1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስ

በዘገምተኛ ኢንተርኔት መስራቱ ተመራጭ አድርጎታል

ረቡዕ፣ መስከረም 10 2010

ለሞባይልም ሆነ ለኮምፒውተር ተብለው የሚሰሩ አፕልኬሽኖች በተወሰኑ ሰዎች ዘንድ መገልገያ ሆነው ይቆይዩና ይበልጥ ተወዳጅ የሚያደርጋቸው አጋጣሚ ይከሰታል፡፡ ዜሎ ዎኪ ቶኪ የተሰኘው መተግበሪያ (አፕልኬሽን) ጥቅም ላይ ከዋለ ከአምስት ዓመት በኋላ መነጋገሪያ ሆኗል፡፡ ሰሞኑን አሜሪካንን በገጠማት የተፈጥሮ አደጋ ሁነኛ የመገናኛ ዘዴ ሆነ አገልግሏል፡፡

https://p.dw.com/p/2kOj7
Symbolbild NSA Überwachung Handy
ምስል imago/avanti

በዘገምተኛ ኢንተርኔት መስራቱ ተመራጭ አድርጎታል

መስከረም 1 ቀን 2010 ዓ.ም፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የአዲስ ዓመት በዓላቸውን እያከበሩ ባሉበት ሚሊዮን አሜሪካውያን ደግሞ ቁዘማ ላይ ነበሩ፡፡ ወዲህ ከ16 ዓመት በፊት በዚያው ዕለት በሀገራቸው የደረሰውን የሽብር ጥቃት እያስታወሱ ወዲያ ደግሞ ስሙን እየቀያየረ የሚያሸብራቸው ወጀብ የቀላቀለ ኃይለኛ አውሎ ነፋስ እያደረሰ ያለው ጥፋት እያሳሰባቸው ነው፡፡ 

“ሃሪኬን ኤርማ” የሚል ስያሜ የተሰጠው አውሎ ንፋስ በዚያው ዕለት ብቻ 7.2 ሚሊዮን የሚሆኑ ቤቶች እና የንግድ ተቋማትን ያለ መብራት ኃይል አስቀርቷል፡፡ “ሀሪከን ኤርማ” ይበልጥ ተጠቂ የሆነችው በደቡብ ምስራቅ አሜሪካ የምትገኘው የፍሎሪዳ ግዛት ነበረች፡፡ የግዛቷ የመብራት ኃይል አገልግሎት አቅራቢ ድርጅት በወቅቱ ይፋ እንዳደረገው በአደጋው ምክንያት 6.5 ሚሊዮን ደንበኞቹ ከመብራት ጋር ተቆራርጠዋል፡፡ በአውሎ ንፋስ የደረሰበትን ጉዳትም  “በድርጅቱ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ” ብሎታል፡፡

Florida Hurricane Irma  Vilano Beach Haus
ምስል Reuters/ St Johns County Fire Rescue

እንዲህ የመሰረተ ልማት አውታሮች በአንዴ ከጥቅም ውጭ መሆን ዜጎቹን ከአደጋው የማዳን ተግባሩን አስቸጋሪ አድርጎታል፡፡ የአሜሪካውያን ዋነኛ ምርጫቸው የሆነው የገመድ አልባ የኢንተርኔት ግንኙነት መቋረጥ ደግሞ የመረጃ ልውውጡን ገድቦታል፡፡ ይሄኔ ነው የ“ዜሎ ዎኪ ቶኪ” መተግበሪያ (አፕልኬሽን) ስም ከዚህም ከዚያም መደመጥ የጀመረው፡፡ በዚያው ዕለት ብቻ አፕልኬሽኑን አንድ ሚሊዮን ተጠቃሚዎች በስልካቸው ላይ እንደጫኑት የዜሎ ኩባንያ አስታውቋል፡፡ ያለ ገመድ አልባ ኢንተርኔት በመደበኛ እና ዘገምተኛ የኢንተርኔት ፍጥነት በቅጡ የሚሰራውን ይህን አፕልኬሽን በአውሎ ንፋሱ የተጠቁ ሰዎች ሲገለገሉበት ውለዋል፡፡ 

