1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

Merga Yonas Bula
ሐሙስ፣ ግንቦት 3 2009

«የሞተ አህያ ጅብ አይፈራም» የተሰኘ አባባል በኢትዮጵያ ይዘወተራል። «የሞቱ አህዮች ጅብ አይፈሩም» የሚል ርዕስን የያዘዉ አጭር ዘጋቢ ፊልም በዩናይትድ ስቴትስ ስታይ ቆይቶ ፤ አሁን እዚህ ጀርመን በሙኒክ ከተማ ዶክፌስት በተሰኘዉ የፊልም ፌስትቫል ላይ  እየታየ ይገኛል።

https://p.dw.com/p/2cp20
Dokumentarfilm Äthiopien
ምስል Joakim Demmer

«የሞተ አህያ ጅብ አይፈራም»

የፊልሙ ዳይሬክተር ጆኣሂም ድመር በፊስቲቫሉ ላይ ለእይታ ያቀረበዉ ይህ ፊልም የኢትዮጵያ መንግስት በሚልዮን ሄክታር የሚቆጠር የእርሻ መሬትን፣ ወይም በሱ አጠራር «አረንጓዴ ወርቅ»ን በክራይ ለባለኃብቶች እያደለ መሰንበቱንና ከጥቅሙ ይልቅ ለማኅበረሰቡ የ «ግፍና የመከራ» ጥንስስ መሆኑን የሚያሳይ ነዉ ይላል።

ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ እድገቷ «የአፍሪርቃ አንበሳ» ተብላ ስትጠራ ከግዜ ወደ ግዜ ይሰማል። ከአምስት ዓመት በፊት የኢትዮጵያ መንግስት በግብርና መስክ መዋለ-ኑዋያቸዉን ማፍሰስ ለሚፈልጉ ባለኃብቶች ወደ 3.6 ሚሊዮን ሄክታር መሬት አዘጋጅቶ እንደነበረ  ሮይቴርስ የተባለዉ የብሪታንያ የዜና ወኪል ዘገባ ያመልክታል። በዘገባዉም መንግስት በአንድ ሄክታር ከ1,15 ዶላር እስከ 12,8 ዶላር እያከራየ እስከ 50 ዓመት ለመዝለቅ እቅድ መያዙን ይጠቅሳል።

Dokumentarfilm Äthiopien
ምስል Joakim Demmer

ይህንንም ተከትሎ ሁለት አንጋፋ ኩባንያዎች፣ ማለትም ሳዉድ ስታርና ካራቱር ግሎባል  የተሰኙት የመሬቱን የአንበሳ ድርሻ መዉሰዳቸዉን ሌሎች ዘገባዎች አክሎበታል። ፋይናንሻል ታይመስ የተሰኘዉ የብሪታንያ ጋዜጣ የኢትዮጵያ መንግስት ለሳዉድ እስታር 2.5 ሚሊዮን ሄክታር መስጠቱን ያመለክታል። ካራቱሪ ግሎባል የተባለዉም መጀመርያ 300,000 ሄክታርን ቢወስድም ሙሉዉን ሊያለማ ስላልቻለ ወደ 100,000 ሄክታር እንደተቀነሰበት ጋዜጣዉ ያመለክታል።

«ኢትዮጵያ በፍጥነት እያደጉ ካሉ የአፍሪቃ አጋሮች አንዷ ነች፣ ምንም እንኳን ባለ ብዙ ዘርፍ እድገቷ ቢጠቀስም፣ የፋይናንስ ዘርፉ ግን…» ይልና ተመልካቾችን በጉጉት ቀልባቸዉን ለመያዝ ሲል የፊልሙ ማስታወቅያ (Trailer) ሦስት ነጥብ አድርጎ  ይቀጥላል።

ሳዉድ ስታርና ካራቱርን ጨምሮ ብዙ ቁጥር ያለቸዉ በለኃብቶች በተለያዩ የአገሪቱ  ክልሎች ኃብታቸዉን ቢያፈሱም በጋምቤላ ክልል ሰፊ የእርሻ መሬት እንደተሰጣቸዉም ዘገባዎች ያመለክታሉ። ከቤልጄም የቆዳ ስፋት ጋር የምትነፃጸረዉ ጋምቤላ ለም የሆነ የእርሻ አፈር ስላላት ከዉጭዎችም ሆነ ከአገር ዉስጥ የኢንቬስተሮችን ቀልብ መሳብ እንደቻለች የፋይናንሻል ታይምስ ዘገባ ይጠቅሳል።

