1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስ

የኢትዮጵያውያኑን በ100 ሺህ ዓመት ይበልጣል ተብሏል  

ረቡዕ፣ ሰኔ 7 2009

ለዛሬው ዘመን ሰው የቀረበ ነው የተባለ ቅሪተ አካል በሞሮኮ መገኘቱን ባለፈው ሳምንት አጋማሽ ይፋ ተደርጓል፡፡ የቅሪተ አካላቱ ዕድሜ 300 ሺህ ዓመት እንደሚገመት ጥናቱን ያካሄዱት ተመራማሪዎች ገልጸዋል፡፡ የሞሮኮው ቅሪተ አካል በኢትዮጵያ የተገኙ “ሆሞሳፒያንስ” በተባለው ቤተሰብ የሚካተቱ ቅሪተ አካላትን በ100 ሺህ ዓመት እንደሚበልጥ ተነግሯል፡፡

https://p.dw.com/p/2eioA
Max Planck Institut - Homo sapiens älter als gedacht
ምስል picture-alliance/MPI EVA Leipzig/Shannon McPherron

ሞሮኮ የተገኘዉ ቅሬተ-አፅም

በደቡብ ምዕራብ ሞሮኮ የምትገኛዋ ማራካሽ ከተማ በበርካታ አውሮፓውያን ተመራጭ የመዝናኛ ስፍራ ናት፡፡ ከብዙ የአውሮፓ ከተሞች በሁለት እና ሦስት ሰዓት የአውሮፓላን በረራ ርቀት ላይ መገኟቷም ተደራሽነቷን አስፍቶታል፡፡ ከሰሞኑ ግን በአውሮፓውያን እና በዓለም መገናኛ ብዙሃን ዘንድ ስሟ ሲነሳ የከረመው እጅ በሚያስቆረጥመው ምግቧ አሊያም በተወዳጅ የእድ ጥበብ ውጤቶቿ አልነበረም፡፡ ይልቅስ ከከተማይቱ በስተምስራቅ ዘጠና ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ ካለ የቅድመ ሰው ጥናት ታሪክ የምርምር ቦታ ጋር በተያያዘ ነበር፡፡

የምርምር ቦታው ጀበል ኢራሃድ ይሰኛል፡፡ ሀረሩማ እና ድንጋያማ ስፍራ ነው፡፡ ከጥቂት ቁጥቋጦዎች በስተቀር የዛፍ ዘር የሚባል ነገር አይታይበትም፡፡ በዚህ ጭር ባለ ቦታ ገሚስ አካላቸው የተቦደሰ ኮረብታዎች ስር ተቀምጠው የተከመሩ አፈሮች እና ድንጋዮችን በጥንቃቄ የሚመረምሩ ሰዎች ማየት እንግዳ አይደለም፡፡ ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ ግንቦት 30 ይፋ በተደረገ ግኝት በዚያ ቦታ አሁን በምድር ላይ የሚመመላሰውን ሰው የሚመስል ፍጡር ከ300 ሺህ ዓመት በፊት ይኖር ነበር፡፡ 

Max Planck Institut - Homo sapiens älter als gedacht
ምስል picture-alliance/MPI EVA Leipzig/Philipp Gunz

ግኝቱን በፈረንሳይ ፓሪስ በተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ ለዓለም የናኙት ዤን ዣኩዊ ሁብሊዎ ናቸው፡፡ በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ሰፊ ሽፋን ያገኘው የሁብሊዎ ግኝት ሁለት አዲስ ነገሮችን ይዞ መጥቷል፡፡ አንደኛው ለዘመናዊው ሰው ቅርብ ናቸው የሚባሉትን እና በኢትዮጵያ የተገኙትን ቅሪተ አካላት በ100 ሺህ ዓመት ያስከነዳ ነው መባሉ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የተገኘበት ቦታ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ቅሪተ አካላት በብዛት የተገኙበት እና የሰው ልጅ መነሻ ነው የሚባለው ምስራቅ አፍሪካ ሲሆን ይሄ ግኝት ግን ስፍራውን እስከ ሰሜን አፍሪካ ድረስ ይለጥጠዋል፡፡

“የእኛ ግኝት የመማሪያ መጽሐፍትን ይቀይራልን? አዎ፡፡ አሁን ዘመናዊ ሰው እያልን የምንጠራው መነሻ አካባቢ ከሰሃራ በታች ባለ የሆነ ቦታ እንደሆነ ይታሰብ ነበር፡፡ ያ በእርግጥም እንደገና መታየት አለበት” ይላሉ ፈረንሳዊው ሁብሊዎ፡፡   

