1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢኳቶርያል ጊኒ ፖለቲካዊ ሁኔታ

ቅዳሜ፣ ጥር 5 2010

ኢኳቶርያል ጊኒ ውስጥ ባለፈው ታህሳስ 18፣ 2010 ዓም የመፈንቅለ መንግሥት ተሞክሮ ነበር ተብሏል።  የተባለው መፈንቅለ መንግሥት ከረጅም ጊዜ አንስቶ ውጥረቱ እየተካረረ በመጣባት አምባገነናዊት ሀገር ውስጥ ወደፊትም ውዝግቡ የሚባባስበትን ሁኔታ ጠቋሚ ይሆን? የብዙዎች ጥያቄ ነው። 

https://p.dw.com/p/2qmIW
Symbolbild Äquatorial-Guinea
ምስል picture alliance/ANP

የኢኳቶርያል ጊኒ ፖለቲካዊ ሁኔታ

ለወትሮው ኢኳቶርያል ጊኒ በዓለም አቀፍ ደረጃ በውዝግብና ግጭት ብዙም ከሚነሱት አፍሪቃውያት ሀገሪቱ  መካከል አይደለችም።ይሁን እንጂ፣ የካሜሩን ጦር ኃይላት ባለፈው ታህሳስ 18፣ 2010 ዓም ከባድ የጦር መሳሪያ ትጥቃ ያነገቱ ከቻድ፣ ሱዳን እና ማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ የሄዱ ተዋጊዎች ድንበር ተሻግረው ወደ ኢኳቶርያል ጊኔ እንዳይገቡ ካከላከሉ  እና ተዋጊዎቹን በቁጥጥር ካዋሉ ወዲህ ፣ ይህችው ምዕራብ አፍሪቃዊት ሀገር ድንገት የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ትኩረት አርፎባታል።

ተዋጊዎቹ በቁጥጥር የዋሉበትን ድርጊት በተከተሉት ቀናት የኢኳቶርያል ጊኔ መንግሥት በመላይቱ ሀገር ተቃዋሚዎችን  እየሰረ ነው። ከዚህ በተጨማሪም ፌስ ቡክ እና ዋትስአፕን የመሳሰሉትን የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎችን ዘግቷል። ከዚያም የኢኳቶርያል ጊኒ ፕሬዚደንት ቴዎዶሮ ኦቢያንግ ንጌማ ከ11 ቀን በፊት በፀጥታ ጥበቃ ሚንስትራቸው አማካኝነት ባስተላለፉት መግለጫ፣ አክራሪ በሚሉዋቸው የሀገሪቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የተመለመሉ የውጭ ቅጥረኞች ከስልጣን ለማስወገድ ሙከራ እንዳካሄዱ ፣ ግን ሙከራው እንደከሸፈ ማስታወቃቸው ይታወሳል።

ከዚህ ባለፈ ግን ተሞከረ ስለተባለው መፈንቅለ መንግሥት የወጣ ዝርዝር መግለጫ ም ሆነ የተሰማ ነገር የለም። ለዚህም በነዳጅ ዘይት ሀብት በታደለችው ፣ ግን አሁንም እጅግ ድሀ የሆነችው ሀገር የፕሬስ ነፃነት ላይ ያረፈው ገደብ ምክንያት ነው። አንድ ግልጽ የሚታወቅ ነገር ግን የውጭ ቅጥረኞች ከአፍሪቃ መሪዎች ሁሉ  ስልጣን ላይ ለረጅም ጊዜ የቆዩትን የኢኳቶርያል ጊኒ ፕሬዚደንት  ከስልጣን ለማውረድ ሙከራ ሲያ,ርጉ የሰሞኑ የመጀመሪያ ጊዜ አለመሆኑ ነው። ቴዎዶሮ ንጌማ ኦቢያንግን እጎአ ከ1979 ዓም ወዲህ ኢኳቶርያል ጊኒን በመምራት ላይ ይገኛሉ።በ2004 አንድ በብሪታንያዊ ባለሀብት የተረዳ የደቡብ አፍሪቃውያን ቅጥረኞች የተጠቃለሉበት ቡድን ፣ ኦቢያንግን ከባለተቋማት ይመቻሉ በተባሉ እጩ ለመተካት አቅዶ ነበር። ይሁን እንጂ፣ ቅጥረኞቹ ተዋጊዎች ወደ ኢኳቶርያል ጊኒ ባደረጉት ጉዟቸው እግረ መንገዳቸውን ዚምባብዌ ባረፉበት ጊዜ ማንነታcweቸው ሊጋለች ችሏል። ዎንጋ  የሚል መጠሪያ የያዘው  መፈንቅለ መንግሥት በተለይ አንድ በከፍተኛ ቦታ ላይ የነበረ ብሪታንያዊ  በገንዘብ የረዳው ስለነበር ትልቅ መወያያ ርዕስ ሆኖ  ነበር። ይኸው ግለሰብ የቀድሞ የብሪታንያ ጠቅላይ ሚንስትር ማርግሬት ታቸው ልጅ ማርክ ታቸር ነበር።

