1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አዉሮጳ የባህል መዲና በኢትዮጵያዊዉ ዓይን  

ሐሙስ፣ ግንቦት 2 2010

«ከአዉሮጳ ሃገራት ነዋሪዎች ጋር ሆነን መወያየት የምንፈልገዉ ሁሉም በየፊናዉ የሚያነሳዉ ጉዳይ ነዉ። ለምሳሌ የተለያዩ ባህሎችን ማስተሳሰር፤ የከባቢ አየር ለዉጥን መቅረፍ፤ ድህነት፤ የሥራ አጥነት፤ መቅረፍ የሚሉት ይገኙበታል። አንድ አዉሮጳን በወንድማማችነት እና በጋራ በመመስረት የመጭዉ ዘመን ብሩህ ተስፋ ይሆናል።»

https://p.dw.com/p/2wwh6
Kulturhauptstadt Europas 2018 | Das Fries Museum in Leeuwarden
ምስል picture-alliance/dpa/Kulturhauptstadt Leeuwarden-Fryslan/R. Van Vliet

የኔዘርላንድዋ የአዉሮጳ የባህል መዲና

«ብዙ ጊዜ ሆላንዶቹ ተቆጥበዉ ነዉ የሚኖሩት። በክረምት ጊዜ የቤት ማሞቅያዉን ዝም ብለዉ በሌሉበት ሙሉ ቀን አይከፍቱም፤ አያሞቁም ። ያልተቀመጡበት ክፍል ዝም ብሎ መብራት ማብራት የለም፤ አላስፈላጉጊ ወጭ ዝምብ ሎማ ማጥፋት የለም ። ይህ ፀባያቸዉ ቆንቆናነት ሳይሆን ለሚቀጥለዉ ትዉልድ እሱም የሚበላዉ እንተዉለት እሱም እንደኛ እንዲኖር እድሉን እንሰጠዉ ብለዉ በማሰባቸዉ ነዉ። በእዚህ  ነገራቸዉ ሆላንዶች በጣም ያስቀኑኛል።»

DW Euromaxx - Leeuwarden
ምስል DW

በኔዘርላንድ ሲኖሩ ወደ አርባ ዓመት የሆናቸዉ እና በኔዘርላንድ መንግሥት መሥራያ ቤት ውስጥ በማህበራዊ ምክር አገልግሎት ሠራተኛነት የሚያገለግሉት አቶ ሲራክ አስፋው ዘንድሮ በሰሜናዊ ኔዘርላንድ የአዉሮጳ የባህል ማዕከል ተብላ ስለተመረጠችዉ «ሌዋርደን» ከተማ ካካፈሉን የተወሰደ ነዉ። 

ዘንድሮ የአዉሮጳ የባህል ማዕከል ተብለዉ የተሰየሙት ሃገር ከተሞች በደቡባዊ አዉሮጳ የምትገኘዋ የደሴት ሃገር የማልታ ርዕሰ ከተማ ቫሌታ እና የኔዘርላድንድ ፍሪስንላንድ ከተማ «ሌዋርደን» ናቸዉ። የአዉሮጳ ኅብረት አባል ሃገራት ባህላቸዉን ለማስተዋወቅ ነዋሪዎችንም ለማስተሳሰር ብሎም ለዓለም ሕዝብ ለማስተዋወቅ እና ትስስር ለመፍጠር ሲሉ በአዉሮጳዉያን አቆጣጠር ከ 1985 ዓ.ም ጀምሮ የአንድን  ሃገር ከተማ የአዉሮጳ የባህል መዲና ሲሉ በመሰየም የከተማዋን ጥንታዊነት ታሪካዊነት የሕዝቡን አኗኗር እና ባህል ማስተዋወቅ ጀምረዋል። የሃገራቱን ከተሞች በይበልጥ ለማስተዋወቅ እና ለጎብኝዎች አመቺ ሁኔታን ለመፍጠር ሲባል ከ 17 ዓመት ወዲህ ሁለት የአዉሮጳ ኅብረት አባል ሃገራት ከተሞች በባህል ርዕሰ ከተማነት መሰየም ጀምረዋል። በዚህ ዝግጅታችን የዛሬ በስፋት የምንመለከተዉ በኔዘርላንድዋን የፍሪስላንድ ግዛት ዋና ከተማ «ሌዋርደን»ን ነዉ።  

