1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የእስረኞቹ ሰቆቃ እና «ወርቅ በሰፌድ»

ዓርብ፣ መጋቢት 15 2009

በኢትዮጵያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሊራዘም እንደሚችል ከመናገራቸውም በላይ ነው ያነጋገረው ጠቅላይ ሚንሥትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በፓርላማ ፊት ቀርበው ስለ«ወርቅ በሰፌድ» ያደረጉት ንግግር። በአንጻሩ ደግሞ አቶ ሐብታሙ አያሌው የገለጡት የእስር ቤት ሰቆቃ ብርታት የሰቀጠጣቸው ቃላት ቢያጡ «እግዚኦ!» ብለው አልፈውታል። 

https://p.dw.com/p/2ZrF5
Symbolbild Soziale Netze
ምስል picture-alliance/dpa/Heimken

በኢትዮጵያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሊራዘም እንደሚችል ከመናገራቸውም በላይ ነው ያነጋገረው። «መነሻ ገንዘብ ማምጣት የፈለገ ሰው ሠፌድ ይዞ ሄዶ ወርቁን አንጥሮ ብር ማምጣት ይችላል» አሉ ጠቅላይ ሚንሥትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በፓርላማ ፊት ቀርበው።  ንግግሩ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ተጠቃሚዎች ዘንድ ለቀናት የስላቅ ምንጭ ኾኖ ዘለቋል።  በአንጻሩ ደግሞ የቀድሞው የአንድነት ለዲሞክራሲ እና ለፍትኅ ፓርቲ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሐብታሙ አያሌው በአዲስ አበባ በተለምዶ ማዕከላዊ ተብሎ በሚታወቀው ወኅኒ ቤት ታሳሪዎች ላይ አሰቃቂ የቁም ስቅል ድርጊቶች እንደሚፈጸም ተናገሩ። የሰቆቃው ብርታት የሰቀጠጣቸው ቃላት ቢያጡ «እግዚኦ!» ብለው አልፈውታል። 

የዛሬ ሦስት ወር ግድምም ስለ ውጭ ምንዛሪ እጥረት እና «ስለ ፀጉር ሽያጭ» በተናገሩበት ወቅት ለቀናት መነጋገሪያ ኾነው ነበር። ጠቅላይ ሚንሥትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፦ «የወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ»ን በተመለከተ ለተነሳ ጥያቄ በሚል ፓርላማ ፊት ቀርበው ያደረጉት ንግግር ዛሬም አነጋጋሪ ኾኗል። 

ጠቅላይ ሚንስትሩ፦ ወጣቶች ከመንግሥት የተሰጣቸውን ብድር ይዘው እንዳይጠፉ ለማድረግ መፍትኄ ሲሉ ካቀረቧቸው ሁለት ነጥቦች የአንደኛው መልእክት አጠር ባለ ቪዲዮ በፌስቡክ እና ትዊተር የመገናኛ አውታሮች በስፋት ተሰራጭቷል። «ትግራይ ክልል፤ ቤንሻንጉል ክልል፤ ኦሮሚያ ክልል፤ ጋንቤላ፤ ደቡብ ብሔረሰቦች ክልል ሰፊ የወርቅ ምርት አላቸው። ስለዚህ መነሻ ገንዘብ ማምጣት የፈለገ ሰው ሠፌድ ይዞ ሄዶ ወርቁን አንጥሮ ብር ማምጣት ይችላል» ሲሉ ጠቅላይ ሚንስትሩ የተናገሩትን የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ተጠቃሚዎች ከዳር ዳር ተቀባብለውታል። አብዛኞቹ አስተያየቶች በስላቅ የተሞሉ ናቸው። 

Äthiopien Ministerpräsident Hailemariam Desalegn
ምስል Getty Images

«ጠቅላያችን ባሉን መሰረት በመሀበር ተደራጅተን ወርቅ በሰፌድ ልናፍስ ነው አድራሻ እኛ ሰፈር» ሰፌድ የሚሰፉ የአራት እናቶች ምስልን አያይዛ ያቀረበችው ሙና ተስፋዬ ናት። የሺብር ፋንታሁን፦ «የእናንተን ላይክና ኮሜንት ፌስቡክ ላይ ከማፍስ ከስደት ተመልሼ ኢትዮጵያ ውስጥ ወርቅ በሰፌድ ባፍስ ሳይሻል አይቀርም!» ብላለች። «ወርቅ በሰፌድ አንጥሮ ማውጣት የሚቻልበት ሀገር እያለን ምን በስደት አከራተተን ወደ ሀገር ቤት ጉዞ ልጀምር ነው። አይ አቶ ሀይለማሪያም» ያለችው አይዳ ቢንት ናት። ሮዛ ሐሰን ደግሞ፦«ሃገራችን ላይ ወርቅ በሰፌድ መታፈስ ተጀመረ ከአማራ ክልል ውጪ ሌሎች ክልሎች ወርቅ በወርቅ ናቸው ለካ» ብላለች።  «በሰላማዊት የቀረበ፤ አዎ ወርቅ በሰፌድ እንጂ ሙድ በመያዝ አይታፈስም። ከሰሞኑ ጠቅላያችን በፓርላማ ከተናገሩት ወርቃማ ንግግሮች ውስጥ ገንዘቡን ይዞ መጥቶ በሰፌድ ወርቅ ማፈስ ይችላል ብለዋል» ስትል ሰላሚት አበበ  አስተያየት ሰጥታለች።

