1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሙዚቃ

የኢትዮጵያ መለያው የሙዚቃ ቅኝት

እሑድ፣ ግንቦት 12 2010

በአንዳንዶች ዘንድ እንደ “ኢትዮጵያ መለያ”  ይወሰዳል። ሌሎች ኢትዮጵያዊነትን ገላጭ ሲሉ ያሞካሹታል። የተወሰኑ ሙዚቀኞች ሀገርኛ ቀለሙን ይበልጥ ለማጎላት “የዶሮ ወጥ ቅኝት” ይሉታል - አንቺ ሆዬ የሙዚቃ ቅኝትን። 

https://p.dw.com/p/2y2ge
Symbolbild Retro Notenblätter
ምስል Colourbox

አንቺ ሆዬ የሙዚቃ ቅኝት

ኩኩ ሰብስቤ አስናቀች ወርቁ የሺ ደመላሽ። እነዚህ የሶስት ዘመን ወካይ እንስት ድምጻውያን በአንድ የሙዚቃ ስልት የተቀነቀኑ የየራሳቸውን ሙዚቃዎች አዜመዋል። ኩኩ “ጉብልዬ” እያለች ስትጣራ አስናቀች በክራሯ ታጅባ “አቤት አቤት” ጥያቄዋን ለፈጣሪዋ አሰምታለች። የሺ በበኩሏ ኮከብ ስትል ታሞግሳለች። 

ሶስቱም ድምጻውያን የተጠቀሙበት ስልት በአንዳንዶች ዘንድ እንደ “ኢትዮጵያ መለያ” ይወሰዳል። ሌሎች ኢትዮጵያዊነትን ገላጭ ሲሉ ያሞካሹታል። የተወሰኑ ሙዚቀኞች ሀገርኛ ቀለሙን ይበልጥ ለማጎላት “የዶሮ ወጥ ቅኝት” ይሉታል - አንቺ ሆዬ የሙዚቃ ቅኝትን። 

ብሌን ዮሴፍ የያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ምሩቅ እና የሙዚቃ ባለሙያ ናት። አንቺ ሆዬ ቅኝትን ታስተዋውቃለች። ስልቱ ለመንፈሳዊ አገልግሎት እንደሚውል የምትናገረው ብሌን ለዚህም በምሳሌነት ዘለሰኛን ትጠቅሳለች። ወጣቱ ፒያኒስት ሳሙኤል ይርጋ የአንቺ ሆዬ ቅኝት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በሚገባ አገልግሎት ላይ መዋሉን ይስማማል።የሙዚቃ ባለሙያዋ አንቺ ሆዬ ከመንፈሳዊ ዜማዎችና መዝሙሮች ባሻገር በዓለማዊ ዘፈኖችም ብዙ ቦታ አለው ትላለች። ከኢትዮጵያዊ ሌሎች ቅኝቶች የሚለየውንም ታብራራለች። ብሌን የቅኝቱ አካሄድ ለሙዚቀኞች ከባድ እንደሆነ የታዘበችውን ተንተርሳ ትገልጻለች። ፒያኒስቱ ሳሙኤል አንቺ ሆዬ ለምን ከባድ ነው እንደሚባል ተጨማሪ ትንታኔ አለው። 

Äthiopien Viva con Aqua Auftritt Clueso und Samuel Yirga in Addis Abeba
ምስል Christoph Köstlin für Viva con Agua

ኢትዮጵያዊ ያልሆኑ የሙዚቃ ሰዎች አንቺ ሆዬ ቅኝትን ለመጫወት ይፈተናሉ። በኢትዮጵያውያም አጨዋወት እና የቅኝት አጠቃቀም ይገረማሉ። የቅኝቱ አካሄድ ይበልጥ ምቹ የሚሆነው ለአስፈሪ ፊልሞች ማጀቢያ መሆኑን አንስተው ኢትዮጵያውያን ለተቃራኒ አገልግሎቶች መዋላቸው እንደሚያስደንቃቸው ብሌንም ሆነች ሳሙኤል ታዝበዋል። የውጭዎቹ ሰዎች የሚደመሙት እነርሱ ከሚያስቡት በተቃራኒ ለመፈንሳዊ ዜማዎች እና ለሰርግ ዘፈኖች በመዋሉ ነው።

ሳሙኤል በአንቺ ሆዬ ቅኝት ሙዚቃዎች ለመጫወት እንደማይከብደው ይናገራል። ጉዞ በተሰኘው አልበሙም በዚሁ ቅኝት ስር ያለ “ፊርማ እና ወረቀት” የተሰኘ ቅንብሩን አካትቷል። 

ሙሉ ዝግጅቱን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ። 

ተስፋለም ወልደየስ