1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሐሙስ ሚያዝያ 3 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የዓለም ዜና

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 3 2016

አርዕስተ ዜና፦ መቐለ፥ ትግራይ ክልል «በእሥር ላይ ናቸው» የተባሉ የመከላከያ ሠራዊት አባላት፥ መቂ፤ የፖለቲከኛ ቤቴ ኡርጌሳ ስርዓተ ቀብር ተፈጸመ፤ ጄኔቫ፥የሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነት እንዲያከትም ተመድ ጥሪ አስተላለፈ፤ ጋዛ፥ የፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን ሐማስ መሪ ሦስት ልጆች ተገደሉ፤ ኪዬቭ፥ ሩስያ የዩክሬን የኃይል ማመንጫዎችን በሚሳይሎች ደበደበች፤ ኢዝላማባድ፥ ፓኪስታን ለኢድ በዓል ሲጓዙ የነበሩ መንገደኞች አውቶቡስ ተገልብጦ 17 ሞቱ

https://p.dw.com/p/4efbX

አርዕስተ ዜና

* ትግራይ ክልል ውስጥ በእስር የሚገኙ የቀድሞ የመከላከያ አባላት ሞተዋል በሚል በመንግሥት መርዶ ቢነገረንም አሁንም በሕይወት አሉ ሲሉ ቤተሰቦች ለዶይቸ ቬለ ገለጡ ። ወታደሮቹ ሞተዋል ከተባለ በኋላ በቀይ መስቀል በኩል ቤተሰቦቻቸው ጋር በስልክ መገናኘታቸውን የወታደሮቹ ቤተሰቦች ተናግረዋል ።

*የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር ፖለቲከኛ በቴ ዑርጌሳ ስርዓተ ቀብር ዛሬ በትውልድ ሥፍራቸው መቂ ከተማ መካነ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን ተፈጸመ ። በግድያው ላይ ገለልተኛ እና የተሟላ ምርመራ በአፋጣኝ እንዲደረግ ዩናይትድ ስቴትስን ጨምሮ በርካቶች ጥሪ አስተጋብቷል ።

*ሩስያ ከአየር በተሰነጠሩ መጠነ ሰፊ ጥቃቶች ከዩክሬን ዋና ከተማ ኪዬቭ አቅራቢያ የሚገኘውን ግዙፉን የኃይል ማመንጫ አወደመች ። በጥቃቱ በርካታ የዩክሬን ግዛቶች የኃይል መቋረጥ ተከስቷል ።

ዜናው በዝርዝር

መቐለ፥ ትግራይ ክልል «በእሥር ላይ ናቸው» የተባሉ የመከላከያ ሠራዊት አባላት

ትግራይ ክልል ውስጥ በእስር የሚገኙ የቀድሞ የመከላከያ አባላት ሞተዋል በሚል በመንግሥት መርዶ ቢነገረንም አሁንም በሕይወት አሉ ሲሉ ቤተሰቦች ለዶይቸ ቬለ ገለጡ ። ወታደሮቹ «የሰሜን ኢትዮጵያ» በሚል በሚታወቀውና በፕሪቶሪያ የግጭት ማቆም ስምምነት በተቋጨው ትግራይ፣ አማራ እና አፋር ክልሎችን ባደቀቀው ጦርነት ተሳታፊ የነበሩ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት መሆናቸውንም ቤተሰቦች ተናግረዋል ። በትግራይ ክልል ተዋጊ ኃይሎች ተይዘው በእሥር ላይ የሚገኙ የእነዚህ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ጉዳይ እጅጉን እንዳሳሰባቸው ቤተሰቦቻቸው ለዶቼ ቬለ ገልጠዋል ። ስማቸውን መግለጥ ያልፈለጉ የአንድ ወታደር የእህት ባል መርዶው ሲነገር በቤተሰቡ ዘንድ ተፈጠረ ያሉትን አስደንጋጭ ክስተት ተናግረዋል ።   