Ferd Crone, Bürgermeister Leeuwarden
ምስል DW/B. Riegert

ግሩም የመልከዓ ምድር አገቀማመጥ ያላት የሰሜናዊ ኔዘርላንድ ከተማ ሌዋርደን ከተማበሰዉ ሰራሽ ካናሎች እና የተለያዩ ጥንታዊ ሕንጻዎችን ያቀፈች ናት። ወደ 108 ሺ ነዋሪዎች የሚኖሩባት የፍሪስላንድ ግዛት በፈርጣማ እና ዉብ ፈረሶቻቸዉ እንዲሁም  በአብዛኛዉ ነጭ ጥቁር ነጠብጣባማ ከብቶች ባለኃብትም እንደሆን ይነገርላቸዋል። በሌዋርደን ከተማ መሃል የሚገኙትና በተለያዩ ቀለሞች የተገነቡት እድሜ ጠገቦቹ በጡብ ሸክላ የተገነቡት ሕንጻዎች በአምስተርዳም ከተማ ካሉት ጋር ስለሚያመሳስላቸዉ የኔዘርላንድ ነዋሪዎች ሌዋርደንን ትንሽዋ አምስተርዳም ሲሉም ይጠርዋታል። በያዝነዉ የአዉሮጳዉያን 2018 ዓመት የመጀመርያ ወር ጀምሮ ከተማዋ ለጎብኝዎች ባቀረበቻቸዉ  የተለያዩ የባህል ትዕይንቶች ዓዉደ ርዕዮች እንዲሁም የዉይይት መድረኮች እያሳተፈችና እየጋበዘበት የምትገኘዉ የአዉሮጳ የባህል መዲና የሌዋርደን ከንቲባ ፍሪድ ክሮነ እንደሚሉት ከሌሎች አዉሮጳ አባል ሃገራት ነዋሪዎች ጋር በጋራ ነዋሪዉን በባህል ማቆራኘት ነዉ።       

«ከሌላዉ የአዉሮጳ ሃገራት ነዋሪዎች ጋር ሆነን በከተማችን ዉስጥ መወያየት የምንፈልገዉ ሁሉም በየፊናዉ የሚያነሳዉ ጉዳይ ነዉ። ለምሳሌ የተለያዩ ባህሎችን ማስተሳሰር፤ የከባቢ አየር ለዉጥ፤ ድህነት ፤ የሥራ አጥነት፤ እንዲሁም የተለያዩ ቋንቋዎችን መናገር የሚሉት ይገኙበታል። አንድ አዉሮጳን በወንድማማችነት እና በጋራ በመመስረት የመጭዉ ዘመን ብሩህ ተስፋ ይሆናል።» በአዉሮጳ የባህል ርዕሰ ከተማነት የተሰየመችዉ «ሌዋርደን» በመጭዉ ጊዜያት ያስቀመጠቻቸዉ እቅዶች ይህን ይመስላሉ። በሮተርዳም ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ሲራክ አስፋው በአዉሮጳ የባህል ርዕሰ ከተማነት የተሰየመችዉ ሌዋርደን በመጭዉ ጊዜያት ያስቀመጠቻቸዉ እቅዶች ይህን ይመስላሉ። በሮተርዳም ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ሲራክ አስፋው እንደነገሩን በየአዉሮጳ ኅብረት አባል አገራት የባህል ርዕሰ ከተማ በሚል በመሰየም በተለያዩ ዝግጅቶች በአንድ መድረክ የሚገናኙት፤ በፈጣን ሁኔታ በምትቀያየረዉ ዓለማችን ኃብረተሰቡ በጥሩመንፈስና ሁኔታ አንድነትን እንዲፈጥር ነዉ።  