Äquatorialguinea Präsident Teodoro Obiang
ምስል picture-alliance/dpa/S. Lecocq

ከጥቂት ሳምንታት በፊት ከተሞከረው መፈንቅለ መንግሥት በስተጀርባ ያለውን ቡድን ወይም ምክንያቱን በተመለከተ ትዊተርን በመሳሰሉ የኢንተርኔት ማህበራዊ  መገናኛ ዘዴዎች ላይ መላ ምቱና ክርክሩ ቀጥሏል።  አንዳንዶች በኦቢያንግ አገዛዝ አንፃር ቻድ ወይም ካሜሩንን የመሳሰሉ ጎረቤት ሀገራት የተጠቃለሉበት  ያካባቢ ቡድን ሴራ ነው ብለው ይገምታሉ። ሌሎች መፈንቅለ መንግሥቱ ሙከራ የኢኳቶርያል ጊኒ መንግሥት ተቃዋሚዎችን ለመምታት ሲል ራሱ ያቀነባበረው ነው ይላሉ። በለንደን የሚገኘው የፖለቲካ ጥናት ተቋም፣ ቻተም ሀውስ የአፍሪቃ ክፍል ኃላፊ አሌክስ ቫይንስ እንደሚሉት ግን፣ እውነቱ  የተወሳሰበ ነው።

« የኢኳቶርያል ጊኒ መንግሥት ተቃዋሚዎች ካሜሩን እና ጋቦንን በመሳሰሉ በጎረቤት ሀገራት ይኖራሉ፣ የሀገራቸው መንግሥት ክትትል እንደሚያደርግባቸው ይሰማል። የተቃዋሚዎቹ በነዚህ ሀገራት መኖር የተነሳ ያካባቢው ሀገራት ተሳስረዋል።  ግን፣ ጎረቤት ሀገራት የመንግሥት ለውጥ ይፈልጋሉ ብየ አላስብም። ማዕከላይ አፍሪቃ፣ ቻድ፣ ካሜሩን እና ጋቦ ሁሉም ልክ እንደ ኢኳቶርያል ጊኒ የመልካም አስተዳደር እና ሌሎችም ችግሮች አሉባቸው። ስለዚህ ኦቢያንግ እንዲነሱ የሚደረግ መፈንቅለ መንግሥት አይደግፉም። የሰሞኑም ሙከራ በነዚህ ሀገራት የሚኖሩ የግለሰቦችን የሚመለከት ነው።»

የፈረንሳይ ዜና ወኪል የኢኳቶርያል ጊኒ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አጋፒቶ ምባ ሞኩይን ጠቅሶ እንደዘገበው፣ መፈንቅለ መንግሥቱ የተቀነባበረው ፈረንሳይ ሀገር ውስጥ ነው፣ ይሁን እንጂ ፣ ሙከራው የፈረንሳይን መንግሥትን እንደማይመለከት ሞኩይ መግለጻቸውን ዘገባው አክሎ አስታውቋል።
በዚችው ሀገር ባለፈው ታህሳስ ተካሄደ የተባለው መፈንቅለ መንግሥት እንዳላስገረማቸው የተናገሩት አሌክስ ቫይንስ እንደሚሉት፣ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በርግጥ ተካሂዷል ለተባለበት ሁኔታ ብዙ ምክንያቶች አሉ ። 
« ለብዙ አሰርተ ዓመታት እንደታየው ኢኳቶርያል ጊኒ ውስጥ የተካሄዱ ወይም ተሞክረዋል የተባሉ መፈንቅለ መንግሥት  አዘውትረው የተቃዋሚውን ወገን ለመከታተሉ ተግባር ነው የዋሉት። በወቅቱ ግልጽ የሂነ አንድ ነገር የሀገሪቱ ኤኮኖሚ እድገት አይታይበትም። ኤኮኖሚው በነዳጅ ዘይት ላይ ብቻ ጥገኛ በመሆኑ የነዳጅ ዘይት ዋጋ መቀነሱ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳርፎበታል።   ከዚሁ ጎን ግን በሀገሪቱ ተደጋግሞ መፈንቅለ መንግሥት መካሄዱ ወይም መሞከሩ ሀሳብን በነፃ የመግለጽም ሆነ በነፃ የመወያየት መብት የለም፣ ሰላማዊ ተቃውሞ ማካሄድም አይቻልም። እና  ብዙዎች ሕገ መንግሥታዊ ባልሆነ መንገድ፣ ማለትም በመፈንቅለ መንግሥት ለውጥ ለማምጣት  እንደሚቻሉ ስለሚያምኑ ነው።