ሰዎች እየተደራረቡ መረጃ ሲቀያየሩበት የሰማችሁት የዜሎ አፕልኬሽን ከሳምንት ቀደም ብሎ በተከሰተው “ሃርኬን ሃርቬይ” ወቅትም አውሎ ንፋሱ ባዳረሳቸው አካባቢዎች ተመራጭ ሆኖ ነበር፡፡ በወቅቱ በአንድ ሳምንት ውስጥ ስድስት ሚሊዮን አሜሪካውያን አፕልኬሽኑን ወደ ስልካቸው መጫናቸው ተዘግቧል፡፡ አፕልኬሽኑ እንዲህ የወቅቱ መነጋገሪያ ይሁን እንጂ ለአገልግሎት የበቃው የዛሬ አምስት አመት ግድም ነው፡፡ ከኩባንያው የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው የአፕልኬሽኑ ተጠቃሚዎች ቁጥር 110 ሚሊዮን ደርሷል፡፡ በተለያዩ ሀገራት ለሚገኙ ተጠቃሚዎች እንዲስማማ በሚል በ20 ቋንቋዎች ተዘጋጅቷል፡፡

ዜሎ ዎኪ ቶኪ  ከስሙ መረዳት እንደሚቻለው ዎኪ ቶኪ ተብሎ የሚታወቀውን እና የሬድዮ መገናኛን ወደ ስልክ ያመጣ አፕልኬሽን ነው፡፡ እንደሳምሰንግም፣ አይፎን፣ ብላክቤሪ ዓይነት ስልኮች በነጻ ለተጠቃሚዎች የቀረበው ዜሎ በኢትዮጵያ እንደተለመዱት ቫይበር፣ ዋትስ አፕ እና ኢሞ ዓይነት አፕልኬሽኖች በድምጽ መልዕክትን መለዋወጥ ያስችላል፡፡ አፕልኬሽኑን ከተንቀሳቃሽ ስልክ ሌላ በኮምፒውተር አሊያም ታብሌት ላይ ጭኖ መጠቀም ይቻላል፡፡  

በፌስ ቡክ ገጹ እና በዩቲዩብ ቻናሉ አፕልኬሽኖችን ለኢትዮጵያውያን በማስተዋወቅ ዝናን ያተረፈው ዩሱፍ አህመድ ጉበን ስለዜሎ አጠቃቀም ለተከታታዩቹ አጠር ያለ የተግባር ቪዲዮ ከሁለት ዓመት በፊት አቅርቦ ነበር፡፡ ዩሱፍ ዜሎን አሁንም ድረስ ይገለገልበታል። “በዜሎ መልዕክት መለዋወጥ የሚቻለዉ አፕልኬሽኑ ካላቸዉ ሰዎች ጋር ነዉ” ይላል። ዜሎ ዎኪ ቶኪን ተጠቅሜ ዩሱፍን አነጋግሬው ነበር፡፡

“ለምሳሌ እኔ ዜሎ መደወል ብፈልግ የምደውልለት ሰው ጋር የግድ ዜሎ አካውንት መኖር አለበት፡፡ አካውንት ሲከፍት የሚጠይቀው ምንድነው? የመጠቀሚያ ስም (username)፣ ኤ ሜይል፣ ስልክ ቁጥራችንን ይጠይቃል፡፡  አንዱ ካለን ቀጥታ በሰርች ቦታ ላይ ከላይ ቀስት አለች፣ ሰውን የመቀበያ (add) ምልክት አለ፡፡ እርሱን ስንነካው መቀበል እንችላለን፡፡ ያንን ከተቀበልን በኋላ ነው መደዋወል የምንችለው እንጂ ቀጥታ መደወል አይችልም፡፡ አፕልኬሽኑ ዎኪ ቶኪ ነው፡፡ እንደ ፖሊስ ሬድዮ ማለት ነው፡፡ አንዱ ሲያወራ አንዱ ያደምጣል፡፡ ከዚያ ሌላኛው ሲያወራ ደግሞ አንዱ ያዳምጣል፡፡ ስለዚህ ምንድነው? ክብ ነገር አለች፡፡ የማይክራፎን ምስል ያላት፡፡ በመሀል ላይ እርሷን ጫን አድርገን በመያዝ መልዕክት እናስተላልፋለን፡፡ ከዚያ ለቀቅ ስናደርገው ደግሞ ያ መልዕክት ያስተላለፍንለት ሰው በተራው ይናገራል ማለት ነው” ሲል ዩሱፍ የአፕልኬሽኑን አጠቃቀም ያስረዳል፡፡