አማረ ግርማይ በበኩሉ፦ «የጠቅላይ ሚንስትራችን ስህተት ምን ይሆን?» በሚል ጥያቄ አስተያየቱን ይጀምራል። ጠቅላይ ሚንስትሩ በጠቀሷቸው ቦታዎች ወርቅ የሚጣራው በባህላዊ መንገድ በሰፌድ እንደሆነም ለማብራራት ሞክሯል። ለመሆኑ ወርቅ በየት በኩል ነው በሰፌድ «የሚነጥረው» ሲሉ የሰላ ትችት ያቀረቡ ግን በርካታ ናቸው።
ሳሙኤል አሰፋ «ኢትዮጵያ ውስጥ እርዳታ እህል እንጂ ወርቅ በሰፌድ ሲበጠር አይቼ አላውቅም» ሲል በተቃራኒው፦ አስተያየት ሰጥቷል።

ሩሓማ ሩሓማ፦ «ሰፌድ ባረብኛ ምን ነበር ? ለማዳሜ [ለአሠሪዬ] አገራችን ወርቅ በሰፌድ ማፈስ ተጀምሯል ብዬ ላቅራራባት ፈልጌ ነበር ተባበሩኝ የምታውቁ» ስትል ተሳልቃለች። «ያልታደለ ሠፌድ ወፍጮ ቤት ይዞራል፤ የታደለ ደግሞ ወርቅ ተሸክሞ ቤተ መንግሥት ገብቷል» ፤ «ጉዞ ወደ ወርቅ አፈሳ!» የመሳሰሉ አስተያየቶችም በፌስቡክ ተስተናግደዋል። 

ጠቅላይ ሚንስትሩ ይኽን ያሉት በኦሮሚያ የማዕድን ቦታዎች ከባለ ሀብቶች ተነጥቀው ሊወሰዱ ነው መባሉን ለማስተባበል «አትነኩም» ለማለት የተናገሩት ነው ሲሉ በሌላ መልኩ የተመለከቱትም ነበሩ።

ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ከዚህ ቀደምም ኢትዮጵያ ውስጥ ስለተከሰተው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለጋዜጠኞች መግለጫ ሲሰጡ የሚታዩበት አጠር ያለ ቪዲዮ ሰፊ መነጋገሪያ ኾኖ መቆየቱ የሚታወስ ነው።  በወቅቱ ዛሬ በሥልጣኔ ላይ የሚገኙ ሃገራት በቀድሞ ጊዜ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሲገጥማቸው «ሌላው ቀርቶ የሴቶቻቸውን ጸጉር ጭምር ቆርጠው ኤክስፖርት እስከማድረግ ተገደው ነበር» ማለታቸው ይታወሳል። የዚህ ሳምንቱ ንግግራቸውም በማኅበራዊ የመገናኛ ዘዴዎች ለቀናት ዘልቋል። 

ጠቅላይ ሚንሥትሩ «ወርቅ በሠፌድ» እንደሚታፈስ በተናገሩበት ሳምንት ሌላ በሰፊው መነጋገሪያ የኾነ ዜናም ተሰምቷል። ከበርካታ አቤቱታ በኋላ ለህክምና ከቤተሰቦቻቸው ጋር ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ያቀኑት አቶ ሐብታሙ አያሌው ለአሜሪካ ድምፅ በሰጡት ቃለ-መጠይቅ ሲዘረዝሩ  በእስር ቤት ይፈጸማል ያሉት ሰቆቃ የአብዛኛውን የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ተጠቃሚ ቀልብ ስቧል። አቶ ሐብታሙ አያሌው የቀድሞው የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ህዝብ ግንኙነት  ኃላፊ ነበሩ። በሽብር ወንጀል ተጠርጥረውም ለሁለት ዓመት ግድም በወኅኒ ቤት ቆይተዋል። በስተመጨረሻ ለህክምና ወደ አሜሪካ ያቀኑት አቶ ሐብታሙ በእስር ቤት ቆይታቸው ወቅት ለኅመም ስለዳረጋቸው የማሰቃየት ተግባር እንዲሁም በሌሎች ላይ ይደርሳል ስላሉት ቁምስቅል ገልጠዋል። 

Äthiopien Habtam Ayalew
ምስል DW/Yohannes G.

