1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሴራሊዮን አዳጊ ሴቶች ፈተና

ዓርብ፣ ሰኔ 1 2010

በሴራሊዮን 70 በመቶ የሚሆነው ህዝብ ህይወቱን የሚገፋው በቀን ከሁለት ዶላር ባነሰ ገቢ ነው። በሀገሪቱ የተንሰራፋው ድህነት ሴት ልጆችን ወደ ጎዳና እንዲወጡ ይገፋቸዋል። በአስራዎቹ ዕድሜ ክልል ያሉ ወጣት ሴቶች የትምህርት ቤት ክፍያቸውን ለመሸፈን በሴተኛ አዳሪነት እንዲሰማሩ አድርጓቸዋል። የ77 ከመቶው የተሰኘው ትኩረት ይኸው ነው።

https://p.dw.com/p/2z9eR
Sierra Leone Freetown Straßenszene
ምስል DW/O. Acland

የሴራሊዮን አዳጊ ሴቶች ፈተና

በሴራሊዮን መዲና ፍሪታውን ዘወትር አርብ ማታ ጎዳና አውቶብስ ይሽከረከራል። በየቦታውም እየቆመ ሴተኛ አዳሪዎችን ይጭናል። በአውቶብስ ፌርማታዎች የአውቶብሱን መምጣት የሚጠባበቁት ሴተኛ አዳሪዎች ገና ለአካለ መጠን እንኳ ያልደረሱ ናቸው። የአውቶብሱ አቅራቢ እነዚህን አዳጊ ሴቶች የተመለከተ መርኃ ግብር ነድፎ ላለፈው አንድ ዓመት እየተንቀሳቀሰ ያለው ዶን ቦስኮ የተሰኘው የካቶሊክ ግብረ ሰናይ ድርጅት ነው። አዳጊዎቹ ሴቶች ወደ አውቶብሱ እንደገቡ ምግብ፣ ለስላሳ መጠጦች እና የህክምና ምርመራ በነጻ እንደሚያገኙ ያውቃሉና ነው የሚያዘወትሩት። ፍራንሲስ የዶን ቦስኮው መርኃ ግብር መሪ ናቸው። 

“ዛሬ ከሰዓት ከከተማዋ ማዕከል ተነስተን በፍሪታውን ምስራቃዊ ጫፍ በሴተኛ አዳሪነት የሚተዳደሩ ሴት ልጆች እንሄዳለን። የሚፈልጓቸውን ነገሮች፣ የህክምና እና ሌሎችም ማህበራዊ ፍላጎታቾቻቸውን ማሟላታችንን ማረጋገጥ አለብን። እኛ የምንከተታተላቸው ሴት ልጆች ከ14 እስከ 19 ዓመት ያሉትን ነው” ይላሉ ፍራንሲስ።       

Symbolbild - Prostitution in Brasilien
ምስል Getty Images

አውቶብሱ ከሞላ በኋላ ሴቶቹን በከተማይቱ ዳርቻ ወዳለ ባዶ የገበያ ቦታ ይወስዳቸዋል። ጉዞው ጸሀይ ወደ ማደሪያዋ ስትከተት አካባቢ የሚደረግ ነው። በዶን ቦስኮ የማህበራዊ ጉዳዮች ሰራተኛ የሆኑት ፋትማታ ቢንቱ ከሴቶቹ ጋር ለምን እነዚህን መሰል ቆይታዎች እንደሚያደርጉ ያስረዳሉ።    

“ሴቶቹ አዝነው ይሆናል የሚመጡት። እነዚያን ተግባራት፣ የቀልድ ጨዋታዎች በምናከናውንበት ወቅት ደስተኞች እና ተጨዋቾች ይሆናሉ። አዝነው የሚመጡበት ምክንያት በጎዳናዎች ላይ ብዙ ተግዳሮቶች ስለሚገጥሟቸው ይሆናል። አንዳንዴ ወንዱ ከአነርሱ ጋር ይተኛ እና ሳይከፍላቸው ይቀራል። ያ ሰው ምናልባትም ይደበድባቸው እና የሰበሰቡትን ሁሉ ይዘርፋቸው ሁሉ ይሆናል። በእኛ መርኃ ግብር ምክንያት የተወሰኑት ይህን ስራ አቆመዋል። የተወሰኑት ግን አሁንም ይህንኑ ይሰራሉ” ይላሉ ቢንቱ።      

