» የተሰኘው ረቂቅ ሠነድ በዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት ድምጽ ሊሰጥበት የተቀጠረው የሚያዝያ አንድ ሣምንት መኾኑን ዐስታውቀዋል። በርካቶች በትዊተር እና ፌስቡክ ለምክር ቤት አባሉ ማይክ ኮፍማን እና ድጋፋቸውን ለሰጡ ሌሎች አባላት ምሥጋናቸውን አቅርበዋል፤ አስተያየትም ሰጥተዋል።  

ሕይወት ኒውዮርክ በሚል የትዊተር ስም የሰፈረው መልእክት፦ «ይኽ አምባገነን መንግሥት ተጠያቂ እንዲሆን ያለመታከት በመትጋቶ እጅግ እናመሰግናለን» ይላል። ረቂቁ ለውሳኔ የሚቀርብ መኾኑ ለበርካታ የአፍሪቃ ሃገራት አምባገነንነትን እምቢኝ ለማለት አብነት ሊኾን እንደሚችልም የትዊተር መልእክቱ ይጠቅሳል።

ከሕይወት ተቃራኒ ሐሳብ በትዊተር ያቀረበው አዲስ ይመር ነው። «በሀገሩ ምስቅልቅል እንጂ አንዳችም ነገር አታመጡም» ሲል ረቂቅ ሠነዱ ለውሳኔ ይቀርባል መባሉን ተቃውሟል። «የራሳችንን ችግር በራሳችን እንፈታለን የእናንተን ለእናንተው እዛው ያዙት»ም ብሏል።

#HRes128 የተሰኘው ረቂቅ ሰነድ ለውሳኔ እንዲመራ በውጭ ሃገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ቀደም ሲል የተቀናጀ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ዘመቻ አኪያሂደው ነበር ። በዘመቻውም የዩናይትድ ስቴትስ የኮንግሬስ አባላትን ስም እና የስልክ ቁጥራቸውን በማያያዝ ነዋሪዎች ስልክ በመደወል እና መልእክት በመላክ ጫና እንዲያደርጉ የሚጠይቅ ነበር።  

ረቂቅ ሠነዱ ለምክር ቤት ሲቀርብ አባላት እንዲደግፉት ኢትዮጵያውያን ጫና እንዲያደርጉ ክብሩ በትዊተር ጥሪ አስተላልፈዋል፦ «አሁን ጊዜው የእኛ የኢትዮጵያውያን ነው፤ ተወካዮቻችን የማግኘት እና HRes128ን እንዲደግፉ ጫና የመፍጠር» ሲሉ።

ወደ ሌላኛው ርእሰ ጉዳያችን እንሻገር። የፌስቡክ ተጠቃሚዎች የግል መረጃዎች ከፌስቡክ ውጪ በሌሎች ወገኖች ያለደምበኞች ፍቃድ አልጋባብ ጥቅም ላይ ውለዋል የሚለው ዜና በሳምንቱ መጨረሻ ላይ መሰማቱ ከፍተኛ ውዝግብ አስነስቷል።  የፌስቡክ መሥራች እና ባለቤት ማርክ ሱከርበርግ የፌስቡክ የግለሰቦች መረጃዎች በሌሎች ጥቅም ላይ መዋሉን አምነው በመቀበል ይቅርታ ጠይቀዋል።  

መቀመጫውን ታላቋ ብሪታንያ ውስጥ ያደረገው ካምብሪጅ አናሊቲካ  (Cambridge Analytica) የተሰኘው ተቋም ለፖለቲከኞች እና ድርጅቶች ከግለሰቦች ሠነድ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን የሚያማክር ተቋም ነው። የዚህ ተቋም ደምበኞች ከኾኑት መካከል የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና ከአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ እጩ ተፎካካሪዎች አንዱ የነበሩት ቴድ ክሩዝ እና ሌሎችም የዓለማችን ግዙፍ ስም ያላቸው ሰዎች ይገኙበታል።  

ካምብሪጅ አናሊቲካ ከፌስቡክ ተጠቃሚዎች የ50 ሚሊዮን ሰዎችን ግላዊ መረጃዎች እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር ከ2014 ጀምሮ ሲሰበስብ ቆይቷል ተብሏል። ያም ብቻ አይደለም የግለሰብ መረጃዎችን ፖለቲከኞች እንዲጠቀሙበት አሳልፎ ሲሰጥ ነበር ተብሏል።

የፌስቡክ መረጃዎች ካምብሪጅ አናሊቲካ ጋር የደረሱት አሌክሳንደር ኮጋን የተባለው ተመራማሪ በፈጠረው የዳሠሣ ጥናት መሥሪያ ማስተናበሪያ (Application) ነው።  ይህን ማስተናበሪያ ከ270,000 በላይ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች ስልካቸው ላይ ጭነው ሲጠቀሙበት ነበር።

Großbritannien Sitz von Cambridge Analytica in London
ምስል Reuters/H. Nicholls

ኮጋን ይኽን ማስተናበሪያ የሚጠቀሙ ሰዎችን ብቻ ሳይኾን የጓደኞቻቸውንም የፌስቡክ መረጃዎችን ሰብስቦ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2015 ለካምብሪጅ አናሊቲካ አሳልፎ እንደሰጠ ነው የተጠቀሰው።

የፌስቡክ ባለቤት ማርክ ሱከርበርግ ድርጊቱ የመረጃ ደኅንነት የመጣስ ተግባር ነው ሲል ኮጋን የፌስቡክ አገልግሎቶችን እንዳይጠቀም አግዶት ቆይቷል። የሰበሰባቸው በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ መረጃዎችም እንዲሰረዞ ጠይቆ እንደነበር ተናግሯል። ኾኖም ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ ሠነዶቹ እንዳልተሰረዙ የሚያጋልጥ መረጃ ይፋ መኾኑ ውዝግቡን አጡዞታል።

የተፈጠረው ውዝግብም የፌስቡክ ገቢን በብርቱ ጎድቷል።  የፌስቡክ ተጠቃሚዎች መረጃቸው ለሌሎች መጠቀሚያ ኾኗል በተባለ በሁለት ቀናት ብቻ ግዙፉ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ አውታር ፌስቡክ 50 ቢሊዮን ዶላር የገበያ ዋጋ ማጣቱ ተዘግቧል። ኢኮኖሚክ ታይምስ የተሰኘው ድረ-ገጽ በቪዲዮው ጠቅሷል። ያም ብቻ አይደለም በርካታ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች ከፌስ ቡክ ጋር ስላላቸው ግንኙነት እያጤኑበት መኾኑን ዐስታውቀዋል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