1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የንፁሕ የመጠጥ ውኃ ችግር በኢትዮጵያ

ማክሰኞ፣ መጋቢት 18 2010

የዘንድሮው የዓለም የውኃ ቀን ባለፈዉ ሐሙስ ዕለት ሲታሰብ የተመድ ያወጣዉ መረጃ 663 ሚሊየን ሕዝብ በቤቱ አቅራቢያ የንፁሕ ውኃ አቅርቦት እንደሌለው አመልክቷል። ዋተርኤይድ የተባለዉ ድርጅት በበኩሉ ኢትዮጵያ ዉስጥ 61 ሚሊየን ሕዝብ ንፅሕናዉ የተጠበቀ ዉኃ ማግኘት እንደማይችል ይገልጻል።

https://p.dw.com/p/2v5f0
Äthiopien Wokro In the drought area in Wokro ( avalibility of Water by UNESCO support )
ምስል DW/G. Tedla

በዋና ከተማዋ አዲስ አበባም የከፋ ነው፤

በተለይም በገጠር አካባቢ ሴቶች እና ሕፃናት ውኃ ለመቅዳት ከሦስት ሰዓት ያላነሰ በየቀኑ እንደሚጓዙም የድርጅቱ ድረገጽ ዝርዝር መረጃ ያመለክታል። በዶቼ ቬለ ዋትስአፕ መስመር ስለውኃ አቅርቦት አስተያየታቸዉን ያጋሩን አድማጮቻችን መልዕክትም የዚህን እውነትነት የሚያመላክት ይመስላል። 

«አይ የአዲስ አበባ ነዋሪ በአሁን ወቅት አቅሙ ያለው የመስመር ውኃን መጠቀም አቁሞዋል። አማራጩ የሌለው ነዋሪ ግን ፈጣሪን በመመካት ዝም ብሎ ይጠቀማል። የውኃሀ መስመር አመጣጡን ብታዩት በጣም ይዘገንናል፡ መስመሮቹ በሚያልፋበት ቦታ ሁሉ ይህ የፕላስቲክ ውኃ መስመር ከመቶ 90 ፕርሰንቱ በቆሻሻና የሽንትቤት ፍሳሽ በሚያልፍበት ላይ ነው የሚያልፈው። ብታዩት ለማመን በሚከብድ ሽንት በሚደፋባቸው ወንዞችና ኩሬዎች ላይ ነው መስመሮቹ የተዘረጉት። ማን እንደ ሚጠየቅ እንኩዋን የማናውቅበት አገር ላይ ነው ያለነው፡ በቀበሌ ስብሰባ ላይ ንፁህ ውኃ አይመጣልንም እንዴት ነው ነገሩ ብለን ስንጠይቅ በማግስቱ የሚጠብቀን ምላሽ መንግስትን እየተቃወምክ ነው ትባላለህ፤ ምን እንደ ሚሻል አናውቅም። ተወልደን ባደግንበት አገር እንደ ሁለትኛ ዜጋ እየተቆጠርን ነው።» ይላል አንደኛዉ አስተያየት፤

«ተወልጄ ያደኩት በአዲስ አበባ ባልቻ ሆስፒታል አካባቢ ነዉ፤ አሁን በ 30ዎቹ እድሜ እገኛለሁ። ሰፈሩ የድሮ ስለሆነና መሀል ከተማ ስለሆነ የዉኃ ችግር ሊያሳስብ ባልተገባ፤ ሆኖም ከ3 ና 4 አመታት ጀምሮ ዉኃ ማግኘት ብርቅ ሆኗል። አብዛኛዉን ጊዜ ለሊት ተነስቶ መጠበቅ የግድ ነው። የንፅህናዉ ነገርም አያስተማምንም: አንዳንዴ ያልተለመደ ጠረንና መደፍረስ አለዉ። ይሄንንም የማያገኝ አለ በሚለዉ እየተፅናናን ከችግሩ ጋር አብረን አለን። መቼም የሚቀርብ ሰበብ አያልቅባቸዉም።» ይላል ሌላኛዉ።