የዶን ቦስኮው ፍራንሲስ “ደስተኛ የሆነ ያጨብጭብ” የሚለውን የልጆች መዝሙር ከሴቶቹ ጋር አብረው እየዘፈኑ ነው። ቢንቱ ስለ መርኃ ግብሩ ማስረዳታቸውን ይቀጥላሉ። “የእነዚህ ቆይታዎቻችን ጊዜያዊ ግብ የእነርሱን መንፈስ ጥንካሬን መገንባት፣ በሚያስፈልግ ጊዜ የመጀመሪያ ደረጃ የህክምና እርዳታ መስጠት እና ለታመሙ ደግሞ ተጨማሪ ህክምናዎችን ማቅረብ ነው። ወደ ትላልቅ ሆስፒታሎች ሄደው እንዲታከሙ እናደርጋለን። የጤና ምርመራ እናደርጋለን። ለኤች አይ ቪ እና ጉበት በሽታ እንኳ በነርስ አማካይነት ፈጣን ምርመራ እንሰጣለን። ብዙዎቹ በሽታዎች አሉባቸው። ኮንዶም ጭምር እናቀርብላቸዋለን” ይላሉ ቢንቱ። 

በዚህ መርኃ ግብር ተሳታፊ ከሆኑት ውስጥ አንዷ አሚኒታ ነች። አሚኒታ እውነተኛ ስሟ አይደለም። ማንነቷን ለመደበቅ የተሰጣት ነው። አሚኒታ ጎዳና ዳር መቆም የጀመረችው ገና የ11 ዓመት ልጅ እያለች ነበር። በመርኃ ግብሩ መሳተፍ ከጀመረች ወዲህ ግን ሴተኛ አዳሪነቱን እርግፍ አድርጋ ትታለች። የዶን ቦስኮዋ ቢንቱ ለሌሎቹ ታዳጊዎች ስለ ጤና እና የግል ንጽህና እየነገረቻቸው ሳለ አሚኒታ በመንገድ ዳር ካለ አነስተኛ ግንብ ላይ ተቀምጣ ታሪኳን እንዲህ ስትል አውግታለች።  

“የመጣሁት ከካባላ ነው። በዚያ ከእናቴ ጋር እስከ ስድስት ዓመቴ ቆይቻለሁ። የእናቴ ጓደኛ አለች። ልጅ የላትም። ወደ እናቴ መጣችና ከእርሷ ጋር እኖር ዘንድ እንድትፈቅድልኝ እናቴን ጠየቀቻት። እናቴን ለመርዳት ብላ ነው። ከዚህች ሴትዮ ጋር እስከ 11 ዓመቴ ድረስ ቆይቻለሁ። ሴትዮዋ ገንዘብ የለኝም በማለቷ ወደ ትምህርት ቤት መሄድ አቆምኩ። እናም ቤት መዋል ጀመርኩ። ልብስ ማጠብ፣ ውሃ መቅዳት እና ሌሎችንም ስራዎች ስሰራ ቆየሁ። ከዚያ ለመጥፋት ወሰንኩ።  

መንገድ ላይ ሁለት ቀን አድሬያለሁ። ማማ አዪ የሚሏቸውን ሴትዩ ሳገኝ ስሜን ጠየቁኝ። ከዚያ ከእርሷ እና ከሌሎች ሴት ልጆች ጋር እንድኖር ጋበዘችኝ። መጀመሪያ ላይ ፈርቼ ነበር ግን እዚያው መቆየቴ አልቀረም። ሴቶቹ ብር ይዘው ሲመጡና ሲጎርሩ እመለከት ነበር። ያ እነርሱን እንድከትል አደረገኝ። ገንዘብ ለማግኘት እኔም ወደ ጎዳና ወጣሁ” ስትል ወደሴተኛ አዳሪነት የገፋትን ምክንያት ታስረዳለች።  