«ማዕከላዊ ወንጀል ምርመራን የገነባው ማነው?» ሲል የሚያጠይቀው ዳዊት ሰለሞን ማዕከላዊ ከዘውዳዊ አገዛዙ አንስቶ በደርግ እንዲሁም በአሁኑ ወቅት የመሰቃያ ስፍራ መሆኑን ያብራራል። ማዕከላዊ «ፍትህ ለማስፈን ታቅዶ ተገነባ» የሚል ካለ የዋህ እንደሆነ የሚገልጠው ዳዊት ኢትዮጵያ «በሕግ ለመዳኘት ቃል የገባ» ሥርዓት እንደሌላት ጠቅሷል። 

«ወንድሜ ሀብታሙ፡- ከዚያ ግፍ ተርፈህ «ምስክር» መሆንህ የፈጣሪ ተዓምር ነው። አፍኣዊ ብቻ ሳይሆን ውሳጣዊ ሕማምህን በቸርነቱ የሚያቀልል አምላክ እርሱ ይጎብኝህ እንጂ ምን ይባላል?» ያለው ኤፍሬም ኤፍሬም ነው። 
«አቤት የሰው ልጅ ግፍ፤ አቤት የሰው ልጅ መከራ። በአገራችን እየተደረገ ያለው ግፍ፣ የመከረኞች ጩኸት፣ ጻድቁ ኢዮብ እንዳለው ነው» በማለት ግፍ ደርሶ ቢጮኽ ፍርድ እንደሌለ አክሎ ተናግሯል።

«እጅግ በጣም የሚዘገንን ያማል» በምሥራቅ ጣሰው የተሰጠ አጭር አስተያየት። «በጣም ያማል» የፍቅር ያሸንፋል አስተያየት ነው። «የወንድ ልጅ ስቃይ !ማሳሰቢያ ፦ ህፃናት ልጆች እንዲሰሙት አይመከርም» የሚለው ደግሞ በእስማኤል ዳውድ የተሰጠ ማሳሰቢያ ነው ልክ በሬዲዮው እንደተነገረው ማለት ነው። «የሐብታሙ አያሌው ፦ በማእከላዊ ምርመራ ክፍል የደረሰበት ስቃይ እና ጭካኔ » ከሚል ጽሑፍ ጋር ቃለመጠይቁ ተያይዟል። ዮናስ በለጠ በአጭሩ «አይ ሰው....» ሲል፦ በለጠ ሽፈራው ደግሞ «ይህንን ፡ እየሰማን፡ እንዴትስ ፡ እንቅልፍ ፡ ይወስደናል! !» ብሏል። 

ጠጠር ካለው የፖለቲካዊ አስተያየቶች ስንወጣ ደግሞ የኢትዮጵያ ቡና የመሀል አማካይ ተጫዋች ጋቶች ፓኖም በውድድር ዘመኑ መሀል ውሉ ማለቁ እና ሊራዘም እንደማይችል መነገሩ በስፖርት ወዳዱ ዘንድ ሰፊ መነጋገሪያ ኾኖ ነበር። ተጨዋቹ ከቡድኑ ጋር ውሉን ለማራዘም ቢፈልግም በአመራር ዘንድ ችግር እንደተፈጠረበት የገለጠበት ባለ ሁለት ገጽ ማብራሪያም ብዙዎች ተቀባብለውታል። ጋቶች ችግሩን ለደጋፊዎቹ በደብዳቤ ማሳወቁን በተመለከተ በርካቶች አድናቆት ችረውታል። ጋዜጠኛ ኢብራሒም ሻፊ ሁለት ገፁን ደብዳቤ አያይዞ ባቀረበበት አስተያየት የጋቶች ድርጊትን በማወደስ «ሌሎችም የሀገራችን ተጨዋቾች እዚህ ጋር የሚማሩት ነገር አለ» ብሏል።  ጢሞቲዎስ ባዬ በበኩሉ፦ «ጋቶች ፓኖም ከክለቡና ከወኪሉ ዳዊት ባሻህ የበለጠ ግልፅ መሆኑን ሳላደንቅ አላልፍም» ሲል አድናቆቱን ገልጧል። የጋቶች ወኪል ዴቪድ በሻን በመጥቀስ  ተጫዋቹ ከኢትዮጵያ ቡና ቡድኑ ጋር ለቀጣይ ሦስት ወራት ሊቆይ እንደሆነ መነገሩ በትናንትናው እለት ተዘግቧል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሠ