1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሲቪል ማኅበረሰብ ተሳትፎ ወሳኝነት እንደሆነ እየረተነገረ ነዉ፤

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 21 2010

በየዓመቱ የዓለም መንግሥታት በአየር ንብረት ጥበቃ ጉዳይ ለመነጋገር ሲሰባሰቡ መሟላት የሚያስፈልጓቸዉ መሠረታዊ ነገሮች አሉ። ጊዜ፣ ገንዘብ እና ቦታ። የተመድ ከተማ በመባል የምትታወቀዉ የጀርመን ከተማ ቦን በእንግሊዝኛ ምህጻሩ COP 23 በመባል የሚጠቀሰዉን የዘንድሮዉን ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ተመካች ጉባኤ ለማስተናገድ ዝግጅቷን አጠናቃለች።

https://p.dw.com/p/2mpJP
Anfang der Bauarbeit des COP23-Geländes im DW-Hinterhof Bonn
ምስል DW/S. Diehn

25ሺህ ተሳታፊዎች ይጠበቃሉ

 ከሌሎች የጀርመን ትላልቅ ከተሞች ጋር ስትነፃጸር አነስ ብላ የምታተየዉ የቦን ከተማ እጅግም ግርግር አይታይባትም። ከያዝነዉ ሳምንት ማለቂያ ጀምሮ ግን ባላት ከ300 ሺህ የሚበልጥ ነዋሪ ላይ 25 ሺህ የሚሆኑ እንግዶችን ተቀብላ ልታስተናግድ ዝግጅቷን እያጠናቀቀች ነዉ። የከተማዋ አስተዳደር መንገዶችን ከማሳመር አንስቶ፤ ከተለያዩ ሃገራት በአዉሮፕላን ተጉዘዉ ወደቦን በፈጣን አገር አቋራጭ ባቡሮች የሚመጡት እንግዶቿ የስብሰባዉን ቦታ በመፈለግ እንዳይደናገሩ የሚረዳና መንገዳቸዉን የሚያቀልል አዲስ የባቡር ጣቢያ ሳይቀር አዘጋጅቶላታል። ምንም እንኳን በርከት ያለ የዉጭ ሀገር ዜጋን ዶቼ ቬለን እና የተመድን ጨምሮ ባሏት ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ምክንያት ያሰባሰበችዉ ቦን ለእንግዶች እጅግም እንግዳ ባትሆንም፤ በአየር ንብረቱ ጉባኤ ሳቢያ ግን ያ የተለመደዉ ፀጥታዋ ደፍረስ ማለቱ እንደማይቀር ይገመታል።

ፓሪስ ፈረንሳይ ላይ ከሁለት ዓመታት በፊት አየር ንብረት ለዉጥን ሊገታ ይችላል የተባለ ዉል የፈረሙት 196 ሃገራት በሁለት ሳምንታት ቆይታቸዉ፤ ዉሉን ተግባራዊ ሊያደርጉ የሚያስሉ ተጨባጭ እና ወሳኝ ስምምነቶችን ይቋጫሉ የሚል ተስፋ አለ። እንደአስተናጋጅነቷ ጀርመን ለጉባኤዉ አስፈላጊዉን ሁሉ ለማመቻቸት 117 ሚሊየን ዮሮ መመደቧ ተሰምቷል። የጉባኤዉ አዳራሽ እና አስተባባሪዉ መሥሪያ ቤት የተመድ የሚገኘዉ ከራይን ወንዝ ዳርቻ እንደመሆኑ ለክፉም ለደጉም ተብሎ ተንሳፋሪ የጎርፍ መከላከያ ለመገንባት 2 ሚሊየን ዮሮ አዉጥታለች። ይህ ሁሉ እንግዲሁ ለ2 ሳምንቱ የተመድ የአየር ንብረት ተመልካች ጉባኤ ተብሎ የተሰናዳ ነዉ። ተሳታፊዎች በቡድን በቡድን ሆነዉ የተለያዩ ጉባኤዎችን የሚያካሂዱባቸዉ በድንኳን የተዘጋጁት የመስክ ላይ መሰብሰቢያ አዳራሾች ስምንት የእግር ኳስ ሜዳዎች በአንድ ላይ ሲቀናጁ የሚይዙትን ስፋት በሚሆን ስፍራ ላይ አስፈላጊዉ የሙቀትም ሆነ የማቀዝቀዣ ስልቶች ተገልጥመዉላቸዉ በብርሃን ደምቀዉ ዝግጅታቸዉን ተጠናቆ ጉባያተኛዉን ሲጠባበቁ ከዶቼ ቬለ ሕንጻ በስተጀርባ ይታያሉ።

