1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስ

የመጀመሪያዋ ሴት የህክምና ፕሮፌሰር

ረቡዕ፣ መጋቢት 5 2010

የመጀመሪያዋ ሴት የህክምና ፕሮፌሰር ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ታሪክ ደግሞ ይህንን ማዕረግ በማግኘት የቀደሟቸው አንድ ሴት ብቻ ናቸው፡፡ በመምህርነት፣ በተማራማሪነት እና በሀኪምነት ላለፉት 33 ዓመታት እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ የስኳር ህመምን የተመለከተ አንድ መጽሐፍም አሳትመዋል፡፡ ፕሮፌሰር የወይንሐረግ ፈለቀ ይባላሉ፡፡

https://p.dw.com/p/2uKcL
Professor Yeweyenhareg Feleke
ምስል Ethiopian Medical Association

የመጀመሪያዋ ሴት የህክምና ፕሮፌሰር

ዕለቱ ጥቅምት 14 ቀን 2008 ዓ.ም ነበር፡፡ ቦታው ሸራተን አዲስ፡፡ ዝግጅቱ ደግሞ በስራቸው እና አበርክቶዎቻቸው የላቁ ሴቶች ዕውቅና የሚያገኙበት ስነስርዓት፡፡ ይህን ዓመታዊ የሽልማት ስነስርዓት የሚያዘጋጀው የደፋር ሴቶች ማህበር (በእንግለዚኛ ምህጻሩ EWIB-ኤውብ) ለአራተኛው ዙር ዕጩ አድርጎ ካቀረባቸው ሰባት ሴቶች መካከል ፕሮፌሰር የወይንሐረግ ፈለቀ አንዷ ነበሩ፡፡ የማህበሩን የላቀች ሴት ሽልማት ቀደም ሲል አሸንፈው የነበሩት ወ/ሮ ፍሬአለም ሽባባው ያኔ ዕጩዎቹን ሲያስተዋውቁ እንዲህ ብለው ነበር፡፡ 

“በምኖርበት ማህበረሰብ ውስጥ በተለይ ሴቶችን ወደ ህልማቸው እና ወደነፍሳቸው ጥሪ እንዳይሄዱ ሊከለክሉ የሚችሉ የተለያዩ አመለካከቶች ወይም አስተሳሰቦች ቢኖሩም እነዚህን ሁሉ ጫናዎች ጥሰው በመውጣት እነዚህ ድንቅ ሴቶች ‘እኔ መስራት የምፈልገው ይሄን ነው፤ መስራት የምፈልገውም በዚህ መንገድ ነው’ ብለው በመወሰን መገፋት ቢኖር፣ ተስፋ መቁረጥ ወይም ደግሞ ተስፋ ማጣት እነዚህን ሁሉ ተቋቁመው መስራት ወደሚፈለጉት ነገር በማተኮር በማህበረሰባችን ውስጥ ያበረከቱት አስተዋጽኦ እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ አስተሳሰብን ተገዳድረዋልና ምስጋና ይገባቸዋል” ብለዋል ወ/ሮ ፍሬአለም። በህክምና የስራ መስክ ለሽልማት ዕጩ የነበሩት ፕሮፌሰር የወይንሐረግ ይህን ገለጻ በእርግጥም የሚያሟሉ ናቸው፡፡ ዘጠኝ ልጆች ባሉበት ቤተሰብ በደቡብ ኦሮሚያ ባለ የገጠር ስፍራ ተወልደው ያደጉት የወይንሐረግ በመጀመሪያ ሀኪም፣ ለጥቆ መምህር ከዚያም ተማራማሪ መሆን ችለዋል፡፡ በአዲስ አበባ ዩነቨርስቲ የህክምና ትምህርት ቤት ማስተማር በጀመሩ በ13 ዓመት ውስጥ የፕሮፌሰርነት ማዕረግ ደርበዋል፡፡ በታህሳስ 2002 ዓ.ም በዩኒቨርስቲው የጸደቀላቸው ይህ ማዕረግ በኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ ሴት የህክምና ፕሮፌሰር አድርጓቸዋል፡፡ በዩኒቨርስቲው ታሪክ ደግሞ የፕሮፌሰርነት ማዕረግ በማግኘት ሁለተኛዋ ሴት ሆነዋል፡፡ የተጓዙበትን መንገድ ወደ ኋላ መለስ ብለው የሚያስታውሱት ፕሮፌሰር የወይንሐረግ “ቀላል አልነበረም” ይላሉ፡፡ የሳይንሱን ዘርፍ ሲቀላቀሉ የነበረባቸውን ፈተና እንዲህ ያስረዳሉ፡፡  