በነዳጅ ዘይት ሀብ/ እና በአነስተኛው የሕዝቧ ቁጥር የተነሳ  ኢኳቶርያል ጊኒ ከሰሀራ በስተደቡብ ካሉት ሀገራት በጠቅላላ ከፍተኛው የነፍስ ወከፍ ገቢ ያላት ሀገር ናት ። ምንም እንኳን የነፍስ ወከፉ ገቢ 8,474 ዶላር ቢመዘገብም፣ አብዛኛው ሕዝቧ እድህነት አፋፍ ውስጥ እንደሚገኝ  ነው የተመድ መዘርዝሮች የሚያሳዩት። ለዚህም በሀገሪቱ የተስፋፋው ሙስና በዋነኛነት እንደ ምክንያት ይጠቀሳል። 

Karte Äquatorialguinea ENG

ባለፈው ጥቅምት ወር ለምሳሌ የፕሬዚደንቱ ልጅ ፓሪስ የመንግሥት ንብረትን ለራሳቸው ጥቅም ማዋላቸው፣ አሳማኝ መረጃ ከቀረበባቸው በኋላ ሶስት ዓመት እስራት በገደብ ተፈርዶባቸዋል።  107 ሚልዮን ዩሮ ፈረንሳይ የሚገኘውኝ ቤት ለመግዛት እንደተጠቀሙበት የተገለጸ ሲሆን፣ እንደአሌክስ ቫይንስ አስተያየት፣ ይህ ምዕራባውያኑ ሙስና ለመታገል እና እና የሰብዓዊ መብትን ለማስከበር አለመፈለጋቸውን የሚያሳይ ምልክት ነው። ምንም እንኳን ኢኳቶርያል ጊኒ የነዳጅ ዘይት አምራች ሀገር ብትሆንም፣ ያን ያህል የአውሮጳውያን እና አሜሪካውያን ትኩረት ያገኘች ሀገር አይደለችም። 

«ኢኳቶርያል ጊኔን በተመለከተ ግድየለሽነት ያለ ይመስለኛል። 1,2 ሚልዮን ሕዝብ የሚኖርባት ሀገሪቱ ነዳጅ ዘይት አምራች ብትሆንም ፣ ከትልቆቹ አምራቾች መደዳ የምትሰለፍ አይደለችም። እርግጥ፣ ዓለም አቀፍ የነዳጅ ዘይት እና ጋዝ አምራች ኩባንያዎች በሀገሪቱ አሉ፣ ትልቁ የአሜሪካውያኑ ኤክሶን ይጠቀሳል። ግን ከምዕራቡ ጋር ጠንካራ የጋራ ግንኙነት የሌላት ንዑሷ ኢኳቶርያል ጊኔ ወደ መረሳቱ የተረሳች ነው የምትመስለው። 

በወቅቱ ትኩረት እያገነ የመጣው ጉዳይ ከዚህ ጎን ሀገሪቱን ላለፉት 39 ዓመታት በመምራት ያሉትን ፕሬዚደንት ቴ ዎዶሮ ተተኪ አለመታወቁ ሀገሪቱን ወደፊት ሊያናጋ ይችላል የሚለው ስጋት ነው።  ኦቢያንግ  እንደሚታወሰው ኦቢያንግ እጎአ  በ2016 ዓም ምክትል ፕሬዚደንት አድርገው የሾሟቸውን ልጃቸውን ተተኪያቸው ሊያደርጉ ይችሉ ይሆናል የሚለው ጭምጭታ ሕዝቡ ዘንድ ተቀባይነት አላገኘም። ይህ እና  በሀገሪቱ በነጻና ትክክለኛ ምርጫ የስልጣን ሽግግር የማይኖርበት አሰራር፣ እንዲሁም የኤኮኖሚያዊ ችግሩ መግዘፍ ሲታሰብ ታድያ ባለፈው ወር የተሞከረው ዓይነቱ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ የመጀመሪያው ቀጣይ አሳሳቢ ጉዳይ ሊሆን እንደሚችል አሌክስ ቫይንስ ገምተዋል።

አርያም ተክሌ/ያን ፊሊፕ ቪልሄልም

ልደት አበበ