Europäische Kulturhauptstadt 2018 Leeuwarden Bahnhof
ምስል DW/B. Riegert

«የአዉሮጳ አባል ሃገራት የባህል ከተማ መንፈስ፤ የተለያዩ የአዉሮጳ ሃገራትን ባህል ማስተዋወቅ ነዉ። ብሎም ሰዉ ወደፊት ተግባብቶ በጋራ አንድ አዉሮጳ የሚለዉን ለማጠናከርም ነዉ። ማን ምን አይነት አመለካከት ማን ምን አይነት ደስ የሚል ባህል አለዉ፤ ማ ምን አይነት የኪነት ባህል አለዉ የሚል ነዉ። ከዚህ ጋር ተያይዞ ለአዉሮጳ በአጠቃላይ ለሰዉ ልጅ ምን የሚጠቅም ነገር ታስቦአል፤ የሚል ጥያቄንም የሚመልስ ስራ ይሰራል። የሰሜናዊ ሆላንድ የፍሪስላንድ ጠቅላይ ግዛት ከንቲባ ክሮነ ይባላሉ ብዙ ነገር ሰርተዋል። ለ 2018 ዓ.ም የአዉሮጳ ከተማ የባህል ማዕከል ለመሆን አምስት የሆላንድ ከተሞች ተወዳድረዉ ነበር። የሰሜን ሆላንድዋ ከተማ ሌዋርደን ያሸንፍል ብሎ የጠበቀ ያለ አይመስለኝም። ያሸንፍል የተባለዉ የሆላንድ ከተማ ዘ ሄግ ነበር። ዘ ሄግ በመሸነፉ የከተማዋ ነዋሪዎች በጣም ደንግጠዋል። በአዉሮጳ የባህል ከተማ ሆኖ ሲመረጥ የተመረጠዉ ከተማ የተለያዩ ባህላዊ እንቅስቃሴዎችን የሚያዘጋጀዉ  ለአስር ወራት ነዉ። የዚህ ዝግጅት ዋና መልክት ኅብረትና አንድነት አቅፎ እንደዚህ በመለዋዋጥ ላይ በምትገኘዉ ዓለማችን ኅብረተሰቡ በጥሩ መንፈስ ወዲትና እንዲት እንደሚሄድ በማሰብ ያንን በትዕይንት ለኅብረተሰቡ ለማሳየት መሞከር ነዉ።» 

የኔዘርላነዱ ንጉሥ ቪለም አሌክሳንደር እና ባለቤታቸዉ ንግሥት ማክሲማ በያዝነዉ የጎርጎረሳዉያን ዓመት 2018 መጀመርያ ወር ላይ ሌዋርደን ተገኝተዉ ከተማዋ ለጎብኝዎችዋ ያቀረበችዉን የተለያዩ ዝግጅቶች መርቀዉ ከፍተዋል። በመክፈቻዉ ሥነ-ሰርዓት ምሽት ላይ በመድረክ የቀረበዉ እና በተለያዩ ቀለማት በታጀበዉ የመብራት ትርኢት ከተማዋ በዓመት ዉስጥ ለእይታ የምታቀበዉን የተለያዩ ዝግጅቶች ተዋዉቀዋል፤ የፍሪስላንድ ነዋሪ ጎብኝዎችን እንግዶቹን እጁን ከፍቶ እንደሚጠብቅም ተነግሮአል።  በመክፈቻዉ ሥነ ስርአት ላይ የቀረበዉ የብርሃን ትርኢት ዳይሬክተር ኢራ ያዳኮቭስካያ እንዳሉት በምናቀርባቸዉ ትርኢቶች ሁሉ የአንድነት ስሜትን መፍጠር እንሻለን። 