Bauarbeit des COP23-Geländes im DW-Hinterhof Bonn
የመሰብሰቢያዉ መንደር ከርቀት ይህን ይመስላል፤ ምስል DW/S.Diehn

ዝግጅቱ ከፍተኛ ገንዘብ ፈሶበት እና በዚህ መልኩ ተጠናቆ ተሰብሳቢዎችን ከጥቅምት 27 እስከ ኅዳር 8 2010ዓ,ም ድረስ ለማስተናገድ በሚጠብቀዉ የአየር ንብረት ጉባኤ ሁለት አበይት ጉዳዮች ይጠበቃሉ። አንደኛዉ በፕሬዝደንትነት መመረጣቸዉን እንኳን ሳያረጋግጡ «የአየር ንብረት ለዉጥ የሚባል የለም»  በሚል ሀገራቸዉ ከፈረመችዉ የፓሪስ ዉል እንድትወጣ አደርጋለሁ በማለት የፎከሩትን በተግባር የፈፀሙት የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ዉሳኔ እስከምን ድረስ ይሄዳል የሚለዉ ሲሆን፤ ሌላኛዉ ደግሞ የአየር ንብረት ለዉጥ ጉዳይ ተደራዳሪዎች ፓሪስ ላይ የተደረሰዉን ስምምነት ወደተግባር መለወጥ የሚያስችል ዝርዝር መመሪያ ያዘጋጃሉ የሚለዉ ተስፋ ነዉ። እንደታሰበዉ ይህ መመሪያ በዚህ የጉባኤ ወቅት ከተጠናቀቀም በመጪዉ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 2018 ፖላንድ በምታስተናግደዉ ተመሳሳይ የአየር ንብረት ተመልካች ጉባኤ ላይ እንዲጸድቅ ይጠበቃል።

በአየር ንብረት ለዉጥ ጉዳይ ሃገራት እየተሰባሰቡ ሲመክሩ በርካታ ዓመታት እንደዋዛ ነጉደዋል።  ዘንድሮም ዉይይቱ ይቀጥላል። ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ወገኖች ከዘንድሮዉ ስብሰባ እና ዉይይት አንዳች ተጨባች ነገር ጠብ ሊል ይገባል የሚል አስተያየታቸዉን ይሰነዝራሉ። እንዲያም ሆኖ በተለይ የአየር ንብረት ለዉጡ በገሃድ እየጎዳቸዉ እና ለአደጋ እያጋለጣቸዉ የሚገኙ የደሴት ሃገራት በዚህ ጉባኤ የሌሎቹን ሃገራት ትኩረት ለመሳብ የመድረኩ አስተናባሪነቱን ይዘዋል። የCOP 23 ጉባኤ ዋነኛ አጋፋሪ ፊጂ ደሴት ናት። የፊጂ ጠቅላይ ሚኒስትር ፍራንክ ባይኒማራማ፤ ለችግሩ በጣም የተጋለጡት ድምፃቸዉ ሊሰማ እንደሚገባ ከወዲሁ አሳስበዋል። በመጨረሻ ማንም ቢሆን ከአየር ንብረት ለዉጥ መዘዝ ማምለጥ እንደማይችል ሁላችንም በጋራ ለመላዉ ዓለም ድምፃችንን እናሰማ የሚል ጥሪም አቅርበዋል።  

UN-Klimakonferenz 2017 in Bonn | Aufbau
የCOP23 አጋፋሪ ፊጂ፤ምስል picture-alliance/dpa/R. Vennenbernd

የሲቪል ማኅበረሰብ ተሳትፎ ወሳኝነት

እየጨመረ መሄዱ የሚነገርለትን የዓለም የሙቀት መጠንን ያህል ግዙፍ ጉዳይ በተግባር ለመቆጣጠርም ሆነ ለመቀነስ በየቀየዉ የሚደረገዉ  እያንዳንዱ ጥቃቅን ርምጃ ትልቅ ሚና እንደሚኖረዉ ነዉ ምሁራን የሚናገሩት። ለዚህ ደግሞ የግድ ዓለም አቀፍ አካላት ሳይሆኑ የየአካባቢዉ ባለስልጣናት ቁልፍ ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ እያሉ ነዉ። የዘንድሮዉ ጉባኤ ዉጤት እንዲያመጣ ከተፈለገም ለዚህ ልዩ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ በጀርመን የራይን ቬስትፋለን ግዛት በአካባቢ ዘላቂነት ላይ የሚሠራ ቡድን ባልደረባ ሞሪትስ ሽሚት ይናገራሉ።