Äthiopien Frauen mit Kanistern
ምስል Reuters/T. Negeri

አብዛኞቹ አስተያየቶች የአዲስ አበባን የውኃ አቅርቦት ችግር አጉልተዉ የሚያሳዩ በመሆናቸዉ ከአዲስ አበባ ዉኃ እና ፍሳሽ ምላሽም ሆነ ማብራሪያ ለማግኘት ከፍተኛ ጥረት ብናደርግም አልተሳካልንም። ከዋና ከተማዋ በተጨማሪ በሌሎች አካባቢዎችም የውኃ ችግር መኖሩን የሚያመለክቱት አስተያየቶች ደግሞ እንዲህ ይላሉ፣ ስለውኃ ትንሽ ላካፍላችሁ ያሉን ደግሞ ከጎንደር ነው «በጎንደር አካባቢ ልዩ ቦታው አይምባ በሚባል አካባቢ ተማሪዎች እና ማኅበረሰቡን ለማሰልጠን ሄደን ውኃ ከመጣ ብዙ ዓመት አስቆጥሯል አሉን። እኛም ተማሪዎች ተማሪዎች ካየናቸው የጉድጓድ ውኃ በወረፋ ነው ያውም አምስት ብር ለአንድ ጀሪካን ከፍለው የሚቀዱት። ማኅበረሰቡም ለበላይ አካል ብናመለክትም የሚሰማን የለም እስኪ እናንተ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች አስተላልፉልን ብለዋል። ስለዚህ እንኳን ንፁሕ ውኃ ቆሻሻዉንም ባገኘነው እና ጠጥተን በሞትን ይላሉ።» በማለት የኅብረተሰቡን የውኃ ችግር ገልጸዋል።

የአድማጮቻችንን በየአካባቢዉ ያለዉን የውኃ ችግር ስታደምጡ የአባይን ልጅ ውኃ ጠማው ሳትሉ አልቀራችሁም። ስለብዙ የዉኃ ሀብቷ የሚነገርላት ሀገር በየጊዜው ሕዝቧ ስለዉኃ ችግር ማውራቱ ጉራማይሌውን ያመላክታል። በእርግጥስ ኢትዮጵያ መቶ ሚሊየን ለሚገመተዉ ሕዝቧ በቂ ውኃ አላት ይሆን? በውኃ ላይ ጥናቶች የሚያካሄዱት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስነምድር ትምህርት ዘርፍ ረዳት ፕሮፌሰር፤ ዶክተር ሰይፉ ከበደ ኢትዮጵያ ስላላት የውኃ ሀብት መነገር የሚገባው እውነታ አለ ይላሉ።

Äthiopien Flüchtlingslager Flüchtlinge aus Eritrea
ምስል Reuters/T. Negeri

«ኢትዮጵያ ከፍተኛ የሆነ የውኃ ሀብት አላት የሚለው በተለምዶ የሚነገር ነው። ሆኖም እውነታዉ ምንድነው የሚለውን መጀመሪያ ማስቀመጥ እፈልጋለሁ። በ1960ዎቹ እና ከዚያ በፊት የነበሩ የኢትዮጵያ የውኃ ሀብት ምን ያህል ነው ተብሎ በሚጠናበት ጊዜ የነበረው የውኃ ሀብት እና በሕዝቡ ቁጥር ተካፍሎ ሲታይ፤ ለአንድ ሰው በነፍስ ወከፍ የሚደርሰው የውኃ መጠን ከሁለት ሺህ ሜትር ኪዩብ በአንድ ግለሰብ በዓመት ይደርሰዋል፤ ይኸም ከፍተኛ ተብሎ ሊጠራ የሚችል ነው። ሆኖም ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ የሕዝብ ቁጥር እየጨመረ ሄዶ አሁን ባለንበት ደረጃ የአንድ ሰው የነፍስ ወከፍ የውኃ ሀብት በኢትዮጵያ ደረጃ አንድ ሺህ አንድ መቶ አንድ ሺህ ሁለት መቶ ሜትር ኪዩብ ሆኗል ይሄ ደግሞ የውኃ እጥረት አለባቸዉ ከሚባሉት አገሮች ውስጥ ለመግባት ጫፍ ላይ ደርሳለች ማለት ነው ኢትዮጵያ።»