Niederlande Leeuwarden Europäische Kulturhauptstadt
ምስል DW/B. Riegert

 «ከተማችንን የጎበኙ ሠዎች ወደመጡበት ሲመለሱ ከጎረቤቶቻቸዉም ሆነ ከሌሎች የአዉሮጳ ሃገራት ነዋሪዎች ጋር የአንድነት ስሜትን ይዘዉ እንዲሄዱ እንፈልጋለን። አሁን እንደምናየዉ ከሆነ አብዛኞች ሃገራት በሮቻቸዉን ዘግተዉ ተቀምጠዋል። አንዳችን አንዳችንን እንዳንፈራ በአንድ መድረክ ተቀምጠን በመወያየት እና በመስራት በጋራ መቆም ይኖርብናል።» የዳይሬክተር ኢራ ያዳኮቭስካያን ጥሪ የሌዋርደን ነዋሪዎች ከልብ የተቀበሉት ይመስላል። በዚሁ ዝግጅት ላይ ለመታደም በከተማዋ የሚኖሩ ወደ 14 ሺህ ነዋሪዎች ተገኝተዉ ነበር ። በሦስት የተለያዩ ቦታዎች ላይ በቀጥታ ስርጭት በሰፊ የመንገድ ላይ ስክሪን የተሰራጨዉን ዝግጅት የታደሙ ነዋሪዎች የተለያዩ አስተያየቶችን ሰጥተዋል። «ሌዋርደን የኔ ከተማ ነች። በጣም ዉብ የሆነች ከተማ ነች ያለችን ከተማችንን ለመላዉ ዓለም ማሳየት እንፈልጋለን » «በሌዋርደን በጣም በጣም ኮርቻለሁ። በፍሪስላንድ በተባለዉ ዉብ የኔዘርላንድ ግዛት እንኖራለን፤ ፍሪስላንድ ትንሽ ግዛት ብትሆንም በጣም ቀና ልብ ያለን ነዋሪዎች ነን» የሰሜን ኔዘርላንድዋ ከተማ የአዉሮጳ ኅብረት የባህል ማዕከል ሆኖ ለመሰየም የሚጠበቁባትን ፈተናዎች አልፋ መሆኑን የነገሩን በሮተርዳም ነዋሪ የሆኑት አቶ ሲራክ አስፋዉ፤ የከተማዋ ከንቲባ የአዉሮጳ የእግር ኳስ ሻንፕዮና የማሸነፍ ያህል መደሰታቸዉን ነግሮናል።

ምርጫዉን ያሸነፉበት ትንሽ እንደምሳሌ ለመጥቀስ ፤ ንጹሕ ዉኃ የማግኘት ዋስትና ፤ የተለያዩ ባህሎችን አስተባብሮ በሰላም መኖር፤ ዘላቂ ፈጠራዎች ለምሳሌ ኃይል ማመንጫ፤ ከነዳጅ ዉጭ ለምሳሌ በፀሐይ በንፋስ ፤ ሌላዉ ፍሪስላንድ ዉስጥ የተነሳዉ ድሕነትን ማጥፋት። ሆላንድ በጣም ሃብታም ሃገር ብትኖርም ከኅብረተሰቡ ኑሮ አኳያ ስር ያሉም ሰዎች አሉባት። ሰዎቹ ከእጅ ወድአፍ ብቻ ይኖሩ ይሆናል፤ በበሽታ አልያም በእድሜ መግፋት ሥራ ባለማግኘት ገንዘብ በቂ ላይኖራቸዉ ይችላል። እና ይህን ችግር ለማጥፋት ተነስተናል ነዉ የሚሉት። በኔዘርላንድ የአዉሮጳ የባህል ከተሞች ተብለዉ የተመረጡት ከአሁኑ ሌዋርደን ጋር ሦስት ሃገራት ተመርጠዋል ። ከዚህ ቀደም በአዉሮጳዉያን 1987 ዓ,ም አምስተርዳም ፤ ሮተርዳም ደግሞ በአዉሮጳዉያኑ 2002 ዓ,ም የአዉሮጳ የባህል ማዕከል ሆነዉ ተመርጠዉ ከፍተኛ ዝግጅትን አድርገዋል። የሌዋርደን ከንትባ እንደተናገሩት የኔ ከተማ ተመራጭ መሆንዋን ስሰማ የአዉሮጳ የእግር ኳስ ሻንፕዮናን እንዳሸነፍኩ ያህል ነዉ የተሰማኝ ስሜት ብለዉ ተናግረዋል። »

