1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የግጭት መረጃዎች ጥንቃቄ ያሻቸዋል ተብሏል

ዓርብ፣ ጥቅምት 17 2010

በኢሉባቡር አካባቢ ባለፈው ሳምንት በተከሰተ ግጭት የሰው ህይወት መጥፋቱ እና በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መፈናቀላቸው ይታወሳል፡፡ ግጭቱ የማህበራዊ መገናኛ ተጠቃሚዎች የሳምንቱ ዋነኛ መነጋገሪያ ጉዳይ ነበር፡፡ የመንግስት ኃላፊዎች ግጭቶቹን “የሚያባብስ ሽፋን ሰጥተዋል” ባሏቸው መገናኛ ብዙሃን ላይ የሰጧቸው ትችቶችና አስተያየቶችም ትኩረት ስበዋል፡፡

https://p.dw.com/p/2mdaR
Social Media - Facebook
ምስል picture-alliance/NurPhoto/J. Arriens

የግጭት መረጃዎች ጥንቃቄ ያሻቸዋል ተብሏል

ለወትሮው ዕለተ ሰንበት በማህበራዊ መገናኛ ተጠቃሚዎች ዘንድ ቀዝቃዛ ተሳትፎ የሚስተዋልበት ነበር፡፡ ባሳለፍነው እሁድ ጥቅምት 12 ግን ኢትዮጵያውያን የፌስቡክ እና ትዊተር አዘውታሪዎችን ወደ መድረኩ የሚስቡ ሁነቶች የበዙበት ነበርና በርካቶች በእነዚህ መገናኛ ዘዴዎች ላይ የሚባል የሚጻፈውን በመከታተል ተጠምደው አሳልፈዋል፡፡ በኦሮሚያ ክልል ባለፈው ሳምንት የተለያዩ አካባቢዎች የታዩ ተቃውሞዎች “መልካቸውን እየቀየሩ ነው” የሚሉ ጥቆማዎች ብቅ ብቅ ማለታቸው ስለጉዳዩ ለማወቅ የሚሹትን የማህበራዊ መገናኛዎችን በትኩረት እንዲከታታሉ አድርጓቸዋል፡፡ ብዙ ደጋፊ ያላቸው የሀገሪቱ ሁለት የእግር ኳስ ክለቦች የሚያደርጉት የዋንጫ ጨዋታ በቴሌቪዥን እና በዩ-ቲዩብ በቀጥታ እንደሚተላለፍ መነገሩም በርካቶችን ስቧል፡፡ 

Deutschland Negativ-Journalistenpreis «Verschlossenen Auster» geht an Facebook
ምስል picture alliance/dpa/K. Nietfeld

የኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለቦች ጨዋታ በቀጥታ እያስተላለፈ የነበረው ENN የተሰኘው የቴሌቪዥን ጣቢያ በድንገት ጨዋታውን አቋርጦ ያስተላለፈው ሰበር ዜና ብዙዎችን ያስደነገጠ ነበር፡፡ ከአንድም ሁለት ጊዜ የተላለፈው ይኼው ሰበር ዜና በኦሮሚያ ኢሉባቡር አካባቢ ያሉ ነዋሪዎች ላይ ጥቃት መድረሱን አውጇል፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች “ድረሱልን፤ እያለቅን ነው” ሲሉ በሲቃ ተሞልተው በስልክ የሚያሰሙትን ልመና አስደምጧል፡፡ 

በርካቶች ይህን ዘገባ በፍጥነት እየተቀባበሉ ያዳረሱት ሲሆን ሌሎች ደግሞ ዘገባውን የቀረበበትን ወቅት፣ የቃላት አመራረጥ እና ድምጸት መሞገት ያዙ፡፡ የዚያኑ ዕለት ረፋድ መቀመጫውን በአዲስ አበባ ያደረገው ዛሚ ኤፍ ኤም ያሰራጨውን ተመሳሳይ ዘገባ በማንሳት መገናኛ ብዙሃኑን ክፉኛ ተችተዋል፡፡ በቴሌቪዥን ጣቢያው ዘገባ ላይ በዕለቱ ተከታታይ ትችቶች ሲያቀርብ የነበረው ጋዜጠኛ የትነበርክ ታደለ “የግጭቱ ዜና መደበቅ የለበትም፡፡ ቢዘገብ ምን ችግር አለው?” ሲሉ ለተከራከሩት ተከታዩን ምላሽ በፌስ ቡክ ገጹ ሰጥቷል፡፡ 

