1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የበርሊን ምርጫ ውጤት እና አንድምታው

ማክሰኞ፣ መስከረም 10 2009

በዚህ ምርጫ የጀርመን ፌደራል ሪፐብሊክን ተጣምረው የሚመሩት ክርስቲያን ዴሞክራት ህብረት እና ሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲዎች ከቀደሙት ምርጫዎች ያነሰ ድምጽ ማግኘታቸው ብቻ ሳይሆን ፀረ የውጭ ዜጋ አቋም ያላቸው ቀኝ ጽንፈኞች በርካታ የምክር ቤት መቀመጫዎችን ማሸነፋቸው አስግቷል ።

https://p.dw.com/p/1K5ax
Deutschland Berlin Wahl SPD
ምስል picture-alliance/Pacific Press/S. Kuhlmey

የበርሊን ምርጫ ዉጤትና እድምታዉ

ሰሜን ምሥራቅ ጀርመን የምትገኘው የጀርመን ርዕሰ ከተማ በርሊን ትልቋ የጀርመን ከተማ ከመሆንዋም በላይ ከ16ቱ የጀርመን ፌደራል ክፍለ ግዛቶች ሃገራት እንዲሁም ከሦስቱ የጀርመን የከተማ ግዛቶች አንዷ ናት ። የመንግሥት እና የጀርመን ምክር ቤት መቀመጫ በርሊን ከ 3.5 ሚሊዮን በላይ ህዝብ መኖሪያ ነች ። ከአውሮጳ ከተሞች ደግሞ በህዝብ ብዛት ሰባተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች ። የባህል የፖለቲካ የመገናኛ ብዙሃን እና የሳይንስ ከተማ የምትባለው በርሊን የበርካታ ሃገር ጎብኚዎች መስህብም ናት ። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በፊት የጀርመን ርዕሰ ከተማ የነበረችው በርሊን ጀርመን ከተሸነፈችበት ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ምሥራቅ እና ምዕራብ ተብላ ተከፍላ ነበር ። ምሥራቅ እና ምዕራብ ጀርመን ከተዋሃዱ በኋላ በርሊን እንደገና የጀርመን ርዕሰ ከተማ ከሆነች 26 ዓመት ሊሞላት ነው ። ከውህደቱ በኋላ ከ 2001 እስከ 2011 በሶሻል ዲሞክራቶች እና በግራዎቹ ፓርቲ ነበር የምትተዳደረው ። ከ2011 ዱ ምርጫ በኋላ ግን ሶሻል ዴሞክራቶች እና የክርስቲያን ዴሞክራቶች ህብረት ፓርቲዎች ተጣምረው ሲመሯት ቆይተዋል ። ካለፈው እሁዱ ምርጫ ውጤት በኋላ ግን አብላጫ ድምጽ ያገኘው የሶሻል ዴሞክራቶቹ ፓርቲ ከተማይቱን ከየትኛው ወይም ከየትኛዎቹ ፓርቲዎች ጋር ተጣምሮ እንደሚመራት ገና አልለየለትም ። ባለፈው እሁድ በተካሄደው የበርሊን ከተማ ምክር ቤት ምርጫ ሶሻል ዴሞክራቶች 21.6 በመቶ ድምጽ አሸንፈዋል ይሁንና ውጤቱ ፓርቲው ከ5 ዓመት በፊት ካገኘው ድምፅ በ6.7 በመቶ ያነሰ ነበር ።ላለፉት 5 ዓመታት ከፓርቲው ጋር ተጣምሮ ከተማይቱን ያስተዳደረው የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል የሚመሩት የክርስቲያን ዴሞክራት ህብረት ፓርቲ በጀርመንኛው ምህጻር CDU ደግሞ ከቀድሞው በ5 .7 በመቶ ያነሰ ድምጽ ነው ያገኘው ። ሁለቱ አውራ ፓርቲዎች የሁሉንም ትኩረት በሳበው የእሁዱ ምርጫ ካለፉት ምርጫዎች ያነሰ ውጤት ማምጣታቸው ብቻ ሳይሆን የግራ እና የቀኝ ጽንፈኛ ፓርቲዎች ከበፊቱ ምርጫ እጅግ የተሻለ ድምፅ ማግኘታቸው ማነጋገሩ ቀጥሏል ። በዚህ ምርጫ የግራው ፓርቲ ካለፈው ውጤት በ3 . 