1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የትራምፕ ውሳኔ እና ትችቱ

ሐሙስ፣ ኅዳር 28 2010

የፍልስጤማውያኑ መሪ ማህሙድ አባስ የትራምፕ ውሳኔ «ዩናይትድ ስቴትስ እስራኤልን እና ፍልስጤማውያንን ለመሸምገል ብቃት እንደሌላት አረጋግጧል ብለዋል። የፖለቲካ ተንታኞችም ትራምፕ የወሰዱት እርምጃ በእሳት እንደመጫወት ይቆጠራል ሲሉ እያስጠነቀቁ ነው።

https://p.dw.com/p/2oykY
Pakistan - Proteste gegen Jerusalem-Status  in Karachi
ምስል Reuters/A. Soomro

የትራምፕ ውሳኔ እሥራኤል እና ፍልስጤማውያን

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለእየሩሳሌም የእስራኤል ዋና ከተማነት ትናንት በይፋ እውቅና መስጠታቸው ከዓለም ዙሪያ ልዩ ልዩ ተቃውሞ እና ትችቶችን አስከትሏል። እርምጃው  በእስራኤል እና በፍልስጤማውያን መካከል ሰላም ለማውረድ ሲካሄዱ የቆዩትን ጥረቶች መና የሚያስቀር  በመካከለኛው ምሥራቅም አለመረጋጋትን የሚያስከትል ነው ሲሉ በርካታ መንግሥታት ትራምፕን ነቅፈዋል። የፍልስጤማውያኑ መሪ ማህሙድ አባስ የትራምፕ ውሳኔ «ዩናይትድ ስቴትስ  እስራኤልን እና ፍልስጤማውያንን ለመሸምገል ብቃት እንደሌላት አረጋግጧል ብለዋል። የፖለቲካ ተንታኞችም ትራምፕ የወሰዱት እርምጃ በእሳት እንደመጫወት ይቆጠራል ሲሉ እያስጠነቀቁ ነው። የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እየሩሳሌምን የእስራኤል ዋና ከተማ አድርገው መቀበላቸውን በይፋ ማሳወቃቸው አካባቢውን ወደ ኋላ ይልቁንም ወደ ጨለማው ጊዜ የሚወስድ እርምጃ ነው ሲል የአውሮጳ ህብረት ኮንኗል። የህብረቱ የውጭ ጉዳዮች መርህ ሃላፊ ወይዘሮ ፌደሪካ ሞገሪኒ ዛሬ በሰጡት መግለጫ የትራምፕ ውሳኔ በጣም አሳሳቢ ተጽእኖ ሊያሳድር ይችላል ሲሉ አሳስበዋል። እርምጃው ዩናይትድ ስቴትስ በአካባቢው ልትጫወት የምትችለውን ሚና የሚያኮስስ ነው ያሉት ሞጎሮኒ በዓለም ዙሪያም ተጨማሪ ውዥንብር ያስከትላል ሲሉም አስጠንቅቀዋል።ከትራምፕ ውሳኔ በኋላ ዛሬ በዮርዳኖስ ወንዝ ምዕራባዊ ዳርቻ ተቃውሞዎች እየተካሄዱ ነው። የትራምፕን ውሳኔ በመቃወም ፍልስጤማውያን አጠቃላይ አድማ መታዋል። ዛሬ ትምህርት ቤቶች እና ሱቆች የተዘጉ ሲሆን ጋዛን የሚቆጣጠረው ሀማስ ለአዲስ አመጽ ጥሪ አድርጓል። ቡድኑ ዛሬ ባስተላለፈው ጥሪ ደጋፊዎች ለሚያስተላልፈው ትዕዛዝ ተዘጋጅተው እንዲጠብቁ ጠይቋል። እስራኤል በበኩልዋ በአካባቢው በመቶዎች የሚቆጠሩ ተጨማሪ ወታደሮች እያሰማራች መሆኑን አስታውቃለች። ከእየሩሳሌሙ ዘጋቢያችን ጋር የተደረገው ቃለ ምልልስ እንዲሁም ከዋሽንግተን እና ከብራሰልስ የደረሱንን ዘገባዎች የድምጽ ማዕቀፎቹን በመጫን ማዳመጥ ይችላሉ። 

ዜናነህ መኮንን 

ናትናኤል ወልዱ

ገበያው ንጉሴ

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