1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስ

የኢትዮጵያ የሳይንስ አካዳሚ ከየት ወዴት?

ረቡዕ፣ የካቲት 15 2009

ሳይንስ በኢትዮጵያ ወደፊት ባሕል ኾኖ መመልከት ዋነኛ ዓላማው ነው፤ የኢትዮጵያ የሳይንስ አካዳሚ። ከተቋቋመ 7 ዓመታት ግድም አስቆጥሯል። ትርፍ ጊዜያቸውን ሰውተው አገልግሎት የሚሰጡ ከ120 በላይ  አባላቶች አሉት። ይኽ በዋናነት በአዲስ አበባ የሚገኝ አካዳሚ በመላ ሀገሪቱ አድማሱን ለማስፋት ፍላጎት አለው።

https://p.dw.com/p/2Y0rm
Hauptcampus der Universität Addis Abeba AAU
ምስል DW

በሰለጠነው ዓለም በሚገኙ ሃገራት የሳይንስ አካዳሚዎች ከበርካታ መቶ ዓመታት በፊትም ይታወቃሉ። ለአብነት ያኽል በቅርቡ የጀርመን ብሔራዊ አካዳሚ ተብሎ የተሰየመው የሌዎፖልዲና የሳይንስ አካዳሚ የተቋቋመው እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1652 ዓመት ነበር። አካዳሚው ከዛሬ 365 ዓመት አንስቶ ያከማቻቸው ሰነዶች በ1,700 ሜትር ስፋት ተንጣለው ይገኛሉ። በተመሳሳይ ዘመን ከጀርመናዊው ሂዮብ ሉዶልፍ ጋር የትዮጵያ ጥናትን ጀርመን ውስጥ በመመስረት ኢትዮጵያዊው ምሁር አባ ጎርጎሪዮስ ይታወሳሉ። በዚያ ዘመን እና ከዚያ በፊት የነበረው የኢትዮጵያውያኑ ምርምር ከየት ተነስቶ የት ደርሷል? ራሱን የቻለ ሰፊ ጥናት ይሻል። የዛሬው ዝግጅታችንም ዋነኛ ትኩረት እሱ አይደለም።

የዛሬው ዝግጅት ማጠንጠኛችን የኢትዮጵያ የሳይንስ አካዳሚ ነው። አካዳሚውን ለመመስረት የመጀመሪያው ብሔራዊ ጉባኤ ከተኪያሄደ ባለፈው ሳምንት ሰኞ የካቲት 6 ቀን 2009 ዓ.ም. ስምንተኛ ዓመት ተቆጥሯል።  አካዳሚው ከየት ተነስቶ የት ደርሷል? የኢትዮጵያ የሳይንስ አካዳሚን በጠቅላላ ጉባኤ ወቅት ተመርጠው ካለፈው ኅዳር ወር አንስቶ ለሦስት ዓመት በፕሬዚዳንት የሚመሩት ፕሮፌሰር ጽጌ ገብረማርያም ናቸው። 

Berliner Sehenswürdigkeiten - Humbold Universität Juristische Fakultät
በርሊን የሚገኘው የሑምቦልድት ዩኒቨርሲቲ ሕንጻምስል picture-alliance/Eibner-Pressefoto

የኢትዮጵያ የሳይንስ አካዳሚ፦  በኅብረተሰቡ ውስጥ ሳይንስ ባሕል ኾኖ እንዲሰርጽ ጥልቅ ምኞት በነበራቸው ጥቂት ሳይንቲስቶች የግል ተነሳሽነት ነው የዛሬ ዐሥር ዓመት ግድም የተጠነሰሰው። ዛሬ አካዳሚው  ከ120 በላይ አባላት አሉት። ከተለያዩ የሥራ መስኮች እና የምርምር ተቋማት የተወሰኑ አባላትን በማዋቀር በኮሚቴ የተጀመረው የሳይንስ አካዳሚ አኹን የሚመራው በፕሬዚዳንት እና በቦርድ አባላት ነው። 