9 በመቶ ብልጫ 15.6 በመቶ ድምጽ ሲያሸንፍ ፣ አማራጭ ፖለቲካ ለጀርመን የተባለው ሙስሊሞች እና የውጭ ዜጎችን የሚጠላው ፓርቲ ደግሞ ከምንም ተነስቶ 14 .2 በመቶ ድምጽ አግኝቷል ። ከዚህ ሌላ የአረንጔዴዎቹ ፓርቲ 15.2 በመቶ ፣ የነጻ ዴሞክራቶቹ ፓርቲ ደግሞ 6.7 በመቶ አሸንፈዋል ። ከ5 በመቶ በላይ ድምፅ ያገኙት እነዚህ ስድስት ፓርቲዎች ናቸው የበርሊን ምክር ቤት ውስጥ የሚገቡት ። ይህ የምርጫ ውጤትም አብላጫ ድምጽ ያገኘው SPD ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ተጣምሮ መንግሥት ለማቋቋም የሚኖረውን ምርጫ ጠባብ አድርጎታል ይላሉ ጀርመን ለብዙ ዓመታት የኖሩት እና የተማሩት የህግ ባለሞያ እና የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር ዶክተር ለማ ይፍራሸዋ ። በርሳቸው አባባል አሁን SPD ከሌሎች ሁለት ፓርቲዎች ጋር ተጣምሮ መንግሥት መመስረት የሚችልበት አማራጭ ብቻ ነው ያለው ።የሶሻል ዴሞክራቶችን የመንግሥት ምሥረታ ምርጫ ያጠበበው የበርሊኑ ምርጫ ውጤት በመጪው ዓመት በሚካሄደው የጀርመን ፌደራል ሪፐብሊክ የምክር ቤት ምርጫ ላይ ተጽእኖ ማሳደሩ እንደማይቀር ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ይመስላል ። ዶክተር ለማ የበርሊኑ ምርጫ ውጤት የትላላቆቹን የጀርመን ፓርቲዎች ችግር ያሳያል ይላሉ ።ከበርሊኑ ምርጫ በፊት በሰሜን ጀርመንዋ በሜክለንቡርግ ፎርፖመርን ከሁለት ሳምንት በፊት በተካሄደ ምርጫ የክርስቲያን ዴሞክራቶች ህብረት ፓርቲ በአማራጭ ፖለቲካ ለጀርመን ፓርቲ ተሸንፎ ሦስተኛ ደረጃ ማግኘቱ አነጋግሮ ሳያበቃ በበርሊኑ ምርጫ በ10ኛ የጀርመን ፌደራል ግዛት ውስጥ መቀመጫ ማግኘቱ አሳስቧል ። ዶክተር ለማ እንደሚሉት ፓርቲው በዚህ መልኩ እየተጠናከረ ከሄደ ከአንድ ዓመት በኋላ በሚካሄደው የጀርመን ፌደራል ምክር ቤት ምርጫም ላይ የምክር ቤት መቀመጫዎችን የማግኘት እድሉ የሰፋ ነው ። እናም ይላሉ ዶክተር ለማ ህዝባዊ መሠረት ያላቸው ትላላቆቹ ፓርቲዎች ከወዲሁ የማስተካከያ እርምጃዎችን መውሰድ ይገባቸዋል ።

Frauke Petry Jörg Meuthen Bundespressekonferenz BPK Berlin
«አማራጭ ፖለቲካ ለጀርመን»ፓርቲ መሪዎችምስል picture-alliance/dpa/W.Kumm
Deutschland Bundeskanzlerin Angela Merkel in Berlin
አንጌላ ሜርክልምስል picture-alliance/dpa/M. Kappeler

ኂሩት መለሰ

አዜብ ታደሰ