1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሚያዝያ 14 ቀን 2016 ዓ/ም የዓለም ዜና

Tamirat Geletaሰኞ፣ ሚያዝያ 14 2016

https://p.dw.com/p/4f4AO

 

 

ኢትዮጵያ ውስጥ የተወሳሰቡ የፖለቲካ እና የጸጥታ ቀውሶችን ለመፍታት ብሎም በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ ብቸኛው መንገድ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ያሳተፈ ውይይት ማድረግ መሆኑን በኢትዮጵያ የሚገኙ የ 7 ሀገራት ኤምባሲዎች በጋራ ባወጡት መግለጫ ገለፁ።

ሀገራቱ ውዝግብ በተነሳባቸው የሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎች "እየደረሰ ያለው ጥቃት" እንዳሳሰባቸው በጋራ መግለጫቸው አስታውቀዋል። 

በአዲስ አበባ የሚገኙት የካናዳ፣ የፈረንሳይ፣ የጀርመን፣ የጣሊያን፣ የጃፓን፣ የእንግሊዝ እና የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲዎች "የተወሳሰቡ የፖለቲካ እና የጸጥታ ቀውሶችን ለመፍታት እና በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ ሁሉንም ባለድርሻዎች ያሳተፈ ውይይት ብቸኛው መንገድ ነው።" ማለታቸው የአዲስ አበባው ወኪላችን ሰለሞን ሙጬ ዘግቧል።

 የኤምባሲዎቹ የጋራ መግለጫ የተሰማው  ትግራይ እና አማራ ክልሎች ከሚወዛገቡባቸው ቦታዎች አንዱ በሆነው ራያ ሰሞኑን 29 ሺህ በላይ ሰዎችን ያፈናቀለ ሌላ ዙር ችግር መከሰቱን ተከትሎ ነው።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ጌታቸው ረዳ  በወቅቱ  የፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት ጠላት የሆኑ ሐይሎች ግጭት ለመፍጠር እየጣሩ ነው በማለት ከሰዋል።

አማራ ክልል መንግስት በበኩሉ «ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) የፕሪቶሪያውን ስምምነት ሙሉ በሙሉ በመጣስ ለአራተኛ ዙር ሕዝባችን ላይ ወረራ ፈፅሟል» ማለቱ ይታወሳል። የምሽቱ ዜና መጽሔት በዚሁ ጉዳይ ላይ ዝርዝር ዘገባ ይዟል።

 

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኮሬ ዞን ሦስት የአንድ ቤተሰብ አባላትን ጨምሮ አራት ሰዎች በታጣቂዎች ተገደሉ ፡፡  በዞኑ ጎርካ ወረዳ ቆቦ በተባለ ቀበሌ ውስጥ ትናንት እኩለ ቀን ላይ የተፈጸመውን ግድያ ያደረሱት ከአጎራባች የኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን ገላና ወረዳ የተነሱ ታጣቂዎች “ መሆናቸውን የአካባቢው  ነዋሪ ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል  ፡፡ ሟቾቹ ህይወታቸው ያለፈው በጥይት ተደብድበውና በስለት ተወግተው መሆኑን የጠቀሱት የአይን እማኞቹ “ ግድያው የተፈጸመባቸውም  በከብት ጥበቃ ላይ ተሰማርተው በነበሩበት  ወቅት ነው “ ብለዋል ፡፡

«ከአንድ ቤት ሶስት ሰው ነው የሞተው ፤ ወንድም አጎት የአጎት ልጅ ፤ ከብታቸውንም እነሱንም ገድለው ከረዥም ጊዜ በኋላ ነው ሬሳቸው የተደረሰበት ፤ ያስጠላል እንዲህ እንዲህ የሚባል ነገር የለውም። እነሱ እዚያ ሳር ላይ እያደሩ እያለ ከኋላቸው መጥተው ቀጥታ ልጆቹንም እዚያ ገደሉ።»

ዶቼ ቬለ በጥቃቱ ዙሪያ በኮሬ ዞን የጎርካ ወረዳ ሰላምና ፀጥታ ጽህፈት ቤት ሃላፊ  አቶ ብሩክ አየለ  “ ጥቃቱን እየገመገምን በመሆኑ ሲጠናቀቅ ዝርዝር መግለጫ እንሰጣለን “ ብለዋል ፡፡

ዶቼ ቬለ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የኮሬ ዞንና በኦሮሚያ ክልል የምዕራብ ጉጂ ዞን ሃላፊዎችን ለማግኘት አሁንም ተጨማሪ ጥረት ቢያደርግም ሊሳካለት አልቻለም ፡፡ የኮሬ ዞን ህዝብን በመወከል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት ዶክተር አወቀ ሃምዛዬ መንግስት ህዝቡን እንዲከላከል ጥሪ አቅርበዋል። ፡፡