ሁብሊዎ የሆነ ቦታ ይበሉት እንጂ በዘርፉ ባለሙያዎች ዘንድ ከመስማማት የተደረሰባቸው፣ ለዘመኑ ሰው የቀረቡ ቅሪተ አካላት የተገኙት በኢትዮጵያ ነው፡፡ የመጀመሪያዎቹ በጎርጎሮሳዊው 1968 ዓ.ም በኦሞ ሸለቆ በቀድሞው ኩራዝ ወረዳ ኪቢሽ በተባለ ቦታ የተገኙት ናቸው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ በጎርጎሮሳዊው 1997 በአፋር ክልል ከገዋኔ ከተማ በስተምዕራብ በኩል ያርዲ ከተባለ ሀይቅ አጠገብ ነው፡፡ 

“ኢዳልቱ” የሚል መጠሪያ የተሰጠውን የአፋሩን ቅሪተ አካል 160 ሺህ ዓመት ዕድሜ እንዳለው ባለሙያዎች በጥናት ደርሰውበታል፡፡ የኦሞዎቹ መጀመሪያ ላይ ሲገኙ የዕድሜ መለኪያ ዘዴዎቹ እምብዛም ያልዳበሩ ስለነበሩ 100 ሺህ ዓመት ገደማ ተገምተው ነበር፡፡ ከዓመታት በፊት በስፍራው ላይ ተጨማሪ ምርምር በማድረግ አዳዲስ ቅሪተ አካላት ያገኙ ባለሙያዎች ግን ዕድሜያቸውን 195 ሺህ ዓመት እንደሚደርስ አረጋግጠዋል፡፡ የሞሮኮው ግኝት ይገዳደራቸዋል የተባለው ከእነዚህ ሁለት ቦታዎች የተገኙትን ቅሬተ አካላት እንደሆነ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

ወደ ሞሮኮ ልውሰዳችሁ፡፡ በሀገሪቱ ብሔራዊ የቅርስ እና ጥንታዊ ይዞታ ተቋም ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ሞኸሲን ጄራዊ ስለ ቀደምት ግኝቶች ሲያጣቅሱ ጭራሹኑ አፍሪካን አንኳ አይጠቅሱም፡፡ “ዛሬ ይህን ማለት እንችላለን፡፡ ረጅም ዕድሜ ያለው የሆሞሳፕያንስ ዝርያ የሚገኘው በሞሮኮ ጀበል ኢውድ ነው፡፡ በሌሎች የዓለም ክፍሎች የሆሞ ሳፕያንስ ዝርያዎች እንደተገኙ እናውቃለን፡፡ በአውሮፓ የተገኘው ኒያንደርታል ሳፒያንስ ከእኛው ጋር በሰውነት አሰራር ረገድ የተለየ ነው፡፡ ረጅም ዕድሜ አለው የሚባለው የኒያንደርታል ሳፒያንሱ አርባ ሺህ ዓመት ገደማ ወደ ኋላ የሚመለስ ነው፡፡ የአሁኑ ግኝት ግን 260 ሺህ ዓመት ልዩነት በመያዝ በዓለም ባለረጅሙ ዕድሜ ነው” ይላሉ ሞኸሲን ጄራዊ፡፡

Experten vom Middle Awash Research-Team bei Ausgrabungen in Afar Äthiopien
ምስል DW/A. T. Hahn

ላለፉት 36 ዓመታት በቅድመ ሰው ጥናት ዘርፍ  ምርምር ሲያደርጉ የቆዩት ዶ/ር ብርሃኔ አስፋው የሞሮኮውን የግኝት ውጤት አንብበዋል፡፡ በጀበል ኢራሃድ  ከ1960ዎቹ ጀምሮ በቅርብ እስከተገኙ ቅሪተ አካላት ድረስ ለረጅም ጊዜ ጥናት አካሄደዋል፡፡ የሞሮኮው ቅሪተ አካል “ረጅም ዕድሜ እንዳለው ተረጋግጧል” የሚባለውን ግን አይቀበሉትም፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ ተመራማሪዎቹ የተጠቀሙበት የቅሪተ አካል የዕድሜ መለኪያ ዘዴ ነው፡፡

