1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
እምነት

የኢትዮጵያ ስም የተወገደበት መጽሐፍ ቅዱስ ክፍል II

ሐሙስ፣ ኅዳር 28 2010

በመጽሐፍ ቅዱስ የተለያዩ ምዕራፎች ለ 45 ጊዜያት ያህል የተጠቀሰው የኢትዮጵያ ስም ተሰርዟል የሚለው የፓስተር በንቲ መርጃ ነው :: ፓስተር በንቲ ኡጅሉ በተለይ ተሻሽሎ የተዘጋጀው አዲሱ መጽሐፍ ቅዱስ የሉተራውያን ዕምነት ተከታዮች እና አብያተ ክርስትያናትን እንዳስደሰታቸው በኦፕራይዱ ድህረ ገጽ ቃለ መጠይቃቸው ገልጸዋል።

https://p.dw.com/p/2oypj
36. Evangelischer Kirchentag Wittenberg
ምስል picture-alliance/dpa/M. Gambarini

የኢትዮጵያ ስም የተወገደበት መጽሐፍ ቅዱስ


የጀርመኑን የፕሮቴስታንት እምነት መሪ የማርቲን ሉረርን የሃይማኖት አብዮት 500ኛ ዓመት ለማዘከር የተዘጋጀዉ አዲስ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም በኢትዮጵያዉያን ዘንድ ማነጋገሩ እንደቀጠለነዉ። የጀርመን የሉተራን ቤተክርስቲያን ያዘጋጀችዉ አዲሱ ትርጉም ኢትዮጵያ የሚለዉን በኩሽ መተካቱ ተነግሯል። ይህ የባህል መድረክ ዝግጅት ባለፈዉ ሳምንት በጉዳዩ ላይ የጀመረዉ ዘገባ ሁለተኛ እና የመጨረሻ ክፍል  ነው።

"ኢትዮጲስ " የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ሳይሆን የጥንት የታሪክና የሥነ ጽሑፍ ጠቢባንም ስያሜውን በተለያዩ ሥራዎቻቸው ውስጥ ጉልህ ቦታን እየሰጡ ሲጠቀሙበት ለመቆየታቸው በተለያዩ አውደ ጥበቦች እና በልዩ ልዩ የታሪክ ጥናቶች የተጠቀሱት መረጃዎች ዛሬም ድረስ ሕያው ምስክር ናቸው ::  ለአብነትም በግሪክ ሥነ ጽሑፍ ታሪክ ትልቅ አድናቆት የተቸረውና ከክርስቶስ ልደት በፊት በ4ተኛው ምዕተ ዓመት መኖሩ የሚነገረው የሥነ ጥበቡ ሊቅ ሄሊኦዶሩስ « ኤትዮፒካ»  ወይም  « የኢትዮጵያውያን ታሪክ » የተባለውን በአንዲት ኢትዮጵያዊት ልዕልትና በጥንታዊቷ ሰሜናዊ ግሪክ ሜቄዶንያ አቅራቢያ በምትገኘው የቴስአሊን ከተማ ልዑል መካከል ያለውን የፍቅር ወግና የጦርነት ገድል የሚተርክ ተወዳጅ የሆነ ድርሰቱን ትቶልን ማለፉን ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ ላይ ያለዉ ታሪኩ ያብራራል ::

በ 440 ዓመተ ዓለም የኖረው የታሩክ ሊቅ ሄሮዶትስም የደቡባዊ ግብጽን የአሁኗን ኢትዮጵያ እና የሱዳንን መልከዓ ምድራዊ አቀማመጥ ጨምሮ ከላይኛው ናይል አካባቢ እስከ ሕንድ ውቅያኖስ የሚኖሩ የቆዳቸው ቀለም የጠቆረ ህዝቦችን በሙሉ « ኢትዮጲስ» በሚል የገለጸበት ቀደምት መረጃዎች መኖራቸውንም ምሁራን ያስረዳሉ :: አሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘው የሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ቀደምት ታሪኮችን, ጥንታዊ ሥልጣኔዎችን እና የባህል ትውፊቶችን የሚያጠናው ማዕከልም " Myths of Africa-Ethiopia" በሚል ርዕስ በድህረ ገጹ ላይ ባሰፈረው ጥናት በ 8ተኛው ምዕተ ዓመት አካባቢ እንደኖረ የሚነገረው ታላቁ የግሪኩ የታሪክ ሊቅ ፈላስፋና ገጣሚ ሆሜር በዓለም አቀፍ ደረጃ ዝናን ባተረፉለት ሁለት የግጥም ስራዎቹ ማለትም በኢሊአድ ሁለት ጊዜ በኦዲሴይ ውስጥ ደግሞ ሶስት ጊዜያት ያህል ስለ ኢትዮጵያውያን እና አማልክቶቻቸው ከብዙ ሺህ ዘመናት በፊት የገለጸባቸው ስንኞች መኖራቸውን ለመገንዘብ ይቻላል ።
«ኢትዮጲስ« « ኩሽ» « ሞህር»" ማለትም ጥቁር ህዝብ እና አዲሱን የጀርመን ሉተራን መጽሃፍ ቅዱስን እንዲሁም የማሻሻያ ለውጦቹን እያነጻጸርን ማቅረብ የጀመርነው የዝግጅታችን ዋና መነሻ በመጽሐፍ ቅዱስ የተለያዩ ምዕራፎች ለ 45 ጊዜያት ያህል የተጠቀሰው የኢትዮጵያ ስም ተሰርዟል የሚለው የፓስተር በንቲ መርጃ ነው :: ፓስተር በንቲ ኡጅሉ በተለይ ተሻሽሎ የተዘጋጀው አዲሱ መጽሐፍ ቅዱስ የሉተራውያን ዕምነት ተከታዮች እና አብያተ ክርስትያናትን እንዳስደሰታቸው በኦፕራይዱ ድህረ ገጽ ቃለ መጠይቃቸው ገልጸዋል። እንዲያም ሆኖ  አብያተ ክርስትያናቱን በስም ዘርዝረው አልገለጿቸውም ::  ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸዉ ፍራንክፈርት ከተማ የሚገኘው ዋናውን የኢትዮጵያ ወንጌላውያ ቤተክርስትያን አመራሮች አንዱ ፓስተር ሽመልስ ገበየሁ በዚህ ላይ አይስማሙም። በሌላ በኩል ጀርመን ኮሎኝ ከተማ የሚገኘው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ የደብረ ሰላም ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስትያን ዋና አስተዳዳሪ የሆኑት ሊቀ ካህናት ዶክተር መርዓዊ ተበጀም በጉዳዩ ላይ ገልጸውልናል :: ሙሉ ቅንብሩን ከድምጽ ዘገባዉ ያድምጡ፤

እንዳልካቸው ፈቃደ

ሸዋዬ ለገሰ

ነጋሽ መሐመድ