Tanzania commercial sex workers
ምስል Kizito Makoye

አሚናታ የመጀመሪያ ደንበኛዋ ስነ ርዓት አልባ እንደነበር ትናገራለች። ብዙ ማልቀሷንም ታስታውሳለች። ያኔ የተከፈላት 30 ሺህ የሀገሬው ገንዘብ ሊኦንስ አራት ዩሮ እንኳ አይሞላም። ይህ እንደውም የቀና ጊዜ ነው። አንዳንዴ ደንበኞች ከአሚኒታ ጋር የ30 ደቂቃ ቆይታ ለማድረግ የሚከፍሉት ገንዘብ ከአንድ ዩሮም ወርዶ በሳንቲም ደረጃ ብቻ ይሆናል። ለእንዲህ አይነት አጭር ቆይታዎች የሚከፍሉት አምስት ሺህ ሊዮንስ የዩሮ ምንዛሬው 53 ሳንቲም ብቻ ነው። ከዚህ ሁሉ የከፋው ደግሞ ኮንዶም የሚጠቀሙት ከስንት አንዴ መሆኑ ነው።

“አንዳንዴ እስከ 50 ሺህ ሊኦንስ ይከፍላሉ ነገር ግን እንደዚያ ሲከፍሉሽ ለሊቱን በሙሉ ከእነርሱ ጋር እንድታሳልፊ ይሻሉ። ያን ያህል እንዲከፍሉሽ ከፈለግሽ እንደ ፎጣ ትጨመቂያለሽ። አንቺን ከመልቀቃቸው በፊት ፎጣው መድረቁን አረጋግጠው ነው” ስትል ጄን እየተንገፈገፈች ትገልጻለች።   

የዶን ቦስኮ ግብረ ሰናይ ድርጅት አሚናታን ያገኛት እርሷ እና አብረዋት የሚኖሩ ሴቶች በሴተኛ አዳሪነት በሚሰሩበት ቡና ቤት በኩል ነው። አሚናታ አሁን 15 ዓመት ሞልቷታል። እንደ አሚናታ ሁሉ ስሟ የተቀየረው ጄን ከአዳጊ ሴቶቹ መካከል አንዷ ነች። ጄን አሁንም ደንበኛ ፍለጋ በመንገዶች ዳር ትቆማለች። ዶን ቦስኮ ለአዳጊ ሴቶች ባዘጋጀው መጠለያ ለጥቂት ጊዜ ያህል ቆይታለች። ሆኖም ገንዘብ ለማግኘት በሚል መጠለያውን ትታ ወደ ጎዳና ተመልሳለች። 

ጄን በዶን ቦስኮ መርኃ ግብር ከታቀፉ 100 አዳጊ ሴቶች ውስጥ ወደ ጎዳና ከተመለሱ 13 ወጣቶች መካከል አንዷ ናት። ከ15 ዓመቷ ጀምሮ በሴተኛ አዳሪነት የተሰማራችው ጄን አሁን አስራ ሰባተኛ ዓመቷን ይዛለች። ስለ ህይወቷ ተከታዩን ለዶይቼ ቬለዋ ዘጋቢ አጫውታታለች።

“ትክክለኛነት ተሰምቶኝ አያውቅም ምክንያቱም ይህ የእኔ ምኞት አልነበረም። ስለዚህ ጥሩ ስሜት አይሰማኝም። ይህን የጀመርኩበት ምክንያት ከአባቴ ጋር እኖር በነበረ ወቅት እንጀራ እናቴ ስለማትወደኝ ነበር። አባቴ ወደ ስራ ሲሄድ ቤት ውስጥ ትቆልፍብኛለች። እርሱ ከስራ መጥቶ በሩን እስኪከፍትልኝ ድረስ በዚያው እቆያለሁ። የትምህርት ቤት ክፍያን አይከፍሉልኝም ነበር። አባቴ እምብዛም ምግብ አይሰጠኝም ነበር። ያ ነው ወደ ጎዳና እንድወጣ ያደረገኝ” ትላለች ጄን። 

