1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያውያን የባህልና ስፖርት በዓል በፍራንክፈርት

ሐሙስ፣ ግንቦት 16 2010

ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ እና እሁድ ፍራንክፈርት ከተማ የኢትዮ-ጀርመንን የባሕልና ስፖርት በዓል ለማክበር ከመላው ጀርመን በእንግድነት የመጡ ኢትዮጵያውያንን አስተናግዳለች። ሬብሽቶክ ሽፖርትአንላገ በሚባለው ሥታዲየም በተዘጋጀው መሥተንግዶ የብሔር ብሔረሰቦች ባህልና ውዝዋዜ የእግርኳስ ውድድሮች እንዲሁም ልዩ ልዩ አዝናኝ ዝግጅቶች ቀርበዋል።

https://p.dw.com/p/2yFmH
Ethio-German Festival Frankfurt am Main
ምስል DW/E. Fekade

ዝግጅቱ የተጠፋፉ ወገኖች የሚገናኙበት ብቻ አይደለም፤

 በዚሁ ዝግጅት  በርካታ ኢትዮጵያውያን ከአጎራባች የአውሮጳ ሃገራት ጭምር መጥተው ታድመዋል:: የበዓሉ ሞቅ ደመቅ ማለት ልዩ የመነቃቃት ሥሜትን የፈጠረባቸው ኢትዮጵያውያን እና ከተለያዩ ከተሞች የመጡ የእግርኳስ ደጋፊዎች ያሰሙት የነበረው ጭፈራ እና ሆታም የሃገር ቤትን ድባብ ከመፍጠሩም ሌላ ለዝግጅቱም የበለጠ ድምቀትን ሰቶታል ::

የዘንድሮውን የኢትዮ- ጀርመን የሥፖርት እና የባህል ክብረ በዓል ልዩ የሚያደርገው ሥፖርታዊ እንቅስቃሴውን የፍራንክፈርቱ ኢትዮ-አዲስ የስፖርት ክለብ ምግብ እና መስተንግዶውን ለኢትዮጵያውያን ማሕበራዊ እንቅስቃሴ ልዩ ልዩ ድጋፍ የሚያበረክተው አዳብና የኢትዮጵያ የባሕል ሬስቶራንት እንዲሁም የመዝናኛውን ጉዳይ ደግሞ ለረጅም ዓመታት ከሀገር ቤት የሙዚቃ ባለሙያዎችን ወደ ጀርመን እያስመጡ የመድረክ ዝግጅቶችን በማቅረብ የሚታወቁት አቶ አልያስ የማነ በጋራ ያዘጋጁት መሆኑ ነው ::

Äthiopisch-Deutsches Festival Frankfurt 20.05.2018
ምስል DW/E. Fekade

በዚህ የባህል እና ስፖርት በዓል ላይ ከስዊትዘርላንድ ዙሪክ እና ከጎረቤት ኤርትራ በእንግድነት የተጋበዙበት እንዲሁም ከመላው ጀርመን 15 ያህል የእግርኳስ ቡድኖች የተካፈሉበት ውድድርም ከፍተኛ ፉክክር የታየበት ነበር :: ለፍጻሜ የደረሱት ዙሪክ እና ሽቱትጋርት በመደበኛው የውድድር ሰዓት ዜሮ ለ ዜሮ በማጠናቀቃቸው አሸናፊውን ለመለየት በተሰጠው የፍጹም ቅጣት ምት ሽቱትጋርት 5 ለ 4 በሆነ ውጤት አሸንፎ ዋንጫውን ወስዷል :: ከዚህ ሌላ የኮሎኙ እቴሜቴ ኢትዮ-ጀርመን የቤተሰብ እና የባሕል ማሕበር ያሰለጠናቸው ወንድ እና ሴት ሕጻናቶች ያቀረቡት የብሔር ብሔረሰቦች ውዝዋዜ እና የእግርኳስ የሥፖርት ውድድር ተሳትፎም በበዓሉ ታዳሚዎች ዘንድ ከፍተኛ አድናቆት አግኝቷል ::

Ethio-German Festival Frankfurt am Main
ምስል DW/E. Fekade

የበዓሉ ታዳሚዎችም ይህ ዓይነቱ ዝግጅት የተራራቀን ወዳጅ ከማገናኘት እና ከአዝናኝነቱ ባሻገር በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አንድነታቸውን እንዲያጠናክሩ አኩሪ ባሕሎቻቸውን ቅርሶቻቸውን እና ወጎቻቸውንም ጠብቀው ለተተኪው ትውልድ እንዲያስተላልፉ ይረዳል ይላሉ:: በተለይም በውጭ የሚወለዱ ሕጻናት ከደባል ሱሶች ርቀው በሥፖርታዊ የጨዋነት ሥነምግባር እንዲታነጹ ሀገራቸውን እንዲወዱ ብሎም ተሰጥዖ እና ችሎታቸው ለፍሬ እንዲበቃ ትልቅ እገዛ ያበረክታል ሲሉ ገልጸውልናል :: ሙሉ ቅንብሩን ከድምፅ ዘገባው ይከታተሉ፤

እንዳልካቸው ፈቃደ

ሸዋዬ ለገሠ