1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሚያዝያ 12 ቀን 2016 ዓ/ም የዓለም ዜና

Tamirat Geletaቅዳሜ፣ ሚያዝያ 12 2016

https://p.dw.com/p/4f0kr

 

የአፋር እና የሶማሌ ክልሎች በአዋሳኝ አከባቢዎች የሚቀሰቀሱ ግጭቶች እንዲቆሙ እና እርቅ እንዲወርድ ከስምምነት መደረሱን የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አስታወቀ፡፡

ምክር ቤቱ ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጠው መግለጫ በምክር ቤቱ ፕሬዚደንት ሸይኽ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ አደራዳሪነት ሲካሄድ የቆየው የአፋርና የሶማሌ ክልሎች የእርቀ ሰላም ውይይት ሁለቱ ክልሎች ተኩስ ለማቆም ከስምምነት ላይ በመድረስ መጠናቀቁን  የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት ሸይኽ አብዱልከሪም ሸይኽ ቤድረዲን ተናግረዋል።

“ለብዙ ወራትና ዘመናት ሲጋጩና ደም ሲፋሰሱ የነበሩ ወንድማማቾች መካከል ስር ነቀል እርቅ ለማምጣት በምክር ቤታችን መሪ በኩል የተጀመረው የሽምግልና ሂደት ከብዙ ጥረት በኋላ ኡጋዞች እና የጎሳ መሪዎችን በማነጋገር ተኩስ አቆም ስምምነት ላይ ተደርሷል”

በሁለቱ ጎሳዎች መካከል ሰላምነብ ያወረደው እርቁ ለአገርም ትልቅ ትርጉም እንዳለው ተጠቁሟል፡፡  ከሀጎሳ መሪዎች እና ኡጋዞች ጋር በተናጥል የተደረጉ ውይይቶች ረጂም ሂደት የወሰደ  መሆኑን የገለጸው የምክር ቤቱ መግለጫ በመንግስት በኩልም ከዚህ ቀደም ሰፊ የእርቅ ጥረት ተደርጎ እንደነበር የአዲስ አበባው ወኪላችን ስዩም ጌቱ ዘግቧል።

 

 

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ኮንታ ዞን በረዶና ንፋስ ቀላቅሎ የጣለ ዝናብ 157 የመኖሪያ ቤቶች ላይ በሙሉና በከፊል ጉዳት አደረሰ ፤ በ468 ሄክታር ላይ የነበረ ሰብልን አወደመ ፡፡

የዞኑ መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን መምሪያ ሃላፊ አቶ አበበ ጎበና ለዶቼ ቬለ አንዳሉት በረደ የቀላቀለው ብርቱ  ዝናብ በዞኑ በሚገኙ 32 ቀበሌዎች ውስጥ ጉዳት አድርሷል ፡፡

ካለፈው ሐሙስ ጀምሮ እስከ ትናንት አርብ ድረስ በተከታታይ በጣለው በረዶ የቀላቀለው ዝናብ  በሰው ላይ የደረሰ ጉዳት ባይኖርም ሰባ ዘጠኝ የመኖሪያ ቤቶችን በሙሉና ሰባ ስምንቱን ደግሞ በከፊል አውድሟል። በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ቤት አልባ አድርጓል።

«ሰባ ዘጠኝ መኖሪያ ቤቶች ሙሉ በሙሉ ወድመዋል። እነዚህ ሙሉ በሙሉ የወደሙ ሲሆኑ በከፊል 78 የሚሆኑ ወድመዋል። እንደአጠቃላይ 260 የቤተሰብ አባላት ተፈናቅለው በተለያዩ ቦታዎች ተጠልለው ይገኛሉ።»

በተጨማሪም በ468 ሄክታር ላይ የሚገኝ የቦቆሎ ፣ የማሽላ እና የቦሎቄ ማሳዎችን ማውደሙንም የመምሪያው ሃላፊ ገልጸዋል ፡፡

በአሁኑ ወቅት የመኖሪያ ቤቶቻቸውና ሰብላቸው ለወደመባቸው ቤተሰቦች አስቸኳይ የሰብአዊ ድጋፍ ለማድረግ ጥረት በመደረግ ላይ እንደሚገኝም ሃላፊው ጠቅሰዋል ፡፡

 