«በእኔ እምነት የእስከ ዛሬዉ የአየር ንብረት ጉባኤ ታሪክ የዚህ ጉዳይ ተዋናዮች መንግሥታት ብቻ መሆን እንደሌለባቸዉ ፤ ይልቁንም ማኅበረሰቡ እና ሲቪል ማኅበራት ተገቢዉን ግፍት ማድረግ እንደሚኖርባቸዉ በግልፅ አሳይቷል።  የአየር ንብረት ለዉጥን የመቋቋም እና ከለዉጡ ጋር ተላምዶ የመኖሩ ርምጃ ባጠቃላይ ተግባራዊ የሚሆነዉ በየአካባቢዉ ማኅበረሰብ ደረጃ ነዉ፤ ስለዚህም እነዚህ እጅግ አስፈላጊ ተዋናዮች ተገቢዉ ነገር ሁሉ ሊቀርብላቸዉ ይገባል ብዬ አስባለሁ።»

ለዚህም ደግሞ ሽሚት እና የእሳቸዉ ቡድን እንደኒካራጓ እና ፔሩ ካሉ ሃገራት ሲቪል ማኅበረብ ጋር ሊደረግ የሚገባዉን የአየር ንብረት ትብብር እንቅስቃሴን የሚመለከት እቅዳቸዉን የሁለት ሳምንቱ ጉባኤ ከመጠናቀቁ አስቀድመዉ ይፋ ለማድረግ ዝግጅታቸዉን አጠናቀዋል። በእሳቸዉ እምነትም በየሀገራቱ የሚገኙ ሲቪል ማኅበራት እንዲህ ላለዉ ተሳትፎ በፈቃደኝነት እየተንቀሳቀሱ ነዉ። የዓለማችንን የአየር ንብረት ለዉጥ ለመቆጣጠር የሚደረገዉ ዉይይት እና እንቅስቃሴ ሁሉ በከባቢ አየር ዉስጥ ሙቀትን የሚያምቁ ጋዞች አንዳች መፍትሄ ካልተፈጠረላቸዉ ዋጋ እንደሌለዉ የሚናገሩት በርካቶች ናቸዉ። የመሬት ወዳጆች ወይም ፍሬንድስ ኦፍ አርዝ የሚባለዉ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት በጀርመን የኖርድ ራይን ቬስትፋለን የአካባቢ እና የተፈጥሮ ጥበቃ ፖሊሲ ኃላፊ ድሪክ ያንሰን ግን ቁርጥ ያለዉን ነዉ የሚናገሩት። ለዚህም አዉሮጳን በCO2 ክፉኛ በመበከል የሚወቀሰዉ የድንጋይ ከሰል ማዕድን ጥቅም መገታት አለበት ባይ ናቸዉ። ለዚህ ደግሞ ቅዳሜ ዕለት የሚካሄደዉን ከሰል መታገድ አለበት በሚሉ የአካባቢ ተፈጥሮ ተሟጋቾች ሰልፍ ይካፈላሉ።

Deutschland Baustelle Klimakonferenz COP23 in Bonn
የመስበስቢያ ጊዜያዊ ድንኳኖቹ፤ምስል DW/H. Weise

«ሰልፍ የምንፈወጣዉ በፍጥነት እና ሙሉ በሙሉ ከሰልን ከሥራ ዉጭ የሚያደርግ ዉሳኔ እንዲተላለፍ ነዉ፤ ይህን ማድረግ ካልተቻለ ግን ጀርመን የአየር ንብረት ጥበቃ ግቧን ትስታለች ማለት ነዉ። በዚያም ላይ ለመጪዉ የተመድ የዓለም የአየር ንብረት ለዉጥ ጉባኤ የክስረት ምልክት ነዉ። ከሰልን ያላስወገደ የአየር ንብረት ጥበቃ እዉን ሊሆን አይችልም።»

የያንሰን ዋና መከራከሪያ ደግሞ ባለፈዉ  ፓሪስ ላይ መንግሥታት በየግላቸዉ የሚቀንሱትን የበካይ ጋዝ መጠን ለመወሰን መስማማታቸዉ ነዉ። እስከዛሬ መንግሥታት በዚሁ ጉዳይ ሲወያዩ እና አማራጩን ሲያመቻቹ መሰንበታቸዉን በማስታወስም አሁን የተግባር ጊዜ ነዉ በማለት ይከራከራሉ።