«እኔ የእህቱ ባል ነኝ ። መንግሥት ሞቷል ሲል በድንጋጤ እህቱም ሞተች ። አንድ ወንድሙም ሞተ በድንጋጤ ማለት ነው ። አሁን አጋጣሚ ቀይ መስቀሎች ናቸው እኔ ጋ የደወሉት ። ባለፈው ሁለት መቶ ምናምን ሲፈታ ራሱ እሱ ምንም ተስፋ እንደሌለው ነው የነገረው ።»

በሐረር ፣ ሚዛን አማን እና ነገሌ ቦረና አካባቢ የሚኖሩ የሠራዊቱ አባላት ቤተሠቦች እንዳሉት ከሆነ፦ የቤተሰባቸው አባል የሆኑ ወታደሮች «በጦርነቱ ሞተዋል» ተብሎ በመንግሥት መርዶ ተነግሯቸው ነበር ። ይህ ከሆነ በኋላ ግን በቀይ መስቀል በኩል ከወታደር ቤተሰቦቻቸው ጋር በስልክ እንደተገናኙና አሁንም አልፍ አልፎ ስልክ እንደሚደውሉላቸው የወታደሮቹ ቤተሰቦች ተናግረዋል ። በጉዳዩ ላይ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደርን ለማግኘት የአዲስ አበባ ወኪላችን ሰለሞን ሙጬ ተደጋጋሚ ጥረት ቢናደርግም ለጊዜው ሊገኙ አልቻለም ። ጊዜያዊ አስተዳደሩ «በከባድ ወንጀል ተጠርጥረው በእሥር ላይ የቆዩ» ያላቸውን 212 የመከላከያ ሠራዊት አባላት ባለፈው መጋቢት 2016 ዓ.ም መልቀቁን አስታውቆ ነበር። በዜና መጽሄት ተጨማሪ ዘገባ ይኖረናል። 

መቂ፥ የፖለቲከኛ ቤቴ ኡርጌሳ ስርዓተ ቀብር ተፈጸመ

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር ፖለቲከኛ በቴ ዑርጌሳ ስርዓተ ቀብር ዛሬ በትውልድ ሥፍራቸው መቂ ከተማ መካነ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን ተፈጸመ ። አቶ በቴ ማክሰኞ ሚያዝያ 1 ቀን፣ 2016 ዓ.ም.  በጥይት ተደብድበው መገደላቸውና አስከሬናቸውም ከመቂ ከተማ ወደ ባቱ (ዝዋይ) መውጫ መንገድ ዳር ተጥሎ የተገኘው ትናንት ማለዳ እንደነበር ተዘግቧል ። አንድ የቤተሰብ አባል ለዶይቸ ቬለ እንደ ተናገሩት፦ የአቶ በቴ አስከሬን ትናንት ጠዋት ከመንገድ የተነሳው በአከባቢው ማኅበረሰብ እና ቤተሰቦቻቸው ነበር ።

«ቤተሰብ ስንሄድ ፖሊስ እዚያ አላገኙም ። እንደዚህ ኑ እንውሰድ ያላቸው አካል የለም ። እነሱ አሁን ሞቷል ልጃቸው ። ከዚህ በኋላ ወደ ሆስፒታል መሄድ ምንድን ነው አስፈላጊነቱ ብለው [አስክሬኑን] ቀጥታ ወደ ቤት አመጡት ማለት ነው ። ከዚያ በኋላ ሕግ የሚያውቁ ሰዎች ናቸው ቢመረመር ብለው ምክረ ሐሳብ ሲያቀርቡ ዛሬ የሆስፒታል ባለሞያዎችን ጠይቀን ወደዚያ እንዲወሰድ ተደረገ ማለት ነው ።»