“አንደኛ ነገር በእኛ ጊዜ የሳይንስ መስክ እንዳሁኑ 70/30 የሚል ህግ አልነበረውምና ህክምና ኢንጂነሪንግ የሚገባው ተማሪ እጅግ ቁጥሩ አናሳ እና ምርጥ ተማሪ ነበር፡፡ በእዚህ መስክ ለመግባት አስቸጋሪ ዘርፍ ነው፣ ይፈራል፣ ከባድ ነው፡፡ እውነትም ከባድ ነው፡፡ ምክንያቱም ከገጠር ውስጥ መጥተህ ህክምና ትምህርት ቤት ተምረህ ወደዚህ መምጣት በጣም ከባድ ነው፡፡ ብዙ ተግዳሮቶች አሉት፡፡ ግን በእያንዳንዱ ደረጃ የሚኖረውን ተግዳሮት እግዚያብሔርም ይረዳኛል፣ አስተማሪዎችም አሉ፣ የምማረውን ትምህርት በአግባቡ ተምሬ በአግባቡ የሚያስፈልገውን ነገር አደርጋለሁ፡፡ ሌላ አስተማሪዎች የሚሰጡት ዕውቀት ደግሞ መሰረት ሆኖኛል” ይላሉ ፕሮፌሰር የወይንሐረግ፡፡   

AWIBs jährlicher Women of Excellence Award (Association of Women in Business - Ethiopia (AWIB))
ምስል Association of Women in Business - Ethiopia (AWIB)

በ1977 ዓ.ም የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ያገኙት ፕሮፌሰር የወይንሐረግ ለአምስት ዓመት በጠቅላላ ሀኪምነት አገልግለዋል፡፡ ለአራት ዓመት የዘለቀውን የድህረ ምረቃ ትምህርታቸውን ደግሞ በውስጥ ደዌ ህክምና ተከታትለዋል፡፡ ከተመረቁ በኋላ በዚያ በተማሩበት ዩኒቨርስቲ በአስተማሪነት እንዲቀሩ ሲመረጡም በትምህርት ክፍሉ ብቸኛዋ ሴት ነበሩ፡፡ ፕሮፌሰር የወይንሐረግ የምርምር ስራዎችን የጀመሩትም ከዚያን በኋላ ነው፡፡   

“ሜዲካል ዶክተር ሆኖ እንደገና ተመልሶ የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት ስሆን አንድ የመጀመሪያ ብቸኛ ሴት ነው የነበርኩት፡፡ ወደ 23 ወንዶች ነበር የነበሩት፡፡ ትምህርት ክፍሉ ውስጥተወዳድሬ ነው የቀረሁት፡፡ ተመልሼ የገባሁት በቀለም ሲኮተኩቱኝ የቆዩ አስተማሪዎቼ ጋር ነው፡፡ እንግዲህ ከባድ እና ፈታኝ ነው ግን በዚህ ልክ እንደገባሁ የእኔ የበላይ አለቃ የነበሩት አሁን በህይወት የሌሉት ፕሮፌሰር ጀማል አብዱልቃድር ወደ ምርምሩ ዘርፍም እንደገባ አደረጉኝ፡፡ ቶሎ ነው፣ በገባሁ በሶስተኛ ቀን ነው ወደ ምርምር ዘርፍ ሀሳቤ እንዲያደላ ያደረግሁት፡፡ ስለዚህ እኔ በቃ አንዳንድ ተግዳሮቶች ቢኖሩም ግን አማራጭ መንገዶችን በማየት ማለፍ ይኖራል” ይላሉ ምሁሯ፡፡

