1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የእስራኤል የ2019 በጀትና የኢትዮጵያ ቤተ- እስራኤሎች ቅሬታ

ሰኞ፣ መጋቢት 10 2010

እስራኤል ፓርላማ ባለፈዉ ሳምንት ያፀደቀዉን  የ2019 የበጀት ድልድል በሀገሪቱ በሚገኙ የኢትዮጵያ ቤተእስራኤላዉያንን እና  የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችን። ጉዳዩ አጋጋሪ የሆነዉ ወደ እስራኤል ለመጓዝ  በመጠባበቅ ለሚገኙ ከ 8ሺህ በላይ ለሚሆኑ የኢትዮጵያ ይሁዲወች የማጓጓዣ በጀት አልተካተተም መባሉን ተከትሎ ነዉ።

https://p.dw.com/p/2uaeG
Israel Tel Aviv Protestaktion äthiopische Juden
ምስል picture-alliance/epa/Daniel Bar On

Israel Budget Allocation for 2019 and Ethiopian Israel's complaint - MP3-Stereo


እስራኤል የኢትዮጵያ ይሁዲወችን መቀበል ከጀመረች ከጎርጎሮሳዊ 1975 አ/ም ወዲህ 140 ሺህ የሚሆኑ ቤተ እስራኤላዉያን በሀገሪቱ እንደሚኖሩ መረጃዎች ያመልክታሉ።ይሁን እንጅ አሁንም ድረስ ከ8ሺህ በላይ የሚሆኑ ቤተሰቦቻቸዉ ወደ እስራኤል ለመጓዝ ኢትዮጵያ ዉስጥ በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ። ያለፈዉ ሳምንቱ  የሀገሪቱ ፓርላማ የ2019 በጀት ድልድል ግን ከቤተሰቦቻቸዉ ጋር ለመገናኜት ኢትዮጵያ ዉስጥ  በተስፋ የሚጠብቁትን ቤተእስራኤላዉያን የጉዞ በጀት አላካተተም መባሉ  በሀገሪቱ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊ ይሁዲወችንና  ለማህበረሰቡ መብት የሚሟገቱ አካላትን እያነጋገረ ነዉ። በሀገሪቱ የሚገኙ የኢትዮጵያ ቤተ እስራኤሎች ጉዳዩን አግላይና ወጥነት የሌለዉ የሀገሪቱ የስደት ፖሊሲ አንድ አካል አድረገዉ ያዩታል ሲል አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ በዘገባዉ አመልክቷል። መቀመጫዉን ኒዮርክ ያደረገዉ Struggle for Ethiopian Aliyah  የተባለዉ የኢትዮጵያ ይሁዲወች  መብት ተሟጋች ድርጅት  በበኩሉ የሀገሪቱ መንግስት ዉሳኔዉን እንደገና እንዲመረምርና  በችግር ዉስጥ ሆነዉ ለዓመታት ጉዞ በመጠባበቅ የሚገኙ የኢትዮጵያ ቤተ-እስራኤሎችን  በአፋጣኝ እንዲያጓጉዝ ጠይቋል ።
ድርጅቱ ከዚህ ቀደምም ኢትዮጵያ ዉስጥ የሚገኙ ቤተ-እስራኤላዉያን ያሉበትን አስቸጋሪ ሁኔታ በሚመለከት «ኢትዮጵያ ዉስጥ ያሉ ቤተ እስራኤሎች ገፅታ ይህን ይመስላል» በሚ,ል መኖሪያ ቀያቸዉን ለቀዉ  በጎንደርና በአዲስ አበባ  ከተሞች እያጋጠማቸዉ ያለዉን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር በመዘርዘር  አቅርቧል።  የበጀቱን ጉዳዩ የሀገሪቱ ምክር ቤት በቀጣዩ ስብሰባ በድጋሚ ይወያይበታል የሚል እምነት እንዳላቸዉም  የድርጅቱን  ቃል አቀባይ አሊሲያ ቦድነርን ጠቅሶ  አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ከእየሩሳሌም ዘግቧል።
ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸዉ እስራኤል ሀገር የሚገኜዉ  «ጠበቃ» የተባለ የኢትዮጵያ ይሁዲወች የመብት ተሟጋች ድርጅት  ሀላፊ አቶ ፋንታሁን አሰፋ በበኩላቸዉ   ቤት ንብረታቸዉን ጥለዉ ከ10 እስከ 20 ዓመታት ጉዞ የሚጠባበቁ  ሰዎች መኖራቸዉን ጠቁመዉ  የሀገሪቱ መንግስት የኢትዮጵያ ይሁዲዎችን  ችግር ሊገነዘብ እንደሚገባ አሳስበዋል።