የዓለም የጤና ድርጅት የተሻሻለ የኮሌራ መከላከያ ክትባት ስራ ላይ እንዲውል መፍቀዱን ትናንት አርብ አስታወቀ። ከነባሩ የኮሌራ መከላከያ ቀለል ያለነው የተባለለት ክትባቱን በብዛት በማቅረብ ወረርሽኙ እየጨመረ የመጣውን በሽታ ለመቆጣጠር ተስፋ ተጥሎበታል።

 የደቡብ ኮሪያ የመድሃኒት አምራች ኩባንያ የሆነው ኢዩባዮሎጂክስ ምርት የሆነ እና ኢውቪኮል የሚል መጠሪያ የተሰጠው የተሻሻለው የኮሌራ ክትባት ከነባሩ ጋር ተመሳሳይ የመከላከል አቅም ያለው መሆኑን የገለጸው ዓለማቀፉ ድርጅት በፍጥነት እና በብዛት ለማምረት ተመራጭ መሆኑን ገልጿል።

 ክትባቱ በፍጥነት  ጥቅም ላይ እንዲውል ፈቃድ መስጠቱንም ድርጅቱ አመልክቷል።  በጎርጎርሳዉያኑ 2022 473 ሺ በኮሌራ የተያዙ ሰዎች በዓለም የጤና ድርጅት ተመዝግበው የነበሩ ሲሆን ባለፈው የጎርጎርሳዉያኑ 2023 አሃዙ ከ700 ሺ በላይ ማሻቀቡን ተከትሎ ወረርሽኙ በበርካታ ሃገራት ስጋት ሆኗል።

በዓለም ላይ 23 ሃገራት በኮሌራ ወረርሽኝ ሲጠቁ ኢትዮጵያን ጨምሮ ኮሞሮስ ዲሚክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፣ ሞዛምቢክ ፣ ሶማሊያ ፣ ዛምቢያ እና ዚምቧብዌ ወረርሽኙ ጎልቶ የታየባቸው ሃገራት መሆናቸውን ድርጅቱ ይፋ አድርጓል። የተሻሻለው የኮሌራ ክትባት በብዛት እና በፍጥነት ከመመረት ባሻገር እስከ 2 ዓመት ድረስ በክምችት ሊቆይ መቻሉ በሽታውን ለመከላከል ተስፋ አሳድሯል  ።

 

እስራኤል በምዕራባዊ የዮርዳኖስ ወንዝ ዳርቻ ኑር ሻምስ ውስጥ በሚገኝ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ  ባደረገችው ወታደራዊ ዘመቻ 10 ያህል የፍልስጥኤማውያን ታጣቂዎችን መግደሏን አስታወቀች። የእስራኤል ጦር በስደተኞች መጠለያ ጣቢያው አካባቢ ከ40 ሰዓታት ለዘለቀ ጊዜ ከታጣቂ ቡድኑ መከላከል እንደገጠመው አስታውቋል። በውጊያው አንድ የፖሊስ መኮንን ጨምሮ 8 የእስራኤል ወታደሮች ቆስለዋል።

 ወደ መጠለያ ጣቢያው ሰው እንዳይገባ ክልከላ መጣሉን ተከትሎ  የኃይል አቅርቦት መቋረጡን እና የምግብ ክምችቱ እየተሟጠጠ መምጣቱን ነዋሪዎች ለፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘጋቢ ተናግረዋል።

 የእስራኤል ጦር ኃይል በምዕራባዊ የዮርዳኖስ ወንዝ ዳርቻ ስደተኞች በተጠለሉባቸው ከተሞች ታጣቂ የሚሊሻ ቡድኖችን ዒላማ ያደረገ ወታደራዊ ዘመቻ እንደምታደርግ ብታስታውቅም በዘመቻው ህይወታቸውን የሚያጡት ሰላማዊ ሰዎች መሆናቸውን ዘገባው አመልክቷል። በእስራኤል እና ሃማስ መካከል ጦርነት ከተቀሰቀሰ ወዲህ በኃይል በተያዘችው  የምዕራባዊ የዮርዳኖስ ወንዝ ዳርቻ 480 ፍልስጥኤማውያን ተገድለዋል።

 

