1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሳውዲ ተመላሾች / አየር መንገድ እሰጣ እገባ

ማክሰኞ፣ ሰኔ 20 2009

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሪያድ ሳውዲ ዓረቢያ የመንገደኞች ማጓጓዣ ህንጻ ለአራት እና አምስት ቀናት ሲንገላቱ የቆዩትን በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵዊያን የሳዑዲ ተመላሾችን ማጓጓዝ ጀመረ፡፡ አየር መንገዱ በተርሚናሉ ውስጥ ለቀናት የሰነበቱትን ደንበኞቹን እንዲያነሳ ስለተገደደ ሌሎች መደበኛ በረራዎችን ሰርዞ ትኩረቱን ተርሚናል ወዳሉት አዙሯል፡፡ 

https://p.dw.com/p/2fUQM
Rückkehrer Äthiopien Saudi Arabien Riad
ምስል DW/S.Sibiru

Ber. Riyadh(Eth-Airline Flugzeuge zugeteilt für gestrandete Rück_rn in Riyadh ) - MP3-Stereo


የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሪያድ ሳውዲ ዓረቢያ የመንገደኞች ማጓጓዣ ህንጻ ለአራት እና አምስት ቀናት ሲንገላቱ የቆዩትን በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵዊያን የሳዑዲ ተመላሾችን  ማጓጓዝ ጀመረ፡፡ አየር መንገዱ ከሳዑዲ ሲቪል አቪየሽን መስሪያ ቤት ከተርሚናሉ ውስጥ ለቀናት የሰነበቱትን ደንበኞቹን እንዲያነሳ ስለተገደደ ሌሎች መደበኛ በረራዎችን ሰርዞ ተርሚናል ውስጥ ወደነበሩት  ትኩረቱን አዙሯል፡፡ 
በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ትምህርት ቤት ቅጥር እና በየቦታው ለመዋልም ሆነ ለማደር ተገደው የነበሩ ከ300 መቶ በላይ ትኬት የቆረጡ ተመላሽ  ኢትዮጵያዊያን እነርሱ እንደሚሉት በጉልበታቸው አየር መንገዱ አስገድደው አንድ ላምስትም ቢሆን ሆቴል ይዞላቸዋል፡፡
በሪያድ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ማህበር ሊቀመንበር አቶ ሻወል ጌታሁን በበኩላቸው በሳዑዲ መንግስት ህገ ወጥ የተባሉ ዜጎችን ወደ ሀገር የማስመለስ መርሀ ግብሩ ገና ይመጣሉ የሚባሉት ትላልቅ ፈተናዎች ሳይመጡ ትናንሽ ፈተናዎችን እንኳን ባግባቡ ማለፍ ያልተቻለበት እንደሆነ ይገልጻሉ ፡፡
እንኳንስ ውሎ ለማደር ይቅር እና የጉዞ ሰዓት እስኪደርስ እንኳን ደቂቃዎች የሰዓት ያህል በሚረዝሙበት የአየር መንገድ የመንገደኞች ማስተናገጃ ስፍራ ለ ሶስት እና አራት ቀንና ለሊት መቆየት የተለመደ አይደለም፡፡ ሳዑዲ ዓረቢያ ሀገርን ከህገወጦች የማንጻት ባለችው ዘመቻ ቀነ ገደቡ ሳያልቅ ሀገራቸው ለመግባት የጉዞ ሰነድ አሟልተው፤  የመጓጓዣ ትኬት የቆረጡ ኢትዮጵያዊያን ወንዶች ሴቶች እና ህጻናት በሳዑዲ ዓረቢያ 3ተኛው ማስተናገጃ  ህንጻ ለሶስት እና አራት ቀናት በተጨናነቀ መልኩ ከርመዋል፡፡
