1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

"የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በኢትዮጵያ መደንገግ የሰብዓዊ መብቶችን ይገድባል" ጀርመን

ረቡዕ፣ የካቲት 14 2010

የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሰላማዊ ለውጥ እና አስፈላጊ ማሻሻያ የሚያመጣው ከሚመለከታቸው የፖለቲካ አካላት ጋር አካታች እና ሰፊ ውይይት ብቻ እንደሆነ እናምናለን ብሏል። መሥሪያ ቤቱ እንዳለው እንዲሕ አይነቱ ውይይት ለኢትዮጵያ ዘላቂ ውስጣዊ ሰላም እና መረጋጋት መንገድ ይጠርጋል። 

https://p.dw.com/p/2sz5V
Auswärtiges Amt Schild Berlin
ምስል Fotolia/Tom-Hanisch


የኢትዮጵያ ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ እንዳሳሰባት ጀርመን ገለጸች። የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ ባወጣው መግለጫ "የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በኢትዮጵያ መደንገግ የሰብዓዊ መብቶችን ይገድባል" ብሏል። በጀርመን መንግሥት የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ድረ-ገፅ ይፋ የሆነው መግለጫ "መንግሥት በኃይል አጠቃቀም ረገድ ከፍተኛ ጥንቃቄ ያደርጋል ብለን ተስፋ እናደርጋለን" ሲል አትቷል። ኢትዮጵያ ከጀርመን ጋር መልካም ወዳጅነት እንዳላት ጠቅሶ ለፖለቲካዊ ውይይት ተጨማሪ ምኅዳር ለመፍጠር የኢትዮጵያ መንግሥት ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የሚያደርገውን ጥረት እንዲያጠናክር ጥሪ አቅርቧል። ባለፉት ሁለት ወራት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች አባላት ከእስር መለቀቃቸውን መግለጫው አድንቋል። 
የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሰላማዊ ለውጥ እና አስፈላጊ ማሻሻያ የሚያመጣው ከሚመለከታቸው የፖለቲካ አካላት ጋር የሚደረግ አካታች እና ሰፊ ውይይት ብቻ እንደሆነ እናምናለን ብሏል። መሥሪያ ቤቱ እንዳለው እንዲሕ አይነቱ ውይይት ለኢትዮጵያ ዘላቂ ውስጣዊ ሰላም እና መረጋጋት መንገድ ይጠርጋል። 
ብሪታኒያ በተመሳሳይ ትናንት ባወጣችው መግለጫ ጊዜው ለኢትዮጵያ አሳሳቢ መሆኑን ገልፃ ነበር። በብሪታኒያ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በምኒስትር ማዕረግ የአፍሪቃ ኃላፊዋ ሐርየት ባልድዊን የኢትዮጵያ መንግሥት የደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዳሳሰባቸው እና እንዳስከፋቸው ገልጸዋል። 
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መደንገግ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እና ለውጭ ባለወረቶች ተስፋ አስቆራጭ መልዕክት ማስተላለፉንም ጠቁመዋል። ውሳኔው በኢትዮጵያ በቅርብ ጊዜያት የታየው ማሻሻያ የማድረግ እርምጃ ለመቀልበሱ ምልክት አይሆንም ብለን ተስፋ እናደርጋለን ያለው የሐርየት ባልድዊን መግለጫ በሥራ ላይ የሚቆየው ለአጭር ጊዜ እንደሚሆን ያለውን ተስፋም አትቷል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ገቢራዊ ሲሆን የኢትዮጵያ መንግሥት ሰብዓዊ መብቶች እና ሕገ-መንግሥቱ መከበራቸውን እንዲያረጋግጥም ጠይቋል። በመግለጫው "በጅምላ የማሰር ሥልጣን እና የኢንተርኔት አገልግሎት ገደብ ሊወገዱ ይገባል" ሲል ገልጿል። 

እሸቴ በቀለ

ኂሩት መለሰ