ለእርሻ አመች ቦታዉ ላይ ሲኖሩ ለነበሩት ግን ጉዳዩ ሌላ ነበር። የጋምቤላ ክልል ነዋሪ አንድ አዛዉንትና ጎልማሳ ከሦስት ነጥቡ በኋላ እንዲ ሲሉ ይተርካሉ።
«ወታደሮቹ መሬታችንን እንድንለቅ አዘዙን፣ እምቢ ብትል ያጠቁሃል።»
«እዚህ ብሔራዊ መናፈሻ አለ። በእርሻ ላይ የተሰማሩ ወደ ጋምቤላ የሚመጡ ባለኃብቶች መሬት ይሰጣቸዋል የሚል ጭንቀት አለ።»

Dokumentarfilm Äthiopien
ምስል privat

የስዊድን ተወላጅ የሆነዉ የፊልሙ ዳይሬክተር፣ ጆአክም ደመር፣ ወደ ኢትዮጵያ ሲመላለስ በመሬት ላይ የሚካሄድ መዋለ-ንዋይ ምን ያህል ከእለት እለት «ህወታችን» ጋር መቆራኘቱን እንደታዘበ ይናገራል። ፊልሙን ለመስራት ያነሳሳዉም ብዙ የእርሻ መሬት ለዉጭ ባለኃብቶች ይከራያል ሲባል ሰምቼ ነዉ ይላል። «የሙዚቃ ዘጋቢ ፊልም ለመስራት ወደ ኢትዮጵያ መጥቼ ነበር። በግዜዉም በኢትዮጵያ ስላለዉ የመሬት ጉዳይ ብዙ ሰማሁ። እሱም ብዙና ሰፋፊ የእርሻ መሬት ለዉጭ ባለኃብቶች እንደተከራየ ነበር። በቦሌ አየር ማረፍያም በአገር ዉስጥ የሚመረቱ የግብርና ምርት ዉጤቶች እንዴት ወደ ዉጭ ገበያ እንደሚላኩና የዉጭ ርዳታ ደግሞ እንዴት ወደ አገር ዉስጥ እንደሚገቡ ተመለካከትኩ። በዉጭ ርዳታ ላይ ተንጠልጥላ ያለችዉ አገር ለዉጭ ገበያ ምግብ ስታቀርብ ግራ የሚያጋባ ሆኖ ስላገኘሁት ይህን ፕሮጄክት ጀመርኩ።»

ፊልሙን መስራት ስጀምር በኢትዮጵያ በመሬት መዋለ-ንዋይ ስም ምን ያህል ሰዎች እንደተጎዱና መሬታቸዉን ላጡት ደግሞ «ህመሙ» ምን ያህል እንደሆነ መረዳት እንደቻለ ጆአክም ይናገራል። «የሞቱ አህያዎች ጅብ አይፈሩም» የሚለዉ የፊልሙ ርዕስም ህመሙን ሊያሳይ ይችላል ተብሎ በዚህ ምክንያት መወሰዱንም ለዶይቼ ቬሌ ይናገራል።«ሲጀመር ያለህን ነገር ሁሉ ካጣህ፣ ከዚያ በኋላ ምንም የሚያስፈራህ ነገር አይኖርም። ይህ የፊልሙ ርዕስ  የብዙዎችን  ሰዎች  ስሜት የሚገልፅ ነዉ። ምክንያቱም በመሬት ቅርምቱ ሰበብ የብዙ ሰዎች ህይወት አዳጋች ሁኔታ ዉስጥ መግባቱን ስለምያዉቁ ነዉ። ለዛም ነዉ ፊልሙ ላይ ድምፃቸዉን ሳይደብቁ የሚናገሩት።»

ድንበር የማይገድበው የጋዜጠኞች ድርጅት፣ «ሪፖርተር ዊዝአውት ቦርደርስ» የፕሬስ ነጻነትን አስመልክቶ ኢትዮጵያን ከ 180 አገሮች 150ኛ ደረጃ ላይ አስቀምጦታል። በዘገባዉም ብዙ ጋዜጤኞች እስር ላይ እንደሚገኙና ሌሎች ደግሞ አገር ጥለዉ እንደሚሰደዱ  ይጠቅሳል።