«ዓላማው አንድ አናሳ ብሄረሰብን ለማጥፋት ያለመ ነው የሚመስለው ፤ እና መንግስት ይሄ አይደለም ብሎ የሚል ከሆነ ህዝቡን መከላከል መቻል አለበት ። ጦር ሰራዊት አስገብቶ የገላና ሸለቆ በነገራችን ላይ 20፣ 25 ኪሎሜትር ነው። እዚያ አማጺ ቁጭ ብሎ ህዝብ የሚፈጅበት ምንም ምክንያት የለም»

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኮሬ ዞን መነሻቸውን ከአጎራባች የምዕራብ ጉጂ ዞን ያደረጉ ናቸው የተባሉ ታጣቂዎች በአካባቢው ተደጋጋሚ ጥቃቶችን እየሰነዘሩ ይገኛሉ ፡፡በዞኑ ባለፉት አምስት አመታት ብቻ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በታጣቂዎች ሲገደሉ ከ50 ሺህ በላይ ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን ዶቼ ቬለ ከዚህ ቀደም ዘግቦ ነበር   ፡፡

 

በማዕከላዊ ማሊ በአውቶቢስ ሲጓዙ የነበሩ ከ110 በላይ ሲቪላውያን በእስላማዊ ጂሃዲስቶች ታግተው ተወሰዱ ። ጂሃዲስቶቹ ባለፈው ማክሰኞ በሶስት አውቶቢሶች በጉዞ ላይ የነበሩ ሰላማዊ ሰዎችን አግተው አቅራቢያ ወደ ሚገኝ ጫካ መውሰዳቸውን የማህበራት ህብረት እና የአካባቢው ባለስልጣናት ተናግረዋል። ታግተው የተወሰዱ ሰዎቹ በፍጥነት እንዲለቀቁም ማህበራቱ ጠይቀዋል። የማህበራት ጥምረቱ ባለፈው ዓርብ ባወጡት መግለጫ በአካባቢው እየተጠናከረ የመጣው የሽብርተኞች ጥቃት ለነዋሪዎች መፈናቀል መጨመር ምክንያት እየሆነ መምጣቱን አመልክቷል። በማሊ ባለፈው ነሀሴ የጂሃዲስቶችን ጥቃት ተከትሎ በተቀሰቀሰ አመጽ እና ተቃውሞ በርካቶች መገደላቸው ይታወሳል።

ከጎርጎርሳዊኑ 2012 ጀምሮ በአልቃይዳ እና በአይ ኤስ የሚደገፉ የተለያዩ አንጃዎች የሽብር ጥቃት የምትናጠው ማሊ ቀውሱ ድንበር ተሻግሮ ቡርኪና ፋሶ እና ኒጀርንም እያመሰ ይገኛል። ሶስቱም ሃገራት በወታደራዊ ሁንታ ይመራሉ ።

 

ብሪታንያ ለረዥም ጊዜ ሲያወዛግብ የነበረውን ተገን ጠያቂዎችን ወደ ርዋንዳ የማጋጓጓዝ መርሃ ግብሯን ተግባራዊ ማድረግ ልትጀምር ነው። ስደተኞችን የመከላከል ዕቅድ አካል የሆነው  የተገን ጠያቂዎችን ወደ ርቃንዳ ማጓጓዝ ከቀጣዩ ወር ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር ሪሺ ሱናክ ዛሬ ተናግረዋል። ተገን ጠያቂዎችን ከሀገር ለማስወጣት የሀገሪቱ መንግስት የያዘው ውጥን ለፓርላማው ቀርቦ ከመጽደቁ በፊት ሪሺ በሰጡት መግለጫ «በረራዎቹን ለማስጀመር ዕቅድ ተይዟል፤ ያንንም ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጁ ነን » ብለዋል።

የተገን ጠያቂዎችን ከሀገር መባረር በብርቱ የሚነቅፈው ኬር ፎር ካላይስ የተሰኘው የግብረ ሰናይ ድርጅት በበኩሉ የብሪታንያ መንግስት የያዘው ውጥን «ተግባራዊ ሊሆን የማይችል ፤በጭካኔ የተሞላበት» ሲል ተቃውሞውን አሰምቷል።

አዲሱ የሪሺ ሱናክ መንግስት ረቂቅ ህግ ዳኞች ምስራቅ አፍሪቃዊቷን ሀገር ርዋንዳን  እንደ ሶስተኛ ሀገር አድርገው እንዲመለከቱ የሚያስገድድ ሲሆን በአንጻሩ ሚንስትሮች የአለም አቀፍ እና የእንግሊዝ የሰብአዊ መብት ህግ ክፍሎችን ችላ ብለው ስራቸውን እንዲሰሩ  ስልጣን ይሰጣቸዋል።

