1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ተፅእኖ እና ትኩረት ከኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ አንጻር 

ቅዳሜ፣ ጥር 28 2014

የትልቁ አህጉራዊ ድርጅት የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ እንደ ሌላው ዓለም ቃጣናዊ እና አህጉራዊ ድርጅቶች የዓለም ትኩረት ሲስብ አይስተዋልም፡፡ ሕብረቱ የራስን አጀንዳ ከማቀድ እና ከመፈጸም አንጻር የሚያጋጥመው ተግዳሮት ብሎም አባል አገራቱ ውሳኔዎቻቸውን ከመተግበር አንጻር የሚያሳዩት ውስንነቶች የህብረቱን አቅም ከተፈታተኑ ጉዳዮች ተጠቃሽ ነው፡፡

https://p.dw.com/p/46ZyH
Addis Abeba Treffen Africa Union | Impressionen aus der Stadt
ምስል Seyoum Getu/DW

የአፍሪቃ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ ከኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ አንጻር

 

በአፍሪካ ትልቁ አህጉራዊ ድርጅት የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ እንደ ሌላው ዓለም ቃጣናዊ እና አህጉራዊ ድርጅቶች የዓለም ትኩት ሲስብ አይስተዋልም፡፡

ህብረቱ የራስን አጀንዳ በራስ መፈጸም እና ማቀድ ላይ ከበጀት ጀምሮ የሚያጋጥመው ተግዳሮት ብሎም የህብረቱ አባል አገራት ውሳኔዎቻቸውን አክበረው መተግበር ላይ የሚያሳዩት ውስንነቶች ህብረቱን ትኩረት ከነፈጉት ይባላል፡፡

Addis Abeba Treffen Africa Union | Impressionen aus der Stadt
ምስል Seyoum Getu/DW

አንድ የአፍሪካ ጉዳዮች ተንታኝ ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት የህብረቱ ዋና ትኩረት አባል አገራቱ ከተፅእኖ ተላቀው የእርሰበርስ ትስስር ማጠናከር ላይ መሆን ይኖርበታል ብለዋል፡፡

ልክ የዛሬ 3 ወራት ገደማ ነዋሪነታቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ የምዕራባውያን ዲፕሎማቶች በኤምባሲዎቻቸው በሚሰጡ የደህንነት ስጋቶች በገፍ መዲናይቱን ተሰናብተው የተሻለ ሰላም አለ ወዳሉት ሌሎች ከተሞች ሲጎርፉ ነበር፡፡ በዚህ እያገባደድን ባለው ሳምንት ግን የሆነው በተቃራኒው ነው፡፡ የተለያዩ አገራትን የወከሉ ልዑካን 55 አባል አገራት ላለው የአፍሪካ ህብረት 35ኛ ጉባኤ ሲተሙ ነው የሰነበቱት፡፡

Addis Abeba Treffen Africa Union | Impressionen aus der Stadt
ምስል Seyoum Getu/DW

በሰሜን አሁንም ጦርነት ያላቧራባት ኢትዮጵያ የፀጥታ ስጋት ሰብራ ከሁለት ዓመታት በኋላ በጉጉት ስትጠብቀው የነበረውን የህብረቱን ጉባኤ ማስተናገዷ በእርግጥም በአሸናፊነትና በአድናቆት ተነስቷል፡፡ በአዲስ አበባ የኒቨርሲቲ መምህርና የአፍሪካ ጉዳዮች ተንታኝ ዶ/ር ሳሙኤል ተፈራ ለዶይቼ ቬለ በሰጡት ቃለ ምልልስ የዘንድሮ የህብረቱ ስብሰባ ከወትሮ በተለየ የበርካታ አገራትና አህጉራት መገናኛ ብዙሃን ትኩረትንም የሳበ ብለውታል፡፡ 

እንደ ዶ/ር ሳሙኤል ማብራሪያ አፍሪካ የተለያዩ የፖለቲካ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን አንስቶ አቅም ያለው የመገናኛ ብዙሃን ድርጅቶችም የላትም፡፡ ህብረቱ እና የህብረቱ ጉባኤም ቢሆን እንደ ሌላው አህጉራዊ ድርጅቶች አህጉር ተሻጋሪ አጓጊ ውሳኔዎች የሚተላለፉበት አለመሆኑ ትኩረት ሳቢነቱን አነስ እንዲል አድርጎታልም ባይ ናቸው፡፡ የዘንድሮው የህብረቱ 35ኛ የመሪዎች ጉባኤ የምዕራባውያን በአፍሪካ ጉዳዮች ጣልቃ መግባትን የሚተቸው የሃሽታግ ኖሞር እንቅስቃሴ አገራትን ባዳረሰበት ወቅት መደረጉ በተወሰነ መልኩ እንዳነቃውም ተብራርቷል፡፡ 

Addis Abeba Treffen Africa Union | Impressionen aus der Stadt
ምስል Seyoum Getu/DW

ህብረቱ በበጀት ውስንነት የራስን አጀንዳ መቅረጽ እና ማስፈጸም ላይ ሁሌም ተግዳሮት እንደሚገጥመውም የአፍሪካ ጉዳዮች አጥኚ እና ተንታኝ ዶ/ር ሳሙኤል ተፈራ አመልክተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ዛሬ በተጀመረው የህብረቱ አባል አገራት የመሪዎች ጉባኤ ከዚህ ቀደም የሴኔጋል፣ ደቡብ አፍሪካ እና ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የወቅቱ መሪዎች ያነሱት የአፍሪካ የተመድ ፀጥታ ምክር ቤት ተሳትፎ እና የጠንካራ አፍሪካዊ መገናኛ ብዙሃን መቋቋምን አስፈላጊነት በአጽዕኖት አንስተዋል፡፡