ፖሊስ አስከሬኑን ለምርመራ ባይወስድም፤ ትናንት ጠዋት መረጃዎችን አሰባስቦ ስለመሄዱም እኚህ የቤተሰብ አባል ለዶይቼ ቬለ አክለው ገልጠዋል ። የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በአቶ በቴ ዑርጌሳ ላይ የተፈጸመውን የግድያ ወንጀል አጣርቶ ለሕዝብ ይፋ ያደርጋል ሲል ዐስታውቋል ። ምርመራው በፀጥታ አካላት ተጣርቶ ይፋ እስኪደረግ ተጠያቂነቱን ለየትኛውም አካል ከመስጠት መቆጠብ ያስፈልጋልም ሲል አክሏል ። የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የአቶ በቴ ግድያ ገለልተኛ እና ሙሉ በሆነ ምርመራ በአፋጣኝ ተጣርቶ ወንጀለኞች ለሕግ እንዲቀርቡ ሲል ጠይቋል ። የዩናይትድ ስቴትስ መንግስትም በውጪ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ የአፍሪቃ ጉዳዮች ጽ/ቤት በኩል ባወጣው አጭር መግለጫ፦ የኢሰመኮን ጥሪ መቀላቀሉን ገልጧል ።  በአቶ በቴ ግድያ ዙሪያ ሙሉ ምርመራ እንዲደረግ ጠይቋል ። ፍትሕና ተጠያቂነትን ማስፈን ከግጭት አዙሪት ለመውጣት ወሳኝ መሆኑን አስረድቷል ። የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር ፖለቲከኛ በቴ ዑርጌሳ ከትናንት በስቲያ ማክሰኞ ሚያዚያ 01 ቀን 2016 ዓ.ም. ሌሊቱን ተገድለው ትናንት ጠዋት አስከሬናቸው በትውልድ ቀዬያቸው መቂ ከተማ መገኘቱን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ጄኔቫ፥የሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነት እንዲያከትም ተመድ ጥሪ አስተላለፈ

አንድ ዓመት ሊደፍን በጣት የሚቆጠሩ ቀናት የቀሩት የሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነት እንዲቆም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ጥሪ አስተላለፈ ። ተመድ ከጄኔቫ ዛሬ ባስተላለፈው መልእክት ጦርነቱ፦ «ለሱዳናውያን ከሚሸከሙት በላይ ሆኗል» ብሏል ። የፊታችን ሰኞ፤ ሚያዝያ 7 ቀን፣ አንድ ዓመት በሚሞላው የሱዳን ጦርነት የተነሳ በሺህዎች የሚቆጠሩ ተገድለዋል ከስምንት ሚሊዮን በላይ ተፈናቅለዋል የሰብአዊ ርዳታ ለጋሾች በሱዳን የሰብአዊ ቀውሱ አሁን ካለበትም ሊባባስ እንደሚችል በተደጋጋሚ አስጠንቅቀዋል ።  በሱዳን ጦር ሠራዊት ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም እና የሀገሪቱ የበላይ ጄነራል አብደል ፈታህ አል-ቡርሃን ፊታውራሪነት የተጀመረው ጦርነት አንድ ዓመት ሊደፍን አራት ቀናት ብቻ ይቀሩታል ።

ጋዛ፥ የፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን ሐማስ መሪ ሦስት ልጆች ተገደሉ

እስራኤል፣ ዩናይትድ ስቴትስ፣ የአዉሮጳ ኅብረት፣ ብሪታንያና ተከታዮቻቸዉ በአሸባሪነት የፈረጁት የፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን ሐማስ መሪ ሦስት ልጆች ተገደሉ ። የእሥራኤል ጦር ከአየር በሰነዘረው ጥቃት ተሽከርካሪ ውስጥ እንዳሉ የተገደሉት የሐማስ ወታደራዊ አባላት ናቸው ብሏል ። እሥራኤል  ሰሜን ጋዛ ሠርጥ ውስጥ ትናንት በወሰደችው የአየር ጥቃት የሐማስ ኃላፊ እስማኤል ሀኒዬህ  ሦስት ልጆች እና አራት የልጅ ልጆች መገደላቸውን የሐማስ ታጣቂ ቡድኑ ገልጧል ። ሌሎች ተጨማሪ ዐሥር ልጆች እንዳላቸው የሚነገርላቸው የሐማስ መሪ ስለ ቤተሰቦቻቸው መርዶ ሲነገራቸው የሚያሳይ የቪዲዮ ምስል ታይቷል ። እሥማኤል ሀኒዬህ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2019 ከጋዛ ወጥተው ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በግዞት የሚኖሩት ካታር ውስጥ ነው ።