«ጉባኤዉ የሚካሄድበት የቦኑ የመሰብሰቢያ ስፍራ በአዉሮጳ ከፍተኛዉን CO2 የሚያመነጨዉ ማለትም የራይኑ የድንጋይ ከሰል ማዕድን ከሚገኝበት ጥቂት ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ ነዉ። ይህ ስፍራ ደግሞ የጀርመን የካርቦን ብክለት የሚታይበት አይነተኛ ስፍራ ነዉ። እናም የጋለ አየር እና የሞቁ ቃላት ከበቂ በላይ ተሰምቷል አሁን ተግባር መከተል ይኖርበታል።»

ተግባራዊ ርምጃዎች የሚጠይቁ ተቃዋሚዎች እና የጉባኤዉ አስተባባሪዎች በአንድ ነገር ይስማማሉ። ይህም COP 23 በሚል በአጭር ምህጻረ ቃል የተሰየመዉ የባለ ድርሻዎች ጉባኤ፤ ለአየር ንብረት ለዉጥ መቀልበሻ ለሚደረገዉ ትግል የመጨረሻዉ እና ወሳኙ መድረክ ነዉ ባይ ናቸዉ። ይህ ግዙፍ ጉባኤ ለማስተናገድ ጀርመን ያወጣችዉ ወጪ ሁሉ ተገቢ እንደሆነ የሚያምኑት ያንሰን ይህ ሁሉ የሆነዉ ደግሞ ስለሰብዓዊ ፍጥረት ሕልዉና ሲባል እንደሆነ ያስረዳሉ።

Deutschland Baustelle Klimakonferenz COP23 in Bonn
የመሰብሰቢያ ድንኳኖቹ መግቢያ፣ምስል DW/H. Weise

«እንዲህ ያሉት ጉባኤዎች እጅግ ስፈላጊዎች ናቸዉ፤ አስፈላጊነታቸዉ ደግሞ ለአየር ንብረቱ ፍትሃዊ የሆነ ዉጤት ለማስገኘት ብቻ ሳይሆን ለመላዉ ሰብዓዊ ፍጥረት ሕልዉና ነዉ። ይህንን ኃላፊነት እዉን ለማድረግ ደግሞ በእንደዚህ ያሉ ተግባራት ጥረቱ ሊገለጥ ይገባል።»

ምድር ከዕለት ወደዕለት እየሞቀች ብቻ ሳይሆን እየጋለች መሄዷን የሚጠቁሙ በርካታ ምልክቶች መታየት መጀመራቸዉን የዘርፉ ባለሙያዎች እየጠቆሙ ነዉ። እነሱ ከሚናገሩት በዘለለ ደግሞ ተፈጥሮ በራሷ ትንቢቱን ሁሉ እዉን እያደረገችዉ መጥታለች። በዘንድሮዉ የሰሜን ንፍቀ ክበብ የበጋ ወራት ደቡብ አዉሮጳ ፤ እስያ እና ዩናይትድ ስቴትስ ዉስጥ የዘሩት በሙቀት ማዕበል ምክንያት የተጎዳባቸዉ ገበሬዎች የዚህ ሕያዉ ምስክሮች ናቸዉ። የየሃኪም ቤቱ ሠራተኞችም በሙቀት ጤናቸዉ የተቃወሱ ሕሙማንን ሲያስተናግዱ ስለሰነበቱ በእማኝነት ይጠራሉ። ከምንም በላይ ደግሞ  ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በየጊዜዉ በሰደድ እሳት ቤት ደቡባዊ አዉሮጳ እና አሜሪካን ዉስጥ ንብረታቸዉን የሚያጡት ደግሞ ለረዥም ጊዜ ሲያስተዉሉት እንደቆዩ ይታመናል። በተቃራኒዉ በካሬቢያን እና በሜክስኮ ተደጋጋም ማዕበል እና ወጀብ የተፈጥሮን ጉልበት እያሳየ ነዉ። አፍሪቃም ቢሆን በተራዘመዉ ድርቅ በሚሊየኖች የሚቆጠሩት ለርሃብ መጋለጣቸዉ እየተነገረ ነዉ። ይህ ሁሉ በአየር ንብረት ለዉጥ ምክንያት የተባባሰ ችግር መሆኑን ሳይቲስቶች የሚያሳስቡት።

ለየት ያለ ጉባኤ እንዲሆን ታስቧል፤

 