“ከኢትዮጵያ የተገኙት ቅሪተ አካላት ዕድሜያቸው የተለካው ምንም ዓይነት ጥርጣሬ በሌለበት አርገን አርገን በሚባል ዘዴ ነው፡፡ ከእሳተ ጎሞራ እሳት ወለድ ብናኞች በወጡ ማዕድኖች ምንም ጥርጥር በሌለበት መንገድ ነው ያ ዕድሜ የተለካው፡፡ ይሄኛው ግን እነርሱ አሁን ሪፖርት ያደረጉት ዕድሜ የተለካው ቴርሞልሚኔነሰንስ (thremoluminesence) በተባለ ዘዴ ነው፡፡ ይህ የዕድሜ መለኪያ ዘዴ እስካሁን ድረስ በእኛ የጥናት መስክ ምንም ዓይነት ተዓማኒነት የሌለው የዕድሜ መለኪያ ዘዴ ነው” ሲሉ ዶ/ር ብርሃኔ በኢትዮጵያ ጥቅም ላይ የዋለውን ዘዴ በማነጻጸሪያነት በማቅረብ ያብራራሉ፡፡     

በኢትዮጵያ ቅሪተ አካላት የተገኙባቸው መካነ ቅርሶች በሙሉ በስምጥ ሸለቆ ውስጥ መገኘታቸው ሀገሪቱ የመጀመሪያውን የዕድሜ መለኪያ ዘዴ ያለምንም ችግር እንድትጠቀም እንዳስቻላት ዶ/ር ብርሃኔ ያስረዳሉ፡፡ እነዚህ ቦታዎች እሳት ጎሞራ የፈነዱባቸው በመሆናቸው ለዕድሜ መለኪያነት የሚያገለግሉ ማዕድናትም በቦታዎቹ በቀላሉ ይገኛሉ፡፡ ጊዜ ጠብቀው ወደ ሌላ ማዕድን ከሚቀየሩ እና “ራድዮአክቲቭ” በመባል ከሚታወቁት ከእነዚህ ማዕድናት ውስጥ ፖታሽየምን በምሳሌነት ያነሳሉ፡፡ ፖታሺየም አርገን ወደተባለ ማዕድን የሚቀየርበት የጊዜ መጠን ስለሚታወቅ ያንን በመለካት አስተማማኝ በሆነ መንገድ የቅሪተ አካላቱን ዕድሜ ማወቅ እንደሚቻል ያብራራሉ፡፡

እንደ ሞሮኮ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ቻድ ባሉ ሀገራት ግን ቅሪተ አካላት ቢገኙም የእሳት ጎሞራ ማዕድናት አብረዋቸው ስለሌሉ ሌላኛውን የዕድሜ መለኪያ ዘዴ መጠቀም ግድ እንዳላቸው ዶ/ር ብርሃኔ ይገልጻሉ፡፡ በሞሮኮ ብሔራዊ የቅርስ እና ጥንታዊ ይዞታ ተቋም የዳይሬክተሩ ረዳት የሆኑት አብዱሰላም ሜክዳድ በጀበል ኢራሃድ የተገኘ በእሳት የተቃጠለ የራስ ቅልን ዕድሜ ለመለካት የተጠቀሙበት ቴርሞልሚኔነሰንስ የተባለውን ሳይንሳዊ ዘዴ እንደሆነ አረጋግጠዋል፡፡ በዚህ ዘዴ ዕድሜ የሚለካው እንዴት ነው? ለምንስ “ተዓማኒነቱ ዝቅተኛ ነው” ተባለ?

“ቴርሞልሚኔነሰንስ የሚባለው ከውስጥ ያሉትን ማዕድናት በማየት፣ እነዚያ ማዕድናት የሚለቁትን ጨረር በመለካት ዕድሜውን ለማወቅ ይሞከራል፡፡ ያ ግን የሚሰጠው ዕድሜ በጣም ሰፊ ልዩነት የሚያመጣ ስለሆነ በተለያየ ቦታ በአውሮፓም ጭምር ተሞክሮ በጣም አስቸጋሪ ሆኗል፡፡ እሳት ጎሞራ ብናኞቹ አስተማማኝ የሆነ ዕድሜ መስጠት ስለማይችሉ ሌላ አማራጭ ተጨማሪ ሁለት፣ ሶስት ዕድሜ መለኪያ ዘዴዎች ስንጠቀም ቢያንስ በዚያ መሀከል ሊሆን ይችላል እና ሊቀራረብ ይችላል ይባል ነበር፡፡ እነዚህ ሰዎች ግን ሰፊ የዕድሜ መለኪያ ችግር ያለበትን ተጠቅመው ነው ያቀረቡት” ሲሉ ዶ/ር ብርሃኔ ይመልሳሉ፡፡

