1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአውሮጳ ምክር ቤት ጥሪ እና የኢትዮጵያ እምቢታ

ዓርብ፣ ግንቦት 11 2009

የኢትዮጵያ መንግሥት ተቃዋሚ ፓርቲ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) መሪ ዶ/ር መረራ ጉዲና በአስቸኳይ ከእስር እንዲፈቱ የአዉሮጳ ሕብረት ምክር ቤት ጥሪ አቀረበ። የኢትዮጵያ መንግሥት ጥሪውን አልተቀበለም።

https://p.dw.com/p/2dGgF
Dr. Merera Gudina Addis Abeba Äthiopien Oromo Pressekonferenz PK
ምስል DW/Y.Egziabhare

EUP-Resolution Calls for Urgent UN Inquiry Into Protester Deaths and Detention - MP3-Stereo

የኢትዮጵያ መንግሥት ተቃዋሚ ፓርቲ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) መሪ ዶ/ር መረራ ጉዲና በአስቸኳይ ከእስር እንዲፈቱ የአዉሮጳ ሕብረት ምክር ቤት ጥሪ አቀረበ። የኢትዮጵያ መንግሥት ጥሪውን አልተቀበለም። ምክር ቤቱ ትናንት ባጸደቀው የውሳኔ ኃሳብ በኢትዮጵያ ተቃውሞ የተፈጸሙ ግድያዎችን የሚያጣራ የተ.መ.ድ. መራሽ ቡድን ለማቋቋም ፌዴሬካ ሞግሔሪኒ ጥረት እንዲያደርጉ አሳስቧል። 

የአውሮጳ ሕብረት ምክር ቤት በተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ መሪው በዶክተር መረራ ጉዲና ላይ የቀረቡ ክሶችም ውድቅ እንዲደረጉ ጠይቋል። ጥሪው ግን ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ቀና ምላሽ አላገኘም። ለገዢው ፓርቲ ቅርበት ያለው ራዲዮ እንደዘገበው የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒሥቴር የአውሮጳ ፓርላማን ጥሪ «ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለማሳነስ ከመሞከር የዘለለ ፋይዳ» የለውም ብሏል። 

በጉዳዩ ላይ አስተያየት የሰጡ ኢትዮጵያውያን በበኩላቸዉ የአውሮጳ ምክር ቤት ጥሪ የሚፈይደው አንዳች ነገር የለም። የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒሥቴር ምላሽም ውሐ አያነሳም» ይላሉ። የፍሎሪዳው ነዋሪ አብደላ፦ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከአውሮጳ እና አሜሪካ መንግሥታት ድጋፍ መጠበቅ የለበትም ባይ ናቸው።  አቶ አብደላ ከአፍ ያላለፈው የአውሮጳውያኑ ማሳሰቢያ ዋጋ የለውም ባይ ናቸዉ። 
«እውነት የአውሮጳ ኅብረት የዜጎችን ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብት እንዲከበሩ የሚሹ ቢሆን ከኢትዮጵያ መንግስት ጋ በግልፅ በመነጋገርና አቋም በመውሰድ በሳምንታት እድሜ ማስፈታት ይችሉ ነበር» የሚሉት አማን ቢን ያሲር «ከመግለጫነት ያለፈ ጠብ የሚል ነገር የለውም።ህብረቱ እርምጃ የሚወስድባቸውና የማይወስድባቸው መንግስታቶች(አምባገነን መንግስታትን) ከኅብረቱ ጥቅም አንፃር እንጂ ዜጎቻቸውን ስለሚጨቁን በሚል አይደለም» ሲሉ ተችተዋል። ዶ/ር መረራ ጉዲናን ለእስር የዳረጋቸው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያስፈለገው በመንግሥት ጥፋት ነው የሚሉት አስተያየት ሰጪ ደግሞ የተቃዋሚ ፖለቲካ መሪው ጥፋት የለባቸውም ብለዋል። የመንግሥትን ምላሽ «የእቃ እቃ ጨዋታ» ያሉም ኢትዮጵያዊም አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ ሰጥተዋል።

Friedensnobelpreis EU Europäische Union Symbolbild
ምስል Getty Images/AFP

የአውሮጳ ሕብረት ምክር ቤት ትናንት ባፀደቀዉ ሌላ የዉሳኔ ሐሳብ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ከታኅሳስ 2015 ዓ.ም. እስከ ጥቅምት 2016 በኢትዮጵያ በተቀሰቀው ተቃውሞ የተፈጸመው ግድያ እና የጸጥታ ኃይሎች እርምጃ በገለልተኛ ወገን እንዲጣራ በድጋሚ ጥሪ አቅርቧል። ምክር ቤቱ ያጸደቀው የውሳኔ ኃሳብ የአውሮጳ ኅብረት የዉጪ ግንኙነት ኃላፊ ፌዴሬካ ሞግሔሪኒ ግድያዉን የሚያጣራ ገለልተኛ አጣሪ ቡድን እንዲቋቋም ግፊት እንዲያደርጉ ኃሳብ አቅርቧል። ጥረቱን በሚቀጥለው ወር በጄኔቫ በሚካሔደው የሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ እንዲጀምሩም ጠይቋል። 

እሸቴ በቀለ
ነጋሽ መሀመድ