1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ በጀትና የቤተ-መንግስት ግንባታ

ማክሰኞ፣ ሰኔ 27 2015

ዛሬ በነበረው ውይይት በጀቱ የመንገድ ሥራዎችን ትኩረት የነፈገ ስለመሆኑ ፣ የመንግሥት ሠራተኞች የደሞዝ ጭማሪ ጉዳይ፣ ገቢ ለመሰብሰብ የሀገሪቱ የሰላም ሁኔታ የደቀነው ሥጋት ፣ የበጀት ፍትሐዊ ክፍፍል ጉዳይ ፣ የጥሬ ገንዘብ እጥረት፣ የኑሮ ውድነትና ሌሎች የኢኮኖሚ ጉዳዮች የተነሱበትና ማብራሪያ የተጠየቀበት ነበር።

https://p.dw.com/p/4TPDQ
Äthiopien Amhara Finance Bureau
ምስል DW/Alemnew Mekonnen

የኢትዮጵያ የ2016 በጀት

 

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እያስገነቡት ነው ስለሚባለው አዲስ ቤተ መንግሥት ምንም አይነት የበጀት ጥያቄ እንዳልቀረበለት የሐገሪቱ የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ። የገንዘብ ሚንስትር አሕመድ ሽዴ መስሪያ ቤታቸዉ ለቤተ-መንግስት ግንባታ በጀት አለመጠየቁን ያስታወቁት  ዛሬ ከተወካዮች ምክር ቤት አባል ለቀረበላቸዉ ጥያቄ በሰጡት መልስ ነዉ።ምክር ቤቱ በ2016 በጀት ላይ በሚነጋገርበት ወቅት ለቤተ-መንግስት ግንባታ ተብሎ የሚሰበሰበው ገንዘብ የመንግሥትን አሠራርና ሕግ ተከትሎ የሚከናወን ስለመሆን አለመሆኑ ሚንስትሩ ተጠይቀዉ ነበር። 
ይህንኑ ፕሮጀክት በተመለከተ የሒሳብ ወጪ እና ገቢው ይመርመር የሚል ጥያቄ ከተነሳ እና መረጃ ከቀረበለት ኦዲት ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት በቅርቡ ለምክር ቤቱ አረጋግጧል። ዛሬ በተደረገው የ2016 በጀት ዝርዝር ውይይት ላይ የቀጣዩ ዓመት በጀት ዋና ዓላማው "የዋጋ ንረት እንዳይስፋፋ መቆጣጠር ፣ የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን ማስቀጠል እና የበጀት ጉድለት እንዳይስፋፋ ማድረግ" መሆኑ ተገልጿል።

ለሀገር ውስጥ እዳ ክፍያ፣ ለተፈናቀሉ ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍና ለመልሶ ማቋቋም እንዲሁም ለማዳበሪያ ግዢ ከፍተኛ ገንዘብ የተያዘበት መሆኑ የተነገረለት የ 2016 ዓ.ም በጀት በአንፃሩ የመከላከያ ሠራዊትንና የዩኒቨርሲቲዎችን ወጪ ትርጉም ባለው መጠን የቀነሰ መሆኑ ተገልጿል። 

Äthiopien, Addis Abeba | Äthiopisches Parlament
ምስል Solomon Muchie/DW

ዛሬ በነበረው ውይይት በጀቱ የመንገድ ሥራዎችን ትኩረት የነፈገ ስለመሆኑ ፣ የመንግሥት ሠራተኞች የደሞዝ ጭማሪ ጉዳይ፣ ገቢ ለመሰብሰብ የሀገሪቱ የሰላም ሁኔታ የደቀነው ሥጋት ፣ የበጀት ፍትሐዊ ክፍፍል ጉዳይ ፣ የጥሬ ገንዘብ እጥረት፣ የኑሮ ውድነትና ሌሎች የኢኮኖሚ ጉዳዮች የተነሱበትና ማብራሪያ የተጠየቀበት ነበር። 

ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ ብዙ ፕሮጀክቶች በበጀት ዝውውር ወይም በመጠባበቂያ በጀት ይሠራሉ ብለዋል።
የደሞዝ ጥያቄ ወደፊት የሚታይ ነው ብለዋል። ቅጥር ከመንግሥት ይልቅ በዋናነት ወደግል ዘርፉ እንዲሆን የመንግሥታቸው ውጥን መሆኑን ፣ የሕዝብና ቤት ቆጠራ ይካሄድ ከተባለ ሀብት ለመመደብ ዝግጁ መሄናቸውን ተናግረዋል። ኢኮኖሚው ያድጋል ተብሎ ስለመተንበዩም ጥያቄ ቀርቦ ምላሽ ሰጥተዋል። 
ዛሬም አነጋጋሪ የነበረው ጉዳይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እያስገነቡት ነው የሚባለው አዲስ ቤተ መንግሥት የገንዘብ ምንጭ እና በመንግሥት የገንዘብ ቋት ውስጥ ሕጋዊ ሆኖ ለምን ቁጥጥር አይደረግበትም የሚለው ነበር።ኢትዮጵያ ብርቱ የበጀት ጉድለት ገጥሟታል

ለ 2016 ዓ.ም ከቀረበው 801.6 ቢሊዮን ብር የወጪ ረቂቅ  በጀት ውስጥ 440 ቢሊዮን ብሩ ከግብር የሚሰበሰብ ሲሆን የ281 ቢሊዮን ብር ጉድለት እንዳለበትም ተገልጿል።
ምክር ቤቱ ሀሙስ ሰኔ 29 ቀን 2015 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተገኝተው ማብራሪያ በሚሰጡበት መደበኛ ጉባኤ ለመጽደቅ ይቀርባል።

ሰለሞን ሙጬ

ነጋሽ መሐመድ

ኂሩት መለሰ