1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

የኢትዮጵያ ምጣኔ ሐብት አለመረጋጋትን መሸከም ይችላል?

ረቡዕ፣ የካቲት 21 2010

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ዛሬም ያልፈታቸው በርካታ ፈተናዎች ከፊቱ ተጋርጠዋል። የቀጣዩ ጠቅላይ ምኒስትር ማንነት አልታወቀም፤ ሕዝባዊ ተቃውሞዉ አሁንም አልበረደም። እነዚህ ኩነቶች በኢትዮጵያ ኤኮኖሚ ላይ ብዥታን ፈጥረዋል። የኤኮኖሚ ባለሙያዎች የአገሪቱ ምጣኔ እንቅስቃሴ ሐብት ይበልጥ ሊቀዛቀዝ ይችላል የሚል ስጋት አላቸው።

https://p.dw.com/p/2tU2B
Stadt Dire Dawa in Äthiopien
ምስል Hailegzi Mehari

የኢትዮጵያ ፖለቲካ አለመረጋጋትና ኤኮኖሚው

ጠቅላይ ምኒስትሩ ስልጣን ለመልቀቅ መወሰናቸውን ካሳወቁ እና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከተደነገገ በኋላ በገዢው ግንባር አባል ፓርቲዎች ዘንድ አለ የሚባለው ልዩነት እያደገ መምጣቱን የሚጠቁሙ ምልክቶች ታይተዋል። ገዢው ግንባር የገጠመው ተቃውሞ መልኩን ይቀይር እንደሁ እንጂ መቋጫ አላገኘም። በሰፋፊ የመሠረተ-ልማት ግንባታዎች የሚንደረደረው የኢትዮጵያ ምጣኔ ሐብታዊ ዕድገት ዓለም ባንክን በመሳሰሉ ተቋማት ቢወደስም አሁንም ያልፈታቸው በርካታ ጥያቄዎች አሉ። የአገሪቱ ምጣኔ ሐብት ላለፉት ሶስት  አመታት ገዢውን ግንባር በተገዳደረው ሕዝባዊ ተቃውሞ ሁነኛ ሲፈተን ቆይቷል።

"ለረጅም አመታት የተከማቹ የልማት ጥያቄዎች ያሉበት ኤኮኖሚ ነው። ያለፉት 13 አመታት እድገት የራሱን ለውጦች ማድረግ ቢችልም የኤኮኖሚ እድገቱ መምጣት ከቻለ የሚፈታቸው ብዙ የተከማቹ የልማት ጥያቄዎች አሉ።" የሚሉት አቶ ጌታቸው ተክለማርያም ናቸው። የኤኮኖሚ ባለሙያው "ለዚህ ኤኮኖሚ ከዚህ በላይ የውሳኔ መስጠት ችግር የፖለቲካ አለመረጋጋት ችግር ይጠቅመዋል ብዬ አላስብም። ከዚህ በላይም የእውነት ኤኮኖሚው መሸከም የሚችል አይመስለኝም" ሲሉ ይናገራሉ።

ባለፉት አስር አመታት ከውጭ አገራት ወደ ኢትዮጵያ የገባው የባለወረቶች ገንዘብ በአምስት እጥፍ ገደማ አድጓል። የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት በጎርጎሮሳዊው 2007/2008 ዓ.ም. 814.6 ሚሊዮን ዶላር የነበረው የውጭ መዋዕለ ንዋይ በ2016/17 ዓ.ም. ወደ 4 ቢሊዮን ዶላር አድጓል። አገሪቱ ከውጭ መዋዕለ-ንዋይ ያገኘችው ገንዘብ በተቃውሞ ሳቢያ መቀዛቀዙ ግን አልቀረም። የተቃውሞ ፖለቲከኛው አቶ ግርማ ሰይፉ የአገሪቱ ፖለቲካዊ ቀውስ የበለጠ ጫና ሊያሳድር እንደሚችል ይናገራሉ። አቶ ግርማ እንደሚሉት አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ የኢትዮጵያ መንግሥት ለውጭ ባለወረቶች ስለመጪው ሁኔታ ማረጋገጫ ማቅረብ ይሳነዋል።

ሙሉ መሰናዶውን ለማድመጥ የድምፅ ማዕቀፉን ይጫኑ

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