ኢራቅ ውስጥ በሚገኝ አፍቃሬ ኢራን ታጣቂዎች  ጥምረት  ወታደራዊ የጦር ሰፈር ላይ የአየር ጥቃት መፈጸሙን ባለስልጣናት አስታወቁ። በጥቃቱ አንድ ሰው ሲገደል ሌሎች ስምንት ሰዎች ቆስለዋል። ለጥቃቱ ኃላፊነት የወሰደ ወገን የለም። በጥቃቱ ስለደረሰ ሰብአዊ እና ቁሳዊ ውድመት እስካሁን የተባለ ነገር የለም። 

ከባግዳድ በስተደቡብ በሚገኘው የባቢሎን ግዛት የሚገኘው የካልሱ የጦር ሰፈር ፍንዳታው ሲደርስ የኢራቅ መደበኛ ጦር፣ፖሊስ እና የኢራቅ ሃሺድ አል-ሻቢ አባላት በስፍራው እንደነበሩ የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል ። በኢራቅ የጦር ሰፈር ላይ የደረሰው የአየር ጥቃት የዛሬ ሳምንት ሌሊት ላይ ኢራን መጠነ ሰፊ የአየር ጥቃት ካደረሰች እና ከትናንት ለትናናት አጥቢያ እስራኤል የአጸፋ ጥቃት በኢራን ላይ ከሰነዘረች በኋላ ነው ።

 በግዛቲቱ ከፍንዳታው አስቀድሞ ምንም አይነት የድሮንም ሆነ የተዋጊ አውሮፕላን እንቅስቃሴ እንዳልነበር የኢራቅ የጸጥታ ኃይሎች አስታውቀዋል። ዩናይስትድ ስቴትስ በጥቃቱ እጄ የለበትም ብላለች። እስራኤል በበኩሏ ለመሰል ጥያቄዎች ለውጭ የመገናኛ ብዙኃን መልስ የመስጠት ፍላጎት እንደሌላት ገልጻለች። የጦር ሰፈሩን ይገለገልበት የነበረው የሃሼድ አል ሻቢ ታጣቂ ቡድን በበኩሉ በጥቃቱ ሰብአዊ እና ቁሳዊ ኪሳራ መድረሱን ቢገልጽም በጥቃት ምን ያህል ሰዎችን እንደተገደሉ ከመግለጽ ግን ተቆጥቧል።

 

አትሌት ጉዳፍ ጸጋይ እና ለሜቻ ግርማ በቻይና ዥያሜን በተካሄደ የዳይመንድ ሊግ ውድድሮች አሸነፉ ። በ1500 ሜትር ርቀት የተወዳደረችው ጉዳፍ በርቀቱ ሶስተኛውን የዓለም ፈጣን ሰዓት በማስመዝገብ አሸንፋለች። ጉዳፍ ርቀቱን ለማጠናቀቅ 3:50.30 ወስዶባታል። ጉዳፍን ተከትለው ብርቄ ኃይሎም እና ወርቅነሽ መሰለ ሁለተኛ እና ሶስተኛ ሆነው በመግባት ውድድሩን በአንድ ሀገር አትሌቶች መካከል የተደረገ አስመስለውታል። በውድድሩ ከስድስተኛ ደረጃ በቀር ከ1 ኛ እስከ ስምንተኛ ደረጃ ያለውን ኢትዮጵያውያን ተቆጣጥረውታል።  ይህ በእንዲህ እንዳለ በወንዶች ምድብ በአምስት ሺ ሜትር አትሌት ለሜቻ ግርማ አሸንፏል። የ 3 ሺ ሜትር የመሰናክል ሩጫ የክብረ ወሰን ባለቤቱ ለሜቻ ግርማ በተሳተፈበት የ5 ሺ ሜትር ውድድሩን ለማጠናቀቅ 12:58.96 ወስዶበታል። ኬንያዊው ኪፕሮፕ ኒኮላስ እና ባህሬናዊው በለው ብርሃኑ ሁለተኛ እና ሶስተኛ ሆነው አጠናቀዋል። ዛሬ በቻይና ዢያሜን የተጀመረው የዲያመንድ ሊግ ውድድር ስድስት ወራት ሲወስድ  በመላው ዓለም በሚገኙ 15 ከተሞች ውስጥ እንደሚካሄድ ዓለማቀፉ የአትሌቲክስ ማህበር አስታውቋል።

 

ታምራት ዲንሳ

እሸቴ በቀለ

 

 

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ከዚሕ ዝግጅት ተጨማሪ

ከዚሕ ዝግጅት ተጨማሪ

Äthiopien Alamata City Gondar
ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ስለዚሕ ዝግጅት

ስለዚሕ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።