እስከ 18 ኛዉ ምዕተ ዓመት መጨረሻ የኔዘርላንድዋ ከተማ ሌዋርደን የንጉሳዉያን ቤተሰቦች መኖርያ እንደነበረች ይነገርላታል። በዚህም የኔዘርላነዱ ንጉሣዉያን ቤተሰቦች በተደጋጋሚ ከተማዋን እንደሚጎበኙ ተነግሮአል።  ሌዋርደን ከተማ ከያዘቻቸዉ ታሪካዊ ቤተ መዘክሮች የተለያዩ የፊልም ቤቶችና የትምህርት ተቋማት ሌላ የጎብኝዎችን ቀልብ የሚማርከዉ በከተማዋ ረዥም የሚባለዉ ጠማማ ጥንታዊ የሕንፃ ማማ ይገኛል። ሕንጻዉ በኢጣልያ ቶስካና ግዛት እንደሚገኘዉ ጠማማ ማማ ፒዛ አይነት ነዉ። በኔዘርላንድዋ ሌዋርደን ከተማ እንብርት ላይ የሚገኘዉ ጠማማ የቤተ ክርስትያን ደወል ያለበት ማማ በ 16ኛዉ ክፍለ ዘመን የተገነባ ሲሆን ግንባታዉ የተጀመረዉ በከተማዋ ከፍ ብሎ ከሕንጻዎች ሁሉ ረጅም ቁመት ያለዉ ቤተ-ክርስትያን ለማነፅ የተጀመረ ነበር። ሕንጻዉ በረጅሙ በመገንባት ላይ ሳለ 14 ሜትር ቁመት ሲደርስ መስመጥ በመጀመሩ መቋረጡን የታሪክ መዝገባት ያሳያሉ። ከዝያን ጊዜ ጀምሮ ሕንጻዉ እየሰመጠ እየአዘነበለ እስካሁን ያለምንም ተግብር ግን የከተማዋ የቱሪስት መስዕብ ሆኖ ተጣሞ ቆምዋል።

Kulturhauptstadt 2018 - Leeuwarden, Niederlande
ምስል Imago/ecomedia/R. Fishman

በሽዎች የሚቆጠሩ የኔዘርላንድዋ ሌዋርደን ከተማ ነዋሪዎች ከተማዋ ባጠጋጀቻቸዉ ከ 300 በሚበልጡ ልዩ ልዩ ባህላዊ ክንዉኖች ዉስጥ በመሳተፍ የከተማዋን ጎብኝዎች ማስተናገዳቸዉን ቀጥለዋል። የሌዋርደን ከተማ የዘንድሮዉ ባህላዊ ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ቴጀርድ ፎን ቤኩም እንደሚሉት ማኅብረሰቡን ጥንካሬ የሰጠዉ ባህልና ኪነ-ጥበብ ነዉ። «ባህል ኪነጥበብ ማኅበረሰቡን መንፈሰ ሙሉ አድርጎ ደግፎ ያቆመዉ ነዉ። በከተማችን በሚደረጉት የተለያዩ የባህል እንቅስቃሴዎች ሰዎች ለሰዎች መቆማቸዉን እናሳያለን። ወደ ኔዘልላንድዋ ግዛት ፍሪስላንድ ስትመጣም ይህንኑ ነዉ የምታየዉ። በዚህ አቋማችን የጎብኝዎቻችንን ቀልብ መሳብ እንፈልጋለን። »

ሙሉዉን መሰናዶ የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመቻን ይከታተሉ!

አዜብ ታደሰ

ሂሩት መለሰ