ከነበሩበት ቦታ እና የስራ ጫና የተነሳ ድምጻቸውን መቅረጽ ባልችልም የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሪያድ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሁሴን እንደሚሉት የሳዑዲ አረቢያ ሲቪል አቪየሽን መስሪያቤት በተርሚናሉ የዋሉና ያደሩ ደንበኞቹን እንዲያነሳ ማስጠንቀቂያ አዘል መልዕክት አስተላልፎላቸዋል፡፡  በዚህም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዘግይቶም ቢሆን 400 ያህል ሰዎችን ባንዴ ማጓጓዝ የሚችለውን በይንግ 777 አይሮፕላን መድቦ መንገደኞቹን በማጓጓዝ ላይ ይገኛል፡፡ ከዚህም በላይ በደንበኝነት ሰነድ ውሉ ላይ የተቀመጠውን ግዴታ ሳያሟላ ማደሪያ ነፍጎ በየቦታው በትኗቸው የነበሩ 331 ተመላሽ ዜጎችን ትላንት በጋራ በማድረግ የሆቴል አልጋ ተከራይቶላቸዋል፡፡
ሆቴል ያገኙት ኢትዮጵያዊያን ተመላሾች ግን ሆቴሉ ቀርቶብን አየር መንገዱ በጊዜ ወደ ሀገራችን ይሸኘን ባይ ናቸው ፡፡
አየር መንገዱ በጊዜው ማጓጓዝ ያልቻላቸውን መንገደኞች ከፊሎቹ በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ትምህርት ቤት ቅጽር ሌሎቹም በሳዑዲ አየር ማረፊያ የመስተንግዶ ህንጻ እንዳሉ ለሁለት እና ሶስት ቀናት መደበኛ በረራውን በቀጠለበት ሁኔታ ነበር የሳዑዲ መንግስት ለመደበኛ በረራ ወደ አየር መንገድ የሚሄዱ ኢትዮጵያዊያንን ፍተሻ ኬላ ላይ እየጠበቀ መመለስ የጀመረው፡፡ በዚህም የተነሳ  ለትላንት በረራ ጊዜ ተሰጥቷቸው የነበሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ መንገደኞች ከፍተሸ ኬላው ማለፍ ባለመቻላቸው ማደሪያቸውን በሪያድ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ አዳራሽ አድርገዋል፡፡ ይህም አየር መንገዱን መደበኛ በረራውን አስተጓጉሎ አለኝ የሚለውን ሀይሉን ለቀናት ወደ ተከማቹት መንገደኞች እንዲያዞር አድርጎታል፡፡ ያም ሆኖ ውስን በሆኑ አስተኛጋጆች የሚከናወነው የትኬት ማመሳከር እና የጭነት ማመዛዘን ተግባር ቦይንግ 777 ትን ለሰዓታት ቆሞ እንዲጠብቅ አስገድዶታል፡፡ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ ባይከናወንም የሪያድ የአየር መንገድ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሁሴንም ሆኑ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ምንጮች እንደሚሉት ዛሬ ትኬት የያዙትን በሙሉ ለማጓጓዝ ታቅዷል፡፡ 
ዜጎችን ወደ ሀገር የማስመለሱ ተግባር በዋናነት የአራት ዋነኛ ፈጻሚዎች ሚና ነው ፡፡አቶ ሻወል ጌታሁን የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ማህበር እነዚህን አራት አካላት ሲያብራሩ ተመላሾቹ ራሳቸው ፤ የመውጫ ሰነድ የሚያዘጋጁት የኢትዮጵያ እና የሳዑዲ መንግስት አካላት በሁለተኛነት እና በሶስተኛነት ብሎም በአራተኛን እና በዋና አጓጓዥነት የኢትዮጵያ አየር መንገድን ያስቀምጧቸዋል፡፡ ከእነዚህ አራት አካላት አንድኛው ጋ መጓተት ወይንም መደናቀፍ ካለ አጠቃላይ ሂደቱ ላይ አሉታዊ ሚና ይኖረዋል የሆነውም ያ ነው አቶ ሻወል፡፡
አሁን ባለው ሁኔታ የኮሚኒቲ ማህበሩ ሊቀመንበር አቶ ሻወል እንደሚሉት ትኬት በእጁ ያለውም ሀገር መግባት አልቻለም ትኬት የሚፈልገውም ትኬት ማግኘት አልቻለም፡፡
የውጡልኝ የምህረት ጊዜው ቢያበቃም በሳዑዲ መንግስት ዘንድ እስካሁን ድረስ ካለፉት ሳምንታት  የተለየ የቃልም ሆነ የተግባር እንቅስቃሴ ቢያንስ በሪያድ እና አቅራቢያው አይስተዋልም ፡፡ 

Rückkehrer Äthiopien Saudi Arabien Riad
ምስል DW/S.Sibiru

ስለሺ ሽብሩ 


አዜብ ታደሰ
አርያም ተክሌ