በአገሪቱ የፕሬስ ነፃንት አሁንም ተገድቦ እንዳለና የዉጭም ሆነ የአገር ዉስጥ ጋዜጠኞች ሃሳባቸዉን ለመግለፅ መፈናፈኛ እንደሌላቸዉ ጆአክም ለዶይቼ ቬሌ ይናገራል። ፊልሙን መስራት የተቻለዉ ከካሜራ ጀርባ ከኢትዮጵያ ብዙ ሰዎች ራሳቸዉን ለአደጋ አጋልጠዉ  ስለተሳተፉበት ነዉ ሲልም ጆአክም አክሎሏል።

Dokumentarfilm Äthiopien
ምስል Joakim Demmer

በአሁኑ ጊዜ በዩናዮትድ ስቴትስ የሚኖረዉ ጋዜጠኛ አርጋዉ አሽኔ ከሰባት ዓመት በፊት  የመሬት ቅርምቱ ላይ ለመስራት መረጃ ማሰባሰብ በጀመረበት ግዜ ከጆአክም ጋር እንደተገናኘና ጆአክምም በጉዳዩ ላይ ፊልም መስራት መፈለጉን እንደነገረዉ ገልፆአል። ፊልሙ የሚቀረጽበት ቦታና ለፊልሙ ሃሳብ የሚሰጡትን ማገኘት ከባድ እንደነበረም ይናገራል።

በኢትዮጵያ በተለያዩ ክልሎች የመሬት «ቅርምት» ቢፈፀምም ፊልሙን ለመስራት በጋምቤላ ክልል ላይ እንዳቶኮሩ ጆአክም ይናገራል። ምክንያቱም በጋምቤላ ክልል ሰፊ የእርሻ መሬት ስለተከራየና የመሬት «ቅርምቱን» በነዋሪዎቹ ላይ አስከፊ ጉዳት  ስለነበረ ነዉ ይላል። «…በዛ ክልል ላይ አተኮርን። ፊልሙን ሰርቶ ለመጨረስ ሰባት ዓመት ነዉ ይወሰደብን። ምክንያቱም የመሬት ቅርምቱ በረጅም ግዜ ዉስጥ የሚያመጣዉን ጉዳት ማየት ስለፈለገን ነዉ። ስለዚህ መሬቱን ለእርሻ ከማዘጋጀት ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ያለዉን ተከታተልን ማለት ነዉ።»

ከሰባት ዓመት በፊት የኢትዮጵያ መንግስት በጋምቤላ፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ በሶማልያና በአፋር ክልሎች ተነጣጥሎ የሚኖረዉን ማኅበረሰብ አንድ ላይ አምጥቶ መሰረታዊ አገልግሎት እንድያገን ለማድረግ የመንደር ምስረታ ወይም «villagization» ፕሮግራም ቀርፆ እንደነበር ዘገባዎች ያመለክታሉ። በ2006 ዓ.ም፣ ዘ ጋርድያን የተሰኘዉ የብርትንያ ጋዜጣ፣ የቀድሞዉን የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ኦሞድ ኦባንግ ኦሉምን ጠቅሶ መንግስት ይላል ጆአክም ከ45,000 አባወራዎችን በመንደር ምስረታ ፕሮግራም እንደየዛና ከዝያም ዉስጥ 35,000 የሚሆኑት አባዋራዎች በፍላጎታቸዉ ከቦታቸዉ እንደተነሱ ጠቅሷል።

ከዓለም ባንክ የገንዘብ ድጋፍ ያገኘዉ ይህ ፕሮግራም መሰረታዊ አገልግሎት ለመስጠት ነዉ የሚለዉን አለማ እንደሳታ ተችዎች ይጠቁማሉ። መቀመጫዉን ንዉዮርክ ያደረገዉ ዓለም አቀፉ የሰባዊ መብት ተከራካሪ ድርጅት «Human Rights Watch» በመንደር ምሰራታ ወይም «villagization» ስም መሬቱን ለባለኃብቶች ለመስጠት ሲባል በጋምቤላ ክልል በሽዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከቄዬያቸዉ እንደተፈናቀሉ ይጦቁማል። የመንግስትን ትዕዛዝ ያልተቀበሉም እንደተገደሉ፣ ሌሎች እንደታሰሩ፣ ቀሪዎቹ ደግሞ ቀዬያቸዉን ጥለዉ እንደኮበለሉም ያመለክታል።