Wahl Myanmar Politik Sicherheit
ምስል AP

ዩሱፍ የዜሎን ሌሎች ጠቀሜታዎችም ይዘረዝራል፡፡ “ሌላው በዜሎ አፕልኬሽን ያለው ጥሩ ነገር ያለንበትን ቦታ መላክ እንችላለን፡፡ ልክ እንደዋትስ አፕ፣ ፌስ ቡክ ሜሴንጀር እንደምንጠቀመው ማለት ነው፡፡ እንደገና ፎቶ በቀጥታ አንስተን መላክ እንችላለን፡፡ እንዲሁም ከፋይላችን ውስጥ ገብተንም የምንፈልገውን ፎቶ መላክ እንችላለን፡፡ እስከ 10 ሺህ የሚሆኑ ፎቶዎች በራሱ መያዝ ይችላል፡፡ ስልካችን ቀፎ ላይ ሳይቀመጥ በራሱ በአፕልኬሽን ብቻ መያዝ ይችላል፡፡ እንዲሁም ቀጥታ መልዕክት መጻጻፍ እንችላለን፡፡ ዜሎ አፕልኬሽን ተጠቅመን ማለት ነው”ይላል፡፡

የዜሎ ዎኪ ቶኪ ዋናው አገልግሎት ስለሆነው የድምጽ መልዕክት ልውውጥ አስመልክቶ በአዲስ አበባ የሞባይል አፕልኬሽን ሰሪው ኤፍሬም ተስፋዬ ምሳሌ እየጠቀሰ ያስረዳል፡፡ “ልክ የጹህፍ መልዕክት (SMS)ን እንደመላላክ ይሄኛው ድምጽ መላላክ ነው” ይላል፡፡ ዜሎ የአጭር የሬድዮ መልዕክት መለዋወጫን (ዎኪ ቶኪን) አካሄድ መጠቀሙ ዘገምተኛ ወይም አነስተኛ የኢንተርኔት ፍጥነት ባለበት በሚገባ እንዲሰራ እንዳደረገው ያስረዳል፡፡  

“በትንሽ ባንድ ዊድዝ፣ ትንሽ በሆነ ኢነተርኔት መስራት ይችላል፡፡ ለምንድነው ይሄ እንደዚያ ሊሰራ የቻለው ይሄ ተጭኖ መነጋገሪያ (Push to Talk – PTT) ስለሆነ ነው፡፡ አሁን ቫይበር፣ ዋትስ አፕ ሲሆኑ ሁለት ሰው በአንዴ ማውራት ስለሚችል ተለቅ ያለ የኢንተርኔት ወይም ባንድዊድዝ ይይዛል፡፡ ይሄኛው ግን አንድ ሰው ሲያወራ አንድ ሰው ይሰማል፡፡ ወይም ደግሞ ሌላኛው ቀጥሎ ሲያወራ ይናገር የነበረው ይሰማል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ በአንድ ጊዜ የሚስተላልፈው የድምጽ መጠን አነስተኛ ስለሆነ ትንሽ ኢንተርኔት ባለበት ቦታ ላይ በጥራት መስራት ይችላል ማለት ነው” ሲል ያብራራል፡፡  

አነስተኛ የኢንተርኔት ፍጥነት ስንል በኢትዮጵያ ብዙሃኑ የሚጠቀመውን የ2G ኢንተርኔትን ይጨምራል፡፡ አንዳንድ አፕልኬሽኖች በሚገባ ለመስራት እንደ 3G እና 4G  የኢንተርኔት ግንኙነት እንደሚፈልጉ የሚናገረው ዩሱፍ “ዜሎ” በአነስተኛ የኢንተርኔት አቅም መስራቱ እንደኢትዮጵያ ላሉ ሀገሮች “በጣም ጠቃሚ ያደርገዋል” ይላል፡፡ አሁን ከሚኖርበት ሳዑዲ አረቢያ ወደ ኢትዮጵያ በተጓዘ ጊዜም አፕልኬሽኑን በተግባር ፈትሾት በደንብ እንደሚሰራ ማረጋገጡን ይናገራል፡፡

“ታውቃለህ ኢትዮጵያ ሁሉም [ጥሩ ኢንተርኔት] ተጠቃሚ አይደለም፡፡ 3G፣ 4G ከሆነ  ሂሳቡም በዚያ ልክ ነው የሚባለህ፡፡  አነስተኛ ገቢ ያለው እንደአቅሙ የሚጠቀመው አብዛኛውን ጊዜ 2G ነው፡፡ ስለዚህ በ2G ተጠቅሞ ይሄን አፕልኬሽን አውርዶ ከሚፈልገው ሰው ጋር ያለምንም ችግር መገናኘት ይችላል፡፡ መጻጻፍም መላላክም ይችላል በዚህ አፕልኬሽን” ሲል እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሀገሮች ለምን ተመራጭ እንደሆነ ያስረዳል፡፡  