የኢትዮጵያ የሳይንስ አካዳሚ ማንኛውንም የሳይንስ ዘርፍ የሚያቅፍ ነው። «ዛሬ ከሳይንስ ውጪ የሚኾን ነገር የለም» ያሉት ፕሮፌሰር ጽጌ አንድ ተመራማሪ ጥናት እና ምርምር በማከናውን ጥረት ስለማድረጉ በሁለት ታዋቂ ሳይንቲስቶች ተጠቁሞ  መስፈርቱን  ሲያሟላ በጠቅላላ ጉባኤ ምርጫ የአካዳሚው አባል መኾን ይችላል ብለዋል።

የኢትዮጵያ የሳይንስ አካዳሚ የኅብረተሰቡ የኑሮ ኹኔታ አኹን ካለበት ወደተሻለ የኑሮ ደረጃ ተለውጦ ማየት ይሻል።  ሁሉም የሳይንስ ዘርፎች ሳይንሳዊ በኾነ መንገድ አድገው መመልከትም የአካዳሚው ጥልቅ ፍላጎት ነው።

የኢትዮጵያ የሳይንስ አካዳሚ ስድስት የተለያዩ የሥራ ኮሚቴዎች አሉት። እነሱም፦ የጤና፣ የእርሻ፣ የተፈጥሮ ሳይንስ፣ የምህንድስና እና ስነቴክኒክ፣ የማኅበረሰብ ሳይንስ እንዲሁም በቅርቡ የተካተተው ስነ-ጥበብ ናቸው። አካዳሚው የመጀመሪያ ጉባኤውን ያከናወነው የዛሬ 7 ዓመት ግድም ነበር። በጉባኤው የኢትዮጵያ የምርምር ኹኔታ ምን ይመስላል የሚለው አበይት ጥያቄ ተነስቶ በኹሉም የሳይንስ ዘርፎች ፍተሻ ተደርጎ ነበር።  

አካዳሚው የየዕለቱን ሥራ እየተከታተለ የሚያስተገብር አንድ ሥራ አስኪያጅ አለው። ፕሮፌሰር ጽጌ፦ «በጀት ባያግደን ኖሮ በሁሉም የሳይንስ ዘርፎች በሥራ አስኪያጁ ስር ኾነው የሚሠሩ አንዳንድ ተቆጣጣሪ ሥራ አስኪያጆች መመደብ ያስፈልግ ነበር» ብለዋል። 

Professor Tsige Gebre-Mariam
የኢትዮጵያ የሳይንስ አካዳሚ ፕሬዚዳንት፦ ፕሮፌሰር ጽጌ ገብረማርያም ምስል Privat

በዓዋጅ ከተቋቋመ ወዲህ አራት ዓመት ገደማ ያስቆጠረው የኢትዮጵያ የሳይንስ አካዳሚ ከመንግሥት በድጎማ መልክ በየዓመቱ ዐሥር ሚሊዮን ብር ይመደብለታል።  ወደፊት ለሳይንሳዊ ጥናት እና ምርምሩ በቂ ገንዘብ ሲያገኝም ለሁሉም የሳይንስ ዘርፎች ምክትል ሥራ አስኪያጆች መመደብ እንደሚፈልግ አካዳሚው አስታውቋል። የአካዳሚው ተግዳሮት ግን ይኼ ብቻ አይደለም።

የኢትዮጵያ  የሳይንስ አካዳሚ በዓለም አቀፍ አካዳሚዎች እይታ ገና በጨቅላነቱ ሊታይ ይችላል። ኢትዮጵያ ውስጥ ግን በተለይ በባሕላዊ መንገድ የተከናወኑ ምርምሮች  ዘመን ተሻግረው ያለንበት ደርሰዋል። የፍልስፍና፣ ስነ-መለኮት፤ ስነ ከዋክብት፤ ባሕላዊ የዕጽዋት መድሐኒቶች ግኝቶችን የመሳሰሉ ምርምሮች በተለያዩ ጥንታዊ መዛግብት ላይ ሰፍረው ይገኛሉ። የኢትዮጵያ የሳይንስ አካዳሚ ምናልባት በባሕላዊ መንገድ የተሰባሰቡትን ጥናቶች ከዘመናዊው ጋር አስተሳስሮ አንዳች እመርታ ላይ ያደርሳቸውም ይኾናል። 

ማንተጋፍቶት ስለሺ              

አርያም ተክሌ