የሞሮኮው ግኝት በጋዜጣዊ መግለጫ መልክ ብቻ አይደለም ይፋ የተደረገው፡፡ ይልቁንስ በሳይንሱ ዓለም እንደተለመደው እንደ “ኔቸር” ባሉ የተከበረ ስም ባላቸው የሳይንስ ጆርናሎች ላይ ታትሟል፡፡ የዕድሜ አለካኩ ዘዴ ችግር አለበት ከተባለ ታዲያ እንዴት በ“ኔቸር” ላይ ታተመ? ዶ/ር ብርሃኔ ምላሽ አላቸው፡፡ 

Äthiopien Knochenfund Fossil Australopithecus deyiremeda
ምስል Yohannes Haile-Selassie/Cleveland Museum of Natural History/Handout via Reuters

“እንግዲህ በእኛ የጥናት መስክ ላይ አንዳንዴ የሚያስችግረው ነገር ምንድነው? ‘ዕድሜው በጣም ትልቅ የሆነ ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ የሆነ’ ዓይነት ቅጽሎች መጨመር የተለያዩ የዜና አውታሮችን የሚስብ ቃል ሆኖ ስለሚገኝ ብዙ ጊዜ እንዲህ አይነት ነገሮች ይደረጋል፡፡ እርግጥ እንደመላምት ልንጠቀምበት እንችላለን፡፡ እንደሳይንስ ግን ይሄኛው ነገር ሚዛን የሚደፋ አይደለም፡፡ እኔ ራሴ በግሌ ሳየው በጣም ወዳጅ የሆኑ ገምጋሚዎች (friendly reviewers) ያገኙት ጽሁፍ ይመስለኛል፡፡ ያንን አልፎ ለህትመት ሊበቃ የሚችል ማስረጃ ሊሆን አይችልም የሚል ግምገማ ነው ያለኝ” ይላሉ፡፡

አዲሱን ግኝት የሰሙ ኢትዮጵያ በእነ ሉሲ፣ ሰላም፣ አርዲ፣ ኢዳልቱ እና ሌሎችም ቅሪተ አካላት የተጎናጸፈችውን የ“ሰው ዘር መገኛ” የሚል ስያሜ በሞሮኮ እንደተነጠቀች እንዲያስቡ አድርጓቸዋል፡፡ ዶ/ር ብርሃኔ “እውነታው ሌላ ነው” ባይ ናቸው፡፡ 

“ከጀበል ኢራሃድ የተገኘው አዲሱ መረጃ የእነሉሲን እና የእነአርዲን የኢትዮጵያ ቀደምት የሰው ዘሮች የሚተካ አይደለም፡፡ የመጨረሻው የሰው ዘር፣ አሁን ያለው፣ ዓለምን በሙሉ የሞላው የሰው ዘር እስካሁን ባለን መረጃ ኢትዮጵያ ብቻ ነች የነበረችው፡፡ በዓለም የሚታወቀው ከፍተኛ ዕድሜ ያለው 200 ሺህ ነበረ፡፡ ያም ከኢትዮጵያ ብቻ ነበረ፡፡  ውድድሩ ያለው በዚያ ላይ ነው፡፡ እነርሱ የሚሉት ‘አይ! ኢትዮጵያ ብቻ አይደለም፡፡ እንዲያውም ከኢትዮጵያ በ100 ሺህ ዓመት የሚቀድም ሞሮኮ ላይ ተገኝቷል ስለዚህ የኤደን ምድረ ገነት የሚለው አንድ ቦታ ላይ ብቻ አይደለም ’ ነው፡፡ ሊሆን ይችላል፡፡ ትክክልም ሊሆን ይችላል፡፡ አሁን የምንከራከረው እስከ 200 ሺህ ዓመት ድረስ ነው፡፡ ግን ከዚያም አልፎ እስከ ከስድስት ሚሊዮን ዓመት ድረስ በዓለም ላይ የተገኘባት ሀገር ብትኖር ኢትዮጵያ ብቻ ነች፡፡”

ዶ/ር ብርሃኔ ሲያጠቃልሉ ነገሩን አህጉራዊ መልክ ሊሰጡት የሞክራሉ፡፡ “ቅሪተ አካሉ ከኢትዮጵያም ተገኘ ከሞሮኮ፤ አፍሪካ በአጠቃላይ የሰው ዘር መነሻ እንደሆነች ምንም ጥርጥር የለውም” ሲሉ በልበ ሙሉነት ይናገራሉ፡፡        

 

ተስፋለም ወልደየስ

አዜብ ታደሰ