Logos von WhatsApp & Viber
ምስል picture-alliance/dpa/Tass/S. Konkov

በርካታ ኢትዮጵያውያን እንደ ቫይበር፣ ዋትስአፕ እና ኢሞ የመሳሰሉ ሌሎች የመልዕክት መለዋወጫ አፕልኬሽኖችን ይጠቀማሉ፡፡ በኢትዮጵያ ያሉ የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች እንደሚናገሩት ብዙ ተጠቃሚዎችን በማፍራት ረገድ ቫይበር ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል፡፡ ዋትስ አፕ ይከተላል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢሞ የተሰኘው አፕልኬሽን ተጠቃሚዎች ቁጥር እየጨመረ እንደመጣ ባለሙያዎቹ ይገልጻሉ፡፡ የአዲስ አበባው ኤፍሬም ለድምጽ ቫይበርን፣ ለጽሁፍ መልዕክት እና ፎቶ መልዕክት መለዋወጫ ደግሞ ዋትስአፕን ያስቀድማል፡፡ የሳዑዲው ዩሱፍ ግን ኢትዮጵያውያን ሌሎቹን አፕልኬሽኖች ቢጠቀሙም “ዜሎን የሚመርጡበት ሌላም ምክንያት አለ” ይላል፡፡

“ሳዑዲ አረቢያን ለምሳሌ ብናመጣ ኢሞ እንኳን አሁን ደህና እየሰራ ነው ከዚህ በፊት ግን የግድ ቪፒኤን ተጠቅመን ነው፡፡ ዋትስ አፕ ራሱ ቀጥታ አይሰራልህም፡፡ የግድ ቪፒኤን ኮኔክሽን ተጠቅመን ነው፡፡ ይሄ ግን ያለምንም ነገር ሌላም አፕልኬሽን አይስፈለገንም ቀጥታ በራሱ አፕልኬሽን ወደ ፈለግህበት ሀገር፣ ዜሎ አፕልኬሽን ያለው ሰው ጋር መልዕክት ማስተላለፍ ትችላለህ” ሲል በአረብ ሀገራት ባሉ ኢትዮጵያውያን ዘንድ የመዘውተሩን ምክንያት ያብራራል፡፡

ኤፍሬም ዜሎ ከተለመዱት ከእነ ቫይበር እና ዋትስ አፕ የሚለየው ሌላ ባህሪ አለው ይላል፡፡ “ከዋትስ አፕም ከቫይበርም ለየት የሚያደርገው ነገር ያየሁበት ቻናልስ የሚባል አዲስ ነገር አለ፡፡ ምንድነው ቻናልስ? አሁን ለምሳሌ በአሜሪካን ሃይሪከን ጊዜ በጣም ሰዎች እየተጠቀሙበት ነበር፡፡ ለምንድነው እንደዚያ ሊሆን ይችላል? አንድ አካባቢ ያሉ ሰዎች አንድ ቻናል ውስጥ ይገቡ እና ርዳታ ሲፈልጉ አሁን ለምሳሌ እርስ በእርስ መቀናጀት ይችላሉ፡፡ ስለዚያ ከፍተውት ልክ እንደ ሬድዮ ሰዎች የሚሉትን መስማት እነርሱም ደግሞ ቻናሉ ከፈቀደላቸው ማለት የሚፈልጉትን ማውራት ይችላሉ፡፡ አንዳንድ ቻናል ለምሳሌ እርስ በእርስ ሰው ላያወራበት ይችላል፡፡ ቻናሉን የፈጠረው ሰው የሚያስተላልፈውን መልዕክት እንደሬድዮ መስማት ይችላሉ፡፡ አንዳንድ ቻናሎች ደግሞ ሲፈቅዱ ሰዎች ማውራት የሚችሉበት ነገር አለ፡፡ ይሄ ደግሞ ለአደጋ ጊዜ ወይም ሰዎችን አንድ ላይ አደራጅተህ ወይም አቀናብረህ ለማስኬድ የሚጠቅም አፕልኬሽን ነው ማለት ነው” ይላል ኤፍሬም፡፡

ዜሎ እስከ አምስት ሰዎች ድረስ የሚደረግን እንዲህ አይነት ግንኙነት በነጻ መጠቀም ይፈቅዳል፡፡ ከዚያ በላይ ከሆነ ግን ለአገልግሎቱ ያስከፍላል፡፡ እንደኤፍሬም ገለጻ ከሆነ በአንድ የዜሎ ቻናል ላይ እስከ 2‚500 ሰዎች  መልዕክት መለዋወጥ ይችላሉ፡፡

 

ተስፋለም ወልደየስ

ነጋሽ መሐመድ