Professor Yeweyenhareg Feleke
ምስል Ethiopian Medical Association

እንዲህ የተጀመረው የፕሮፌሰር የወይንሐረግ የምርምር ስራ በርካታ ውጤቶቸ የተመዘገቡበት ሆኗል፡፡ ወደ 65 ገደማ የምርምር ጽሁፎችን ማዘጋጀታቸውን የሚናገሩት መምህሯ 52 የሚሆኑቱ በተለያዩ የምርምር መጽሔቶች (ጆርናሎች) ላይ መታተማቸውን ያስረዳሉ፡፡ አብዛኞቹ የጥናት ስራዎቻቸው በስኳር በሽታ እና ተያያዥ የሆርሞን ህመሞች ላይ ያተኮሩ ናቸው፡፡ የዚህ ምክንያቱ ደግሞ ስፔሻላይዝድ ያደረጉበት ሙያቸው እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት የሆኑት ፕሮፌሰር የወይንሐረግ  በስኳር ህመም እና ሆርሞን ህመሞች ላይ ህክምና እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ በእነዚህ በሽታዎች ዙሪያ ስለሚያደርጓቸው ምርምሮች ማብራሪያ አላቸው፡፡ 

“የስኳር ህመም ላይ የሰራኋቸው ምርምሮች ሰፋ ያሉ ናቸው፡፡ ከ15፣ ከ20 ዓመት ጀምሮ የተሰሩ ናቸው፡፡ በተለያየ ጊዜ በሀገር ውስጥም ከሀገር ውጭም ባሉ ጆርናሎች ላይ ታትመው የወጡ ምርምሮች አሉ፡፡ እነዚህ የምርምር ውጤቶች የሚያሳዩት በአጠቃላይ በሀገራችን ውስጥ የስኳር ህመም እየጨመረ መምጣቱን፣ ከስኳር ህመም ጋር ተያይዘው ያሉ ተጓዳኝ ችግሮች ለምሳሌ የነርቭ፣ የአእምሮ ችግር የምንለው የድብርት ችግር፣ የዓይን ችግሮች፣ በሰውነት ላይ የሚከሰቱ ኢንፌክሽን እና እንደዚህ ያሉ ችግሮች እየጨመሩ በስኳር ህመም ላይ እንደሚታዩ በሰራኋቸው የተለያዩ ጥናቶች ታይቷል፡፡ 

አሁን በቅርቡ ደግሞ የጤና ጥበቃ [ሚኒስቴር] የመራው በህብረተሰብ  ጤና ኢንስቲትዩት ኃላፊነት አገር ውስጥ ያለነው ባለሙያዎች ተሰባስበን የስኳር ህመም ላይ የሰራነው ሰፋ ያለ ምርምር አለ፡፡ ጠቅላላ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ላይ የተሰራ WHO step survey የምንለው ነው፡፡ ሀገር አቀፍ ጥናት ነው የተካሄደው፡፡ በዚህ ላይ አሁን በተለይ የስኳር ህመም፣ የደም  ግፊት፣ የልብ ህመም እንደዚህ የመሳሰሉት ነገሮች እየጨመሩ መምጣታቸውን ውጤቱ ላይ አይተናል፡፡ እንደገና ከዚህ ጋር ተያይዞ ደግሞ የስኳር ህመምን ሊያመጡ የሚችሉ ነገሮችን  በዳሰሳ አብሮ የታዩ አሉ፡፡ ለምሳሌ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ መቀነስ፣ የሰውነት ውፍረት መኖር፣ የአልኮልና የሲጃራ ሱስ፣ አትክልት፣ ፍራፍሬ፣ ቅጠላቅጠሎችን አዘውትሮ ያለመውሰድ እነዚህ እነዚህ ሁሉ ለደም ግፊት፣ ለስኳር ህመም እና ለልብ ህመም መንስኤ እንደሆኑ አሁን ከተሰሩት ጥናቶች ማየት ችለናል” ሲሉ ጥናቶቻቸው የደረሱበትን አስረድተዋል፡፡     