እሳቸዉ እንደሚሉት ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ውኃ የሚገኘው በተወሰኑ ወቅቶች ነው። በበጋ ደግሞ  የውኃዉ መጠን አነስተኛ የሚባል ነው። በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያ ያላትን የውኃ ሀብት ባለሙያዎቹ አስቸጋሪ እንደሚሉት ነው የሚናገሩት። በዚያም ላይ ያላት የውኃ ሀብት በሀገሪቱ አካባቢዎች ሁሉ በእኩል የሚገኝ አለመሆኑም ሌላዉ ችግር ነው። በተለይም አርብቶ አደሩ በሚገኝበት አካባቢ ከፍተኛ የውኃ እጥረት መኖሩንም አመልክተዋል። የውኃ እጥረቱ ታዲያ በቆላማ አካባቢዎች ብቻ የተወሰነ አይደለም በደጋውም ይታያል ነዉ የሚሉት ዶክተር ሰይፉ። ኢትዮጵያ የተመድ የመጠጥ ውኃን ሽፋንን ለማዳረስ አቅዶት የነበረዉን የአምዓቱን ግብ በጎርጎሪዮሳዊዉ 2015ዓ,ም መድረሷን የጠቀሱት ዶክተር ሰይፉ፤ ይህ ምን ማለት እንደሆነ ያብራራሉ።

Äthiopien Mann wäscht seine Hände
ምስል Reuters/T. Negeri

አቅርቦቱን ለማስተካከልም ውኃዉ የሚገኝባቸውን ምንጮች ማበራከት፤ በአጠቃቀም ረገድ ደግሞ ላለው የውኃ ሽሚያ መፍትሄ መፈለግ ችግሩን ለማቅለቅ እንደሚረዳም ይዘረዝራሉ። የውኃ አማራጮች በበዙ ቁጥር ሁሉንም ለመጠጥ ማዋል ይቻላል ማለት እንዳለሆነ ያሳሰቡት ባለሙያዉ፤ ጨዋማነታቸው የበዛዉንም ሆነ በባክቴሪያ የተበከሉ የዉኃ ምንጮችን በተገቢው መንገድ እያከሙ ለአገልግሎት ማዋልም ሌላው ስልት እንደሆነ ገልጸዋል። ማዕከላዊ የውኃ አቅርቦት አላት ስላሏት አዲስ አበባ ውኃ ጉዳይ ደግሞ ይህን ይላሉ። ለውኃዉ እጥረት ዋና ምክንያት ያሏቸዉንም ነጥቦች አንስተዋል።

Äthiopien Landschaft in Provinz Afar Menschen an Wasserstelle
ምስል picture-alliance/Lonely Planet

የንፅህናዉን ጉዳይ በተመለከተም፤ በቅርቡ ይፋ ያልሆነ ጥናት አዲስ አበባ ውስጥ ከ100 ዘጠና አራት እጁ ውኃ ንፁሕ እና ለመጠጥ ሊሆን የሚችል መሆኑን ማመልከቱን ነዉ የገለፁልን። ቧምቧዉ ውኃ ሳይተላለፍበት ለረዥም ጊዜ መቆየቱ የሚያስከትለዉ ዝገት አንዳንዴም ቆሻሻ ሊያስገባ የሚችል ፍሰት ሊያጋጥም የሚችልበት ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችልም አመላክተዋል። የዘንድሮዉ የዓለም የውኃ ቀን መሪ ቃል፤ ተፈጥሮ ለውኃ የሚል ነው። ሀሳቡም በአካባቢ ተፈጥሮ ላይ የሚደርሰው ጥፋት፣ የአየር ንበረት ለውጥ እና የውኃ መበከል ያስከተሉትን የውኃ እጥረት ባለንበት የ21ኛዉ መቶ ክፍለ ዘመን ተፈጥሮን በመከባከብ ማስተካከልን ያመላክታል።

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