1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አንድ የገዢው ግንባር የቅርብ ሰው አቶ በረከት ሥልጣን የሚለቁት "በጡረታ ነው" ብለዋል

ረቡዕ፣ ጥቅምት 8 2010

አንጋፋዉ የኢሕአዴግ ታጋይና ባለሥልጣን አቶ በረከት ስምዖን ኃላፊነታቸውን "ለመልቀቅ" ደብዳቤ ማስገባታቸውን የኢትዮጵያ መንግሥት አረጋግጧል።በመንግሥትና በገዢው ግንባር ውስጥ "አድራጊ ፈጣሪ፤ ሿሚ ሻሪ" ናቸው የሚባልላቸው አቶ በረከት ከግማሽ ምዕተ-ዓመት በላይ ከቆዩበት የሥልጣን አካባቢ መራቅ የፈለጉበት ምክንያት እስካሁን በይፋ አልተገለጠም።

https://p.dw.com/p/2m2Nf
Äthiopien Regierungsvertreter
ምስል DW/Tesfalem Waldyes

አቶ በረከት ኃላፊነት የሚለቁበት ምክንያት አልተገለጠም

በሚንስትር ማዕረግ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሆነው በማገልገል ላይ የነበሩት አቶ በረከት ስምዖን ከኃላፊነታቸው ለመልቀቅ መጠየቃቸውን የኢትዮጵያ መንግሥት አረጋግጧል። ለገዢው ፓርቲዉ ቅርበት ያለው ራዲዮ እንደ ዘገበው አቶ በረከት ጥያቄያቸውን ለጠቅላይ ምኒሥትሩ አስገብተዋል። ምክንያታቸው ግን በይፋ አልተገለጠም።  አንድ የገዢው ግንባር የቅርብ ሰው አቶ በረከት ሥልጣን የሚለቁት "በጡረታ ነው" ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። 

የፖለቲካ ተንታኙ አቶ ቻላቸው ታደሰ "በመንግሥት ሥልጣንም ሆነ በኢሕአዴግ ውስጥ ከመጋረጃ ጀርባ አድራጊ ፈጣሪ፤ ሿሚ ሻሪ ተደርገው" ይቆጠራሉ የሚሏቸው አቶ በረከት ኃላፊነታቸውን ለመልቀቅ የወሰኑበት ምክንያት አነጋጋሪ መሆኑ አልቀረም።  አቶ ቻላቸው እንደሚሉት አቶ በረከት "ከአቶ መለስ ሞት በኋላ በድርጅቱም ሆነ በመንግሥታዊ ሥልጣኑ ብዙም እርካታ እንዳልተሰማቸው" ምልክቶች ነበሩ።

ገዢው ግንባር "በዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት የምመራ ነኝ ባይ ስለሆነ" የአቶ በረከት የመልቀቅ ጥያቄ በማዕከላዊ ኮሚቴ እና በፖሊት ቢሮ ጭምር ውይይት እንደሚደረግበት የፖለቲካ ተንታኙ ተናግረዋል። "በድንገት መልቀቃቸው የሚያመላክተው ነገር በድርጅቱ ውስጥ የተወሰኑ መከፋፈሎች እንዳሉ እና ከአሸናፊው ወገን ሊሆኑ እንዳልቻሉ እና የመሰላቸት ምልክት እንደታየባቸው ነው።" ሲሉ ያክላሉ

Äthiopien Regierungsvertreter
ምስል DW/Tesfalem Waldyes

አቶ በረከት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የቦርድ ሊቀ-መንበርነታቸው እና ከአማራ ክልል ገዢ ፓርቲ ብአዴን ጋር ትስስር ያለው ጥረት ኮርፖሬት ውስጥ የነበራቸውንም ኃላፊነቶች አስረክበዋል።

አቶ ያሬድ ጥበቡ በኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) እና በኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኢሕዴን) በትግል አጋርነት አቶ በረከትን በቅርብ ያውቋቸዋል። "በረከት ድርጅቱ አስከፊ ችግሮች ውስጥ በነበረበት ጊዜ ሁሉ በቀላሉ እጁን ያልሰጠ ሰው ነበር" የሚሉት አቶ ያሬድ በብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) ውስጥ ያላቸው "ተቀባይነት መድከም" ለውሳኔያቸው ምክንያት ሊሆን ይችላል ሲሉ ይጠረጥራሉ።

"በራሱ ብአዴን ውስጥ ተቀባይነቱ እየደከመ መምጣት እና እሱ የአማራ ክልል አስተዳደሩን ይዞ ከሕውሓት ተፅዕኖ ነፃ ለመሆን ወይም የሚገባቸውን ክብር ለመፈለግ የሚያደርጉት ትግል ውስጥ እንደ ደንቃራ እያዩት ስለመጡ ብአዴን ውስጥ የመጣው አዲሱ አመራር እና ካድሬ ጋራ እሱ ታደሰ ጥንቅሹ እና ካሳ ተክለብርሐን ችግር እንደነበረባቸው በተደጋጋሚ እሰማ ነበር።"

አቶ በረከት የገዢው ግንባር፤ የግንባር ሰው ሆነው ሲታገሉለት እና ሲሟገቱለት ኖረዋል። የፖለቲካ ተንታኙ አቶ ቻላቸው "ከባድ ፖለቲከኛ" ይሏቸዋል። በማስታወቂያ ሚኒሥትርነት እና በጠቅላይ ሚኒሥትሩ አማካሪነት ኢሕአዴግ ሥልጣን ከተቆናጠጠበት ጊዜ ጀምሮ ሲያገለግሉ ቆይተዋል። ለአቶ ቻላቸው አቶ በረከት ጥለው ያለፉት አሉታዊ ውርስ ገዝፎ ይታያቸዋል።

Äthiopien Regierungsvertreter
ምስል DW/Tesfalem Waldyes

"አንድ ለአምስት የሚባለውን መዋቅር ጨምሮ ድርጅቱ በጣም ግዙፍ የበላይ ጠቅላላ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦችን ሁለንተናዊ ሕይወት እንዲቆጣጠር የሚያስችል መዋቅር በመዘርጋት የሚታወቁ ናቸው አቶ በረከት።  ያልተማሩ እና በደንብ ያልሰለጠኑ የክልል የፖለቲካ ካድሬዎችን በመንግሥት መዋቅሮች ውስጥ በመሰግሰግ ግንባር ቀደም ሚና የነበራቸው ናቸው።"

ኢሕአዴግ በፖለቲካዊ ተቃውሞ በሚናጥበት ባሁኑ ወቅት አንጋፋዉ ፖለቲከኛ ሥልጣን ለመልቀቅ መወሰናቸዉን አቶ ያሬድ በበጎ አይን አላዩትም። የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከሩቅ ሆነው የሚታዘቡት አቶ ያሬድ አቶ በረከት በኢሕአዴግ ውስጥ ያለውን የኃይል ሚዛን ቢያመጣጥኑ የተሻለ ነበር የሚል እምነት አላቸው።

አቶ በረከት ከፖለቲካዊ ተሳትፏቸው ሙሉ በሙሉ ገለል ይበሉ አሊያም በብአዴን አባልነታቸው ይቀጥሉ ለጊዜው የታወቀ ነገር የለም።

እሸቴ በቀለ

ኂሩት መለሰ