Dokumentarfilm Äthiopien
ምስል Joakim Demmer

ፊልሙም በዚህ ፕሮግራም ተጓዳኝ ያሉትን እንዲ አድርጎ አቅርበዋል፣

«ዓለም ባንክ በቢልዮን የሚቆጠሩ የባጄት ይገዛ ለኢትዮጵያ መንግስት ሰተዋል--- 
«ወታደሮቹ መቶከስ ጀመሩ… አምስት ሰዉ እስኪሞት ድረስ።»
«መታሰርን አልፈራም፣ የስቃይ ቅጣትን ነዉ የምፈራዉ።»
«በኢትዮጵያ ህዝብን የዓለም ባንክ እየረዳ አይደለም፣ እየጎዳቸዉ ነዉ። በሰብዓዊ መብትና በሰብዓዊ ክብር ላይ ገንዘባችንን እናዉል።»

አገሪቷ በአምባገነን ስርዓት ስር ስለምትገኝ በግልፅ አንድ አይነት ዘጋዚ ፊልም መስራት በጣም አስቸጋሪ እንደነበረ የፊልሙ ዳይሬክቴር ጆአክም ዴሜር ለዶይቼ ቬሌ ይናገራል። «ስለዚህ በጣም መጠንቀቅ ነበረብን። አንድንድ ግዜ በጣም አደገኛ ሁኔታ ሁሉ ነበር፣ በተለይ ደግሞ ኢትዮጵያ ሆነ ፊልሙን ከእኔ ጋር ለሰሩት። ይሁን እንጅ ብዙዎቹ ይህን ከመሬት ቅርምት ጋር ተገናኝቶ የሚነሳን አስቸጋሪ ክስተት ለዓለም ለማሳወቅ ፍላጎት ስለነበራቸዉ አስፈላጊ ሆኖ አግኝተዉታል። ስለዚህም ከካሜራ ጀርባም ወይም ፊለፊት ሆነዉ ትልቅ አስተዋፆን አድርገዋል።»

ይህ ፊልሙን ለመስራት የገጠምን አንዱ ዉጣ ዉረድ የአገሪቱ የፖለትካ ችግር ቢሆንም ፊልሙን ለመስራት የገንዘብ እጥረት ሌላኛዉ ፈተና እንደነበረ ጆአክም ይናገራል። «ምክንያቱም ለስድስት ዓመት ፊልሙን ለመስራት ባጀት አልነበረኝም። ስለዚህ ለእኔም እንደ ፊልሙ ዳይሬከትር ሆነ ለፕሮዱክሸን ኩባንያዉ ከባድ ግዜ ነበር። ይሁን እንጅ ይህ ፊልም እቅዱ መደርደርያ ላይ እንዚቀመጥ ሳይሆን ተሰርቶ አልቆ ለእይታ እንዲበቃ  ጠንካራ ፍላጎት ስለነበረን ፊልሙን በገንዘብ የሚደግፍ ዘመቻ አካሄደን። ዉጤቱም መልካም ነበር።»
በኢትዮጵያ ያሉት ሰዎች «የጉዳዩ ባለቤት»ና «የችግሩ ተጠቂ» በመሆናቸዉ  ፊልሙ ትርጉም ይሰጣቸዋል የሚለዉ ጋዜጠኛ አርጋዉ አሽኔ፣ የዉጭ ተመልካቾች ደግሞ ፊልሙን ግንዛቤ እንዲያገኙ ያደርጋቸዋል ይላል።

ጆአክም የዘጋቢ ፍልም ለመስራት ዋና አለማዉ «story tellingp» ወይም በመሬት ቅርምቱ ላይ ያለዉን ጉዳይ ለመተረክና ያለዉን ችግር ይፋ ማድርግ ነዉ ይላል። በኢትዮጵያም 1,5 ሚሊዮን ሰዉ በዚህ መሬት ቅርምት ከቦታቻዉ ተፈንቅለዉ ለማዋዕለ ንዋይ አፍሳሾች  ቦታ እንዲሰጡ ተደርገዋል ይላል። «በጣም አስፈላግዉ ነገር፣ የዚህ ፊልም ዓላማ ድምፅ ለሌላቸዉ ድምፅ ለመስጠት ነዉ። እናም በዚህ ፊልም ዉስጥ የምንሰማቸዉ ቃሎች የአዉሮጳ ኅብረት ወይም የዓለም ባንክ ፖሊስ የዉጭዎች ጆሮ እንደምገባ ተስፋ እናደርጋልን።

መርጋ ዮናስ

አዜብ ታደሰ