Professor Yeweyenhareg Feleke
ምስል Ethiopian Medical Association

ፕሮፌሰር የወይንሐረግ በህብረተሰቡ ዘንድ ስለስኳር ህመም ያለው ግንዛቤ ያደግ ዘንድ ሰለበሽታው የሚያወሳ መጽሐፍ በአማርኛ ቋንቋ አሳትመዋል፡፡ ከ10 ዓመት በፊት ለንባብ የበቃው ይህ መጽሐፍ በ11 ሺህ ቅጂ ተባዝቶ ተሰራጭቷል፡፡ ከመጽሐፉ ሽያጭ የሚገኘው ገቢም ለጥቁር አንበሳ ሆስፒታል እንዲውል መለገሳቸውን ይናገራሉ፡፡ መጽሐፉን በሚያዘጋጁበት ጊዜ ጎን ለጎን የስኳር ህመም እና የህሙማን እንክብካቤ ምን እንደሚመስል የሚገመግም ጥናት አካሄደዋል፡፡ ይህ በአዲስ አበባ በሚገኙ አምስት ሆስፒታሎች እና 21 ጤና ጣቢያዎች ላይ የተካሄደው ጥናትም ሀገር ውስጥ በሚታተም ጆርናል ላይ ለንባብ በቅቷል፡፡ 

አንጋፋዋ ምሁር ከምርምር ጋር ያላቸው ቁርኝት በዚህ ብቻ የተገደበ አይደለም፡፡ የሚያስተምሯቸው ወጣቶች ተመራማሪዎች እንዲሆኑ ያግዛሉ፡፡ በጥናቶቻቸው ላይ በመሳተፍም የምርምር ውጤቶችን በጋራ ያሳትማሉ፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የህክምና ትምህርት ክፍል ላለፉት 25 ዓመታት እያስተማሩ የሚገኙት ፕሮፌሰር የወይንሐረግ መምህርነታቸውን እንደሚወዱት ይናገራሉ፡፡ ስለተማሪዎቻቸው ደግሞ ይህን ይላሉ፡፡ 

“የቅድመ ምረቃ ተማሪዎች አሉ፤ ሜዲካል ዶክተር የሚወጡ ማለት ነው፡፡ የድህረ ምረቃ ተማሪዎች አሉ፡፡ እነዚህ ስፔሻሊስት ሆነው የሚወጡ ናቸው፤ ኢንተርኒስቶች የውስጥ ደዌ ህክምና ስፔሻሊስቶች ማለት ነው፡፡ እነዚህን አስተምራለሁ፡፡ በቅርቡ ደግሞ የኢንዶክሮኖሊጂስቶች የፌሎው ስልጠና ጀምረናል፡፡ በሶስተኛ ደረጃ ማለት ነው፡፡ እኛን ሊተኩ የሚችሉ የስኳር፣ የሆሮሞን ህመም ስፔሻሊስቶች ሊሆኑ የሚችሉ እያሰለጠንን ነው፡፡ እንግዲህ ይሄኛው አዲስ የተጀመረ ነው ግን ላለፉት 20 ዓመታት በላይ ግን እነዚህ የድህረ ምረቃ ተማሪዎች፣ ሀኪሞቹን እነ የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስቶቹን በስፋት ነው ሳስተምር የነበረው፡፡ በጣም ደስ ብሎኝ ነው የማስተምራቸው፤ እወዳቸዋለሁ፡፡ 

ያስተማርኳቸው ግማሾቹ በየዩኒቨርስቲው ዲኖች ነው፡፡ ያው በሚኒስትር ደረጃም በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አካባቢ በሚኒስትር ደረጃ ያሉ አሉ፡፡ እንደገና ከሀገር ውጭም ያሉት የአካዳሚክ መሪዎች ናቸው፡፡ እና በጣም ደስ ይለኛል፡፡ አሁን ከኢትዮጵያ ውጭ ስወጣም፣ የተለያየ ክፍለ ሀገር ለማስተማር ስሄድ ያስተማርኳቸው ሰዎች ኃላፊዎች ሆነው ሲመሩ አያለሁ እና ይሄ ወጣቱ ላይ የተገነባው እውቀት ውጤታማ እንደሆነ አያለሁ፡፡ እንግዲህ የማስተማር ስራ የአንድ ሰው ስራ ብቻ አይደለም፡፡ አንድን ሰው ከታች ጀምረህ ላይ ጎትተህ የምታወጣው አይደለም፡፡ የቡድን ስራ ነው፡፡ ቁጥራችን በርከት ያለ ሀኪሞችን ነን እዚህ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ያለነው እና የእያንዳንዱ ምሁር ውጤት ነው፡፡ የእኔ ብቻ ውጤት ነው ማለት አልችልም” ይላሉ ፕሮፌሰር የወይንሐረግ፡፡ 