“መዘገብና ሰበር ዜና የሰማይና የምድር ያህል ነው። አንድ መረጃ በዜና እወጃ ሲቀርብ መረጃ ነው። በሰበር ዜና ሲቀርብ ግን ‘ተዘጋጅ!’ የሚለውን ሀይለቃል በመያዝ የሰውን ስነልቦና ለተግባር ይቆሰቁሳል! የፖለቲካ ፓርቲዎች ግጭት ወይም የሁለት ሀገራት ጦርነት ቢሆን እሰየው! ይህ ግን የአንድ ሀገር ሰዎች ሳይፈልጉ የተፈጠሩበት የብሄር ማንነት ጉዳይ ነው! ማንም እንዳሻው የሚፈተፍተው ተራ ዜና አይደለም!! ENN ሊለን የፈለገው ምንድነው የምንለውም ለዚያ ነው!” ሲል የትነበርክ ሞግቷል፡፡ 

በላይ አብርሃ በበኩላቸው የቴሌቪዥን ጣቢያው የዘገበው “እውነት ነው” ባይ ናቸው፡፡ ግጭቱ በጣቢያው ከተጠቀሰውም “የባሰ ነበር” ሲሉ በፌስ ቡክ ገጻቸው የጻፉት በላይ “ENN የህዝቡን ሮሮ ስላሳየ እዉነቱን ከህዝብ ለመሰወር ነው፡፡ የሚያሳዝነዉ ግን ይህ ሁሉ ሲፈፀም የፀጥታ አካላት ነበሩ” ብለዋል፡፡ ሚክስ ብጽት በዚያው በፌስቡክ “ሰበር ዜና ሲባል በእለቱ በሰዓቱ የሆነን ድርጊት የምትዘግብበት መንገድ ነው፡፡ ENN ድርጊቱ ተፈፀመ ከተባለ ከ24 ሰዓት በኋላ የህዝቡን ቀልብ በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ጨዋታ ሰብስቦ ሲያበቃ ዜናውን ሰበር ብሎ ማቅረቡ እራሱ ከጀርባው ሌላ ሴራ እንዳለ ያሳብቃል” ሲሉ ወንጅለዋል፡፡ 

በቴሌቪዥን ጣቢያው ላይ የቀረበውን ትችት ይበልጥ ያበረታው ለዜናው መደገፊያ የተጠቀመው ምስል በኒውዝላንድ ሀገር የተከሰተ አደጋ መሆኑን የማህበራዊ መገናኛ ተጠቃሚዎች ካጋለጡ በኋላ ነበር፡፡ ኢ.ኤን.ኤን ከቀናት በኋላ በዘገባው ላይ ለተጠቀመበት የተሳሳተ ምስል ይቅርታ ጠይቋል። ታምሩ ኤች ቦጋለች ይህን አስመልክቶ ተከታዩን በፌስ ቡክ አስፍሯል፡፡ “ችግሩ እንዳለ ሆኖ በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ ፈቃድ ተሰጥቶት እየሰራ ያለ ቴሌቭዥን ጣቢያ በዚህ እጅግ ስሜት ሊነካ የሚችል ጉዳይ ላይ ከኢንተርኔት የውሸት ምስል በርብሮ ካመጣልኝ እንዴት ብዬ ነው በስልክ ያስደመጠኝን የተጎጂዎች ድምፅ የማምነው?” ሲል ጠይቋል፡፡ 