የብሪታንያ መንግስት ከጎርጎርሳውያኑ 2018 ፍልስተኞችን መመዝገብ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከ120 ሺ በላይ ተገን ጠያቂዎች ባህር አቋርጠው ወደ ሀገሪቱ መግባት ችለዋል።

 

የአውሮጳ ህብረት የውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች የዩክሬን የአየር መከላከያን ማጠናከር በሚችሉበት እና ኢራን ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ በሚጥሉበት ሁኔታ ላይ ለመምከር ዛሬ ሉክሰምበርግ ውስጥ ተሰባስበዋል። ሩስያ በዩክሬን የኃይል መሰረተ ልማት ላይ እያደረሰች ያለው አውዳሚ ጥቃት ህብረቱ ተጨማሪ የአየር መከላከያ ለዩክሬን የማቅረብ ግዴታ ውስጥ ሳያስገባው እንዳልቀረ ነው የተዘገበው።

  የዩናይትድ ስቴትስ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ትናንት ለዩክሬን እንዲሰጥ ያጸደቀው የ60 ቢሊዮን ዶላር የእርዳታ ማዕቀፍ አውሮጳውያኑንንም የልብ ልብ እንዲሰማቸው ማድረጉን ነው ዘገባው ያመለከተው።

 የውጭ ጉዳይ ሚንስትሮቹ ስብሰባ ውጤት ሳይሰማ ጀርመን በተናጥል ከዩክሬን ለቀረበላት ጥሪ ተጨማሪ የፓትሮይት የአየር መከላከያ ስረዓት ለመስጠት ቃል መግባቷ ተሰምቷል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሚንስትሮቹ ኢራን ባለፈው ሳምንት በእስራኤል ላይ ላዘነበችው የሚሳኤል እና የድሮን ጥቃት ተመጣጣኝ ነው ያሉትን ማዕቀብ ለመጣል እየመከሩ ነው። የውጭ ጉዳይ ሚንስትሮቹ በስብሰባቸው እግረመንገድ የሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነትንም እንደሚመለከቱ ሮይተርስ ዘግቧል።  

 

ሩስያ በአጎራባች ሃገራት የኒኩልየር የጦር መሳሪያ መትከሏን ተከትሎ የሰሜን ቃል ኪዳን ጦር ጥምረት ኔቶ የኒውክሊር ጦር መሳሪያ ለመታጠቅ ዝግጁ መሆኗን ፖላንድ አስታወቀች። የሩስያ በአጎራባች ሀገራት በኒውክለየር መስፋፋት አጋሮቻቸው የምስራቃዊ ክንፍን ለማጠናከር የጦር መሳሪያውን ለማስታጠቅ ከወሰኑ እኛ ዝግጁ ነን ሲሉ የፖላንዱ ፕሬዚዳንት አንድሬ ዱዳ ተናግረዋል። ሞስኮ በበኩሏ «ደህንነቷን ለማረጋገጥ» የበለጠ እርምጃ እንደምትወስድ አስጠንቅቃለች። የፖላንዱ ፕሬዚዳንት የኒኩልየር የጦር መሳሪያ ስለመታጠቅ የተናገሩት ኒውዮርክ ውስጥ በመንግስታቱ ድርጅት ስብሰባ ላይ ከተሳተፉ በኋላ በዩክሬን ጦርነት ጉዳይ ላይ ከቀድሞው የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ከመከሩ በኋላ ነው ተብሏል።

የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን  ባለፈው ዓመት  ሰኔ ወር  ሩሲያ ዩክሬንን እና ፖላንድን ወደሚያዋስናት ቤላሩስ ታክቲካል የኒውክሌር ጦር መሳሪያ መላኳን አረጋግጠዋል።የኔቶ አባል ሃገራት በበኩላቸው  በቪልኒየስ ባካሄዱት ስብሰባቸው   «የኑክሌር መከላከያ ተልዕኮን ተዓማኒነት፣ ውጤታማነት፣ እና ደህንነት ለማረጋገጥ ሁሉንም አስፈላጊ እርምጃዎችን ለመውሰድ» ቃል ገብተዋው ነበር።

ታምራት ዲንሳ 

አዜብ ታደሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ከዚሕ ዝግጅት ተጨማሪ

ከዚሕ ዝግጅት ተጨማሪ

Äthiopien Alamata City Gondar
ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ስለዚሕ ዝግጅት

ስለዚሕ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።