ጄን ወሲብ ያለ ኮንዶም ለመፈጸም ገንዘብ እንደምትቀበል ትናገራለች። “ወደ ጎዳና ስትወጪ ኮንዶም መጠቀም እንዳለባቸው ወይም እንደሌለባቸው ይጠይቁሻል። ኮንዶም የሚጠቀሙ ከሆነ ገንዘቡ ትንሽ ነው። ኮንዶም የማይጠቀሙ ከሆነ ይሻላል። ያለ ኮንዶም 80 ሺህ ሊኦንስ (8 ዩሮ ገደማ) ሲሆን በኮንዶም ግን 50 ሺህ ሊኦንስ (6 ዩሮ ገደማ) ይሆናል” ስትል በእሳት መጫወት የሆነውን የህይወቷን ክፍል ታስረዳለች። 

Symbolbild Prostitution
ምስል picture-alliance/maxppp

ጄን ብሩህ እና ለመሳቅም ቅርብ የሆነች ነች።  አጠር ያለ ጸጉር እና የሚያንጸባርቁ አይኖች አሏት። እንደ አሚናታ መሆን ትፈልጋለች። “ወደ ትምህርት ቤት መመለስ እፈልጋለሁ። የትምህርት ማጠናቀቂያ ፈተና ወስጄ ስራ ማግኘት እፈልጋለሁ። የሂሳብ ሰራተኛ ብሆን እወዳለሁ። እንግሊዝ ሀገርም መሄድ እመኛለሁ” ስትል ጄን በሳቅ ታጅባ ምኞቷን ታጋራለች።  

የምሽቱ ቆይታ እንደተጠናቀቀ አዳጊዎቹ ሴቶች ወደ አውቶብሳቸው ተመልሰው ቀድመው ወደተሳፈሩበት ቦታ ይበታተናሉ። የተወሰነቱ እስከ ንጋት ለመስራት ከመንገድ ዳር ይቆማሉ። እንደ አሚናታ ያሉቱ ደግሞ በሴተኛ አዳሪነት ከሚተዳደሩ ደርዘን አዳጊ ሴቶች ጋር ወደሚጋሩት ክፍል ተመልሰው ለሊቱን በወለል ተኝተው ያሳልፋሉ።

የዶን ቦስኮ ግብረ ሰናይ ድርጅት ጄንን እና አሚናታን ወደ ትምህርት ቤት ለመላክ እና እምነት ከሚጣልባቸው ዘመዶቻቸው ጋር መልሶ ለመቀላቀል አቅዷል። ጄን ከእናቷ ጋር ትኖርበት ወደነበረው የፍሪታውን ዳርቻ ለመመለስ ትልቅ ተግዳሮት ከፊቷ ተደቅኗል። የዚያ አካባቢ ነዋሪዎች ሴተኛ አዳሪ እንደሆነች ያውቃሉና ነው ችግሩ። ስራውን እንኳ ብታቆም ማግለሉ እንደው መቀጠሉ አይቀር። 

አሚናታም ሆነች ጄን በሴተኛ አዳሪነታቸው ምክንያት ለበሽታ ተጋልጠዋል። ጨብጥ እና ሄፓታይተስ በሽታዎች አለባቸው። የዶን ቦስኮ ግብረ ሰናይ ድርጅት ጄንን ከጎዳና እንድትርቅ ማድረግ ከቻለ እና ሁለቱንም በተቻለ መጠን ወደ ትምህርት ገበታ እንዲመለሱ ካደረገ የተሻለ የወደፊት ህይወት እንዲኖራቸው መንገዱን ጠረገላቸው ማለት ነው።  

ኦሊቪያ አክላንድ/ ተስፋለም ወልደየስ 

ሂሩት መለሰ