በምዕራቡ ዓለም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚካሄዱ ጉባኤዎች ከፍተኛ ተቃዉሞዎችን ከጎናቸዉ ሲያስተናግዱ ይስተዋላል። ይህን የሚያዉቁት የቦን ከተማ ነዋሪዎችም ከወዲሁ ባለፈዉ ለቡድን 20 ጉባኤ ሃምበርግ ላይ የታየዉ አይነት ትርምስ ከተማዋ ላይ ይከሰታል የሚል ስጋት እንዳደረባቸዉ ነዉ የሚነገረዉ። እስካሁን ባለዉ መረጃ መሠረት የቦን ከተማ በዚሁ በአየር ንብረት ተመልካች ጉባኤዉ ምክንያት ከፊታችን ቅዳሜ አንስቶ በተያየዘላቸዉ ቀጠሮ መሰረት የተቃዉሞ ሰልፎችን ታስተናግዳለች። ቅዳሜ ዕለት የከሰል ማዕድንን መጠቀም እንዲቆም፤ የሚጠይቀዉ ሰልፍ እሁድም 1 ሺህ ተሳታፊዎችን አካቶ ይቀጥላል።  ኅዳር 2 ደግሞ «የአየር ንብረት ለዉጥ የሚባል የለም የሚሉ ሰላማዊ ሰልፍ ጠርተዋል። ሁለቱ ተፃራሪ እንደመሆናቸዉ አንዱ ሌላዉን እንዳያዉክ ፖሊስ ከፍተኛ ሥራ ይጠብቀዋል።

Deutschland Köln - Enregiewende / Kohleausstieg
ጀርመን ዉስጥ ድንጋይ ከሰልን መቃወሙ የቆየ ነዉ፤ምስል DW/G. Rueter

 እርግጥ ነዉ በከተማዋ የጉባኤዉ ዝግጅት አስተባባሪዎች ስብሰባዉ በተሳካ ሁኔታ ተካሂዶ እንዲጠናቀቅ የምንችለዉን ሁሉ አድርገናል ብለዉ ሲናገሩ ቢደመጥም፤ አሁንም ግን ቦን ከተማ ይህን ግዙፍ ጉባኤ ማስተናጋዱ ይሳካላት ይሆን የሚል ጥያቄያቸዉን የሚጠይቁ አልጠፉም። የሚሆን 25ሺዎቹ ተሰብሳቢዎች ለሁለት ሳምንታት ምግብ እና ማደሪያ ብቻ ሳይሆን በቂ መጓጓዣም ያስፈልጋቸዋል።  ቦን ዉስጥ ያሉት 9,000 የሆቴል አልጋዎች ለዚህ በቂ ባለመሆናቸዉም ተሳታፊዎች ማደሪያቸዉን እንደ ኮሎኝ እና ኮብለዝ ባሉ ከተሞች ማድረግ ግድ ሆኖባቸዋል። እነዚህ ሁሉ ለማዘጋጀት የጉባኤዉ ዝግጅት አስተባባሪዎች 11 ወራት ብቻ ነበራቸዉ። በተመድ የአየር ንብረት ስምምነት ማዕቀፍ UNFCCC ባልደረባ ኒክ ኑታል የዘንድሮዉ ጉባኤ ከየትኛዉም ተመሳሳይ ስብሰባ «አረንጓዴ» እና የተለየ ነዉ ይሉታል። 

«በምንችለዉ ሁሉ እጅግ የተለየ እና ተደርጎ የማያዉቅ አረንጓዴ የአየር ንብረት ተመልካች ጉባኤ እንዲሆን ከፍተኛ ጥረት አድርገናል።»

ከብክለት ነፃ የሆኑ የመጓጓዣ ስልቶች፣ የእንስሳት ተዋፅኦ የሌለበት የምግብ አቅርቦት፤ ሌላዉ ቀርቶ ወረቀቶች የማይታተሙበት እንደሆነ የሚነገርለት ይህ ጉባኤ በተመሳሳይ ለተካሄዱ ስብሰባዎች ሁሉ መልካም አርአያ ለመሆን ተዘጋጅቷል።  ጀርመኖች ለተፈጥሮ በሚያሳዩት ጥንቃቄ እና ክብካቤ ከመሰሎቻቸዉ ለየት የሚሉበትን ልማዳቸዉን በዚህ አጋጣሚ ለማሳየት የሚሞክሩ መስለዋል። ይሳካላቸዉ።

ሸዋዬ ለገሠ

ማንተጋፍቶት ስለሺ