1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዉይይት፤ የተቃዋሚዎች ተስፋና ጥርጣሬ

እሑድ፣ ሚያዝያ 14 2010

እስረኞቹ መጨረሻ  የተለቀቁትም ሕዝብ ባደረገዉ ተከታታይ ተቃዉሞ፤ የአደባባይ ሠልፍ እና  አድማ መሆኑ አላጠያየቅም።የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች እራሳቸዉን፤ ባልደረቦቻቸዉን ወይም ተከታዮቻቸዉን በደለ እያሉ የሚያወግዙት መንግሥት ለወደፊቱ ተመሳሳይ በደል ላለመፈፀሙ ምን ዋስትና አግኘተዉ ነዉ አዲሱ መሪ በጠሩት ግብዣ ላይ የተካፈሉት?

https://p.dw.com/p/2wQFH
Abiy Ahmed Ali Ministerpräsident Äthiopien
ምስል Office of the Prime Minister-Ethiopia

ዉይይት፤ የተቃዋሚዎች ተስፋና ጥርጣሬ

ንግግር፤ተስፋ፤ ቃል  ጉብኝት፤ ግብዣና የካቢኔ ሹም ሽር የጎላበት የጠቅላይ ሚንስትር የመጀመሪያ ወር ስራ የሐገሪቱን ሕዝብ ማነጋገሩን ቀጥሏል።ጠቅላይ ሚንስትሩ ከነጋዴዎችም፤ ከወጣቶችም፤ አስቀድመዉ ራት የጋባዙት የተቃዋሚ ፓርቲዎች መሪዎችን ነዉ።ግብዣዉ ላለፉት 27 ዓመታት እንደጠላት የሚወጋገዙትን የመንግሥት እና የተቃዋሚ ፓርቲ ባለሥልጣናትን «አንድ ማዕድ ያቋረሰ» በመሆኑ በቀዉስ ማግሥት-ከቀዉስ የሚደፈቀዉን የሐገሪቱን የእስካሁን ፖለቲካ ለማስተካከል ጠቃሚ ነዉ የሚሉ አሉ።

በሌላ በኩል ግብዢያዉ በብዙዉ ዓለም የፖለቲካ ባሕል እንደተለመደዉ የመንግሥት ወይም የገዢዉ ፓርቲ እና የተቃዋሚ ፓርቲ ባለሥልጣናት በእሕል ዉኃዉ መሐል መደበኛ ያልሆነ ዉይይት ያላደረጉበት  በመሆኑ የመቀራረቡ ተስፋ በተስፋ ቀርቷል ባዮች ብዙ ናቸዉ።

እንደሚታወቀዉ እስካለፈዉ የካቲት ድረስ ዕዉቅ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች፤ባለሥልጣናትና አባላት አሸባሪነትን ጨምሮ በተለያዩ ወንጀሎች ተከሰዉ ተፈርዶባቸዉም፤ ሳይፈረድባቸዉ ታስረዉ ነበር።ፖለቲከኞቹ ሕክምና መነፍግን ጨምሮ የተለያ በደሎች እንደተፈፀማቸዉ እራሳቸዉም ባልደረቦቻቸዉም ሲናገሩም ነበር።ግርፋት እና ቁም ስቅል የደረሰባቸዉ እንዳሉም የሚናገሩ አሉ።

እስረኞቹ መጨረሻ  የተለቀቁትም ሕዝብ ባደረገዉ ተከታታይ ተቃዉሞ፤ የአደባባይ ሠልፍ እና  አድማ መሆኑ አላጠያየቅም።የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች እራሳቸዉን፤ ባልደረቦቻቸዉን ወይም ተከታዮቻቸዉን በደለ እያሉ የሚያወግዙት መንግሥት ለወደፊቱ ተመሳሳይ በደል ላለመፈፀሙ ምን ዋስትና አግኘተዉ ነዉ አዲሱ መሪ በጠሩት ግብዣ ላይ የተካፈሉት? እንዲፈቱ ባደባባይ የጮኸ፤የሞተ እና የቆሰለላቸዉን ሕዝብ በቅጡ ሳያመሰግኑ ግብዣ ለመቀበል መጣደፋቸዉስ ለምድነዉ-የሚሉ ጥያቄዎች እያነጋገሩ ነዉ።

ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከገዢዉ ፓርቲ ጋር የጀመሩት ድርድርስ የትደረሰ? ሌላዉ ጥያቄ ነዉ።የኢትዮጵያን ፖለቲካ የሚከታተሉ ወገኖች አነጋጋሪዎቹን  ጥያቄዎች እያነሱ በሚጥሉበት መሐል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሐገሪቱ ሁለት ትላልቅ ከተሞች (አዲስ አበባ እና ድሬዳዋ) ሊደረጉ የታቀዱ የምክር ቤት አባላት ምርጫዎችን ቢያንስ በአንድ ዓመት ማራዛሙን ሰምተናል።ምክር ቤቱ አዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር ያቀረቡትን የካቢኔ አባላት ሹመትም አፅድቋል።የጠቅላይ ሚንስትሩ እርምጃ፤ የተቃዋሚ ፓርቲዎች አቋም፤በየዉሳኔዎቹ ላይ ያላቸዉ ሚና እና አስተያየት የዉይይታችን ትኩረት ነዉ።

ነጋሽ መሐመድ