Israel Tel Aviv Protestaktion äthiopische Juden
ምስል picture-alliance/epa/Daniel Bar On

«ያዉ በአርሶ አደርነት በተለያዬ መንገድ ራሳቸዉንሲያስተዳድሩና ቤተሰቦቻቸዉን ሲመሩ የቆዩ ናቸዉ።አሁን ግን ከአስርና ከሃያ አመት ባለነሰ ጊዜ ከቤታቸዉ ተፈነቃቅለዉ ጊዚያዊ በሆነሁኔታ የነበራቸዉን ሀብታቸዉን ንብረታቸዉን ጥለዉሁል ጊዜ በጭንቀትና በሃሳብ ነዉ ተቀምጠዉ ያሉት።እና ይሄ ነገር ይሄ ስቃይ መቋረጥ አለበት።ፍፃሜ ላይ መድረስ አለበት።ይሄ ነዉ አቋማችን።ስለዚህ መንግስት አስቸኳይ በሆነ ሁኔታ መፍትሄ መስጠት ይኖርበታል ነዉ የምንለዉ።» ካሉ በኋላ
እንዲህ አይነት መጉላላት  በሌሎች ሀገር ይሁዲወች የለም ያሉት ሀላፊዉ ፤የኢትዮጵያ ይሁዲወችም  በእኩል ዓይን ሊታዩ  እንደሚገባ  ነዉ የገለፁት።
እንደ አቶ ፋንታሁን ጉዳዩ ኢትዮጵያ ዉስጥ ሆነዉ በጉጉት የሚጠብቁትን ብቻ ሳይሆን እዚሁ ሀገር ያሉ ቤተሰቦችም ተረጋግተዉ እንዳይኖሩና ዉጤታማ እንዳይሆኑ እያደረገ በመሆኑ መንግስት አፋጣኝ መፍትሄ ሊሰጥ ይገባል። ላለፉት 10 ዓመታት መኖሪያቸዉን እስራኤል ያደረጉትና  በእነዚህ አመታት ሁሉ የሶስት እህቶቻቸዉን መምጣት በጉጉት የሚጠባበቁት  አቶ አዝመራዉ ምትኩ ፤ መንግስት የችግሩን አሳሳቢነት ተገንዝቦ  በጀቱን ያስተካክላል የሚል ተስፋ አላቸዉ።

Bete Israelis in Gondar
ምስል DW/G. Tedla

«ከአስር አመት በላይ ነዉ ከእህቶቼ ጋር ተለያይቼ ያለሁት። ያዉ እነሱ ያሉት ከዚያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ነዉ።በቤት ኪራይ ነዉ የሚኖሩት በጣም ከባድ ችግር ነዉ።እህቶቼ ብቻ ሳይሆኑ ሌሎችም ቤተሰቦች አባት እና እናት ፣እህትና ወንድም እንዲሁም ልጅ ተለያይተዉ ነዉ በኢትዮጵያ የሚኖሩት ። በአሁኑ ስዓት በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ነዉ ያሉት።እኔ ተስፋ የማደርገዉ

መንግስት ችግሩን አይቶ በጀቱን ያስተካክላል ብዬ አስባለሁ።»

 በጎርጎሮሳዊው 2016 ዓም የእሥራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ቤኒያሚን ኔትኒያሁ፤ ኢትዮጵያን ከጎበኙ በኋላ በጉዳዩ ላይ ተስፋ ተጥሎ የነበረ ቢሆንም ከዚያ ወዲህ የጉዞ ፈቃድ አግኝተዉ ወደ እስራኤል የገቡት ግን በመቶ የሚቆጠሩ ብቻ መሆናቸዉን ነዉ ኢትዮጵያዉያኑ ቤተ እስራኤሎች  የሚናገሩት። 
በሀገሪቱ የመመለስ ህግ  መሰረት አሊያህ (የማጓጓዝ ሂደት) በጎርጎሮሳዊዉ 1990 አ/ም የተጠናቋቀ ቢሆንም በአንዳንድ ፖለቲከኞችና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቶች ግፊት እንዲቀጥል መደረጉን መረጃዎች ያመለክታሉ። 
ከሀገሪቱ የ3 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር በጀት ዉስጥም 400 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር እነሱን ለማጓጓዝ የሚያስፈልግ መሆኑን የተለያዩ  ዘገባወች ያሳያሉ።

Äthiopien Addis Ababa Benjamin Netanjahu Staatsbesuch
ምስል picture-alliance/AP Photo/M. Ayene

ፀሐይ ጫኔ

ኂሩት መለሰ