ኪዬቭ፥ ሩስያ የዩክሬን የኃይል ማመንጫዎችን በሚሳይሎች ደበደበች

ሩስያ ከአየር በተሰነጠሩ መጠነ ሰፊ ጥቃቶች ከዩክሬን ዋና ከተማ ኪዬቭ አቅራቢያ የሚገኘውን ግዙፉን የኃይል ማመንጫ አወደመች ። በጥቃቱ በርካታ የዩክሬን ግዛቶች የኃይል መቋረጥ ተከስቷል ። ሩስያ ከ80 በላይ ሚሳይሎችን እና ሰው አልባ ከሰው አልባ ጢያራዎች የተወነጨፉ ቦንቦችን ኪዬቭ ላይ አዝንባለች ። ሩስያ ጥቃቱን የሰነዘረችው ዩክሬን የነዳጅ፤ የጋዝ እና የኃይል ተቋማቴ ላይ ላደረሰችው የሰው አልባ ጢያራ ጥቃት የበቀል ምላሽ ነው ብላለች ።  የዩክሬን መከላከያ ከሩስያ በኩል ከተወነጨፉ 82 ሚሳይሎች 18ቱን እና 39 ሰው አልባ ጢያራዎችን አየር ላይ መትቶ መጣሉን ዐስታውቋል ። በሩስያ ብርቱ የአየር ጥቃት ግን ዩክሬን በኃይል ምንጩዋ ላይ ብርቱ ጉዳት መድረሱን ገልጣአልሸሸገችው ። ጥቃቱ ሩስያ ላለፉት ሁለት ዓመታት ዩክሬን ውስጥ ከሰነዘረችው የከፋው ነው ተብሏል ።

ኢዝላማባድ፥ ፓኪስታን ለኢድ በዓል ሲጓዙ የነበሩ መንገደኞች አውቶቡስ ተገልብጦ 17 ሞቱ

ደቡብ ምዕራብ ፓኪስታን ውስጥ የኢድ አልፈጥር በዓልን ለማክበር ተራራማው ላስ ቤላ ውስጥ ወደሚገኘው የእምነት ሥፍራ መንገደኞችን አሳፍሮ ሲጓዝ የነበረ አውቶቡስ ተገልብጦ ቢያንስ 17 ሰዎች ሞቱ ። የተለያዩ የዜና አውታሮች ትናንት ባሎሽታይን አውራጃ ውስጥ በእኩለ ሌሊት በተከሰተው አደጋ ከ41 እስከ 50 የሚደርሱ ምእመናን ላይ የመቁሰል አደጋ መድረሱን ዘግበዋል ። አውቶብሱ ከመገልበጡ በፊት ፍጥነቱን እንደጨመረና አሽከርካሪውም ለማጠምዘዝ ሲሞክር ከቁጥጥር ውጪ እንደወጣበት የአካባቢው ባለሥልጣናት ተናግረዋል ። «አሽከርካሪው ከአውቶቡሱ ዘሎ በመውጣት ሕይወቱን እንዳተረፈም» ባለሥልጣናቱ አክለዋል ። ከቆሰሉት መካከል 15ቱ ጽኑእ አደጋ የደረሰባቸው ሲሆን፤ ወደ አጎራባቹ የሲንድህ አውራጃ ካራቺ ውስጥ ወደሚገኝ ሐኪም ቤት መወሰዳቸው ተዘግቧል ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሠ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ከዚሕ ዝግጅት ተጨማሪ

ከዚሕ ዝግጅት ተጨማሪ

Äthiopien Alamata City Gondar
ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ስለዚሕ ዝግጅት

ስለዚሕ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።