Professor Yeweyenhareg Feleke
ምስል Ethiopian Medical Association

ፕሮፌሰር የወይንሐረግ በማስተማሩ፣ በምርምሩ እና ህክምናው ብቻ ተወስነው አልቀሩም፡፡ ያላቸውን የተጣበበ ጊዜ እንደምንም አብቃቅተውም ቢሆን በተለያዩ የሙያ ማህበራት በቦርድ እና በስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልነት ይሳተፋሉ፡፡ አባል በሆኑበት የኢትዮጵያ ህክምና ማህበር ፕሬዝዳንት እስከመሆን ደረጃ ደርሰዋል፡፡ ከተመሰረተ 56ኛ ዓመቱን በያዘው በዚህ ማህበር ሊቀመንበርነቱን በመያዝም የመጀመሪያዋ ሴት ሆነዋል፡፡ በኃላፊነት ቦታው ከአንድም ሁለት ጊዜ ተመርጠው አገልግለዋል፡፡ በዚህ ወቅትም ከማስተማር ስራቸው ለተወሰነ ጊዜ ፍቃድ በመውሰድ ጭምር ማህበሩን አንድ እርምጃ ለማራመድ ሞክረዋል፡፡ ይህን ጥረታቸውን ከግምት ያስገባው ማህበሩ ባለፈው ዓመት ሸልሟቸዋል፡፡ ማህበሩን አሁን በፕሬዝዳንት እያገለገሉ የሚገኙት ዶ/ር ገመቺስ ማሞ ስለ ፕሮፌሰር የወይንሐረግ አስተዋጽኦ ተከታዩን ብለዋል፡፡ 

“ህክምና ማህበሩ ድሮ ከነበረበት የመለወጥ ሂደቱ ከእርሳቸው ቀደም ብሎ የተጀመረ ነገር ነው፡፡ ግን ያንን ሂደት ለሁለት የስልጣን ጊዜ በመሩበት ጊዜ እንዲቀጥል አድርገውታል፡፡ ከዚያ በተረፈ እንደመጀመሪያ ሴት ፕሬዝደትነት ያደረጉት አስተዋጽኦ ትልቅ ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ  የኢትዮጵያ ህክምና ማህበርን ወክሎ በመሄድ ስብሰባዎችን [ተሳትፈዋል]፡፡ ትልቁ የኢትዮጵያ ህክምና ማህበር ትልቁ ጉዳይ የማህበሩ ህንጻ (EMA House) ነው፡፡ ህንጻውን ለማስገንባት የህንጻው የበላይ ጠባቂ ከዶ/ር ቴድሮስ [አድኃሃኖም] ጋር በመሆን በተደጋጋሚ ስብሰባዎችን በማድረግ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል፡፡

ከዚያ በተረፈ sabbatical leave ወስደው ለማህበሩ ብዙ አገልግሎት አድርገዋል፡፡ ማህበሩን በሚመለከት በተለይ የማማከር አገልግሎት በጤና ጥበቃ [ሚኒስቴር] በሚኖርበት ጊዜ በተለይ ደግሞ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን (NCD) በተመለከተ እርሳቸው ሙያቸውም ያ ስለሆነ እርሱን በተመለከተ ማህበሩን ወክለው እዚያ ቦታ ላይ ተሳትፈው የጤና ጥበቃ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ፖሊሲን በመቅረጽ ብዙ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡ በዚህ ጉዳይ የማህበሩ ስም ቢጠራ፣ ስማችን ቢጠራ በእርሳቸው አስተዋጽኦ ነው” ይላሉ ዶ/ር ገመቺስ፡፡

ዘርፈ ብዙዋ ምሁር ተሳትፏቸው በርካታ፣ አገልግሎታቸውም በየመስኩ ቢሆንም ለእርሳቸው ትልቁ ነገር የሰው ህይወት ማትረፍ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ “ከህይወት በላይ ምንም ነገር የለምና” ሲሉም ያጠቃልላሉ፡፡

ተስፋለም ወልደየስ 

ኂሩት መለሰ