Facebook neues Logo
ምስል picture-alliance/dpa/L. Schulze

የኦሮሚያ ክልል የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ ኢ.ኤን.ኤን ቴሌቪዥን ጣቢያን እና ዛሚ ኤፍ ኤምን “ግጭትን የሚያባብሱ ዘገባዎችን እያቀረቡ ነው” ሲሉ መወቀሳቸው የማህበራዊ መገናኛ ተጠቃሚዎች መወያያ ሆኖ ነበር፡፡ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዶ/ር ነገሪ ሌንጮም ተመሳሳይ አስተያየት የሰጡ ሲሆን በመገናኛ ብዙሃኑ ላይ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚችል ጠቆም አድርገዋል፡፡ ይህን የዶ/ር ነገሪን አስተያየት መገናኛ ብዙሃኑን “ለማሸማቀቅ” የተደረገ ዘመቻ አድርገው የቆጠሩትም ነበሩ፡፡ ዳኒ ወልዱ ይህን የሚያንጸባርቅ አስተያት በፌስ ቡክ ገጻቸው ጽፈዋል፡፡ “ኢ.ኤን.ኤን እኩይ ተግባርን በመዘገቡ ነው ማስፈራርያና ዛቻ እየተቀበለ ያለው? እውነት ለመሸፈን የሚደረግ መጋጋጥ ይቅርና የተግባር ስራ በመስራት የህዝቡን ሠላም መልሱለት፡፡ ሰላም ለህዝባችን” ብለዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዘርዓይ አስገዶም በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የመገናኛ ብዙሃኑ ግጭቱን መዘገባቸው ትክክል እንደሆነ ማመላከታቸው አነጋግሯል፡፡ አቶ ዘርዓይ የብዙሃን መገናኛዎች ግጭቶችንም ቢሆን በኃላፊነት እስከሰሩ ድረስ ሁነቱን ለመዘገብ “የማንም ፍቃድ አያስፈልጋቸውም” ብለዋል፡፡ በየጎራው ያለውን ማብራሪያ ተከታትያለሁ ያለው ጋዜጠኛ ነጻነት ኃይሉ “ሚዲያ በሙያዊ ስነምግባርና ማህበራዊ ኃላፊነት ካልተመራ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል” በሚል ርዕስ በፌስ ቡክ ገጹ  ካሰፈረው ረዘም ካለ ጽሁፉ ተከታዩን ቀንጭበናል፡፡ 

“የዳበረ ግብረገብነትና ጠንካራ ማህበራዊ ትስስር ያላቸው ህዝቦች ባለቤት በሆነች አገራችን ጋዜጠኝነትን በአግባቡ መስራት ያን ያህል አዳጋች አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም የጋዜጠኝነት እሴቶችን ብንመለከት ከሀገራችን እሴቶች ጋር የተጣጣሙ ናቸው፡፡ ለምሳሌ የተሳሳተ መረጃ የሚያናፍስ ሰው አሉባልተኛ በመባል ይወገዛል፡፡ ሰውን ከሰው ጋር የሚያጋጭ ሰው በጠባጫሪነት ይኮነናል፡፡ ማህበረሰባዊ ተቀባይነት ለማግኘት አለመዋሸት፣ ሰውን ማጋጨት ሳይሆን ማስታረቅ፣ ሳያጣሩ አለማውራትን መካን ወሳኝ ነው፡፡
አንደ አለመታደል ሆኖ የአገራችን ሚዲያ ለዓመታት ከእነዚህ እሴቶች ጋር ሳይስማሙ የመንግስት፣ የቡድኖች ወይም የውስን ግለሰቦችን ፍላጎቶች ሲያስተናግዱ አንጂ እውነተኛውን የዜጎች ድምፅ ሊያስደምጡን አልቻሉም፡፡ ከዚህም የተነሳ የብዙሃን ሳይሆን የጥቂቶች ድምፅ፣ ከበሳል ሞጋቾች ይልቅ ሞገደኞች፣ ከሙያዊ ትንታኔዎች ይልቅ ያልተጣራ የሪፖርት ጋጋታዎችን ሲያቀርቡልን ኖረዋል፡፡ ይህ የሃሳብ ብዝሃነትን የደፈጠጠ አሰራር ዘሬም ቢሆን አልተቀረፈም” ሲል ጽፏል፡፡

ነጻነት የብዙሃን መገናኛዎች ሰሞኑን በኦሮሚያ የተከሰቱ አይነት ሁነቶችን ሲዘግቡ “ከቃላት ምርጫ” ጀምሮ “ከፍተኛ ጥንቃቄ” ማድረግ እንዳለባቸው ይመክራል፡፡ የብዙሃን መገናኛዎቹ በእንደዚህ አይነት ዘገባዎች ወቅት “ጉዳትን የመቀነስ መርህ”ን ታሳቢ ማድረግ እንዳለባቸው በጽሁፉ ጠቁሟል፡፡ “የብዙሃን መገናኛ አንድን መረጃ ከማሰራጨት በፊት መረጃው የሚኖረውን ተፅዕኖ ማጤን አለበት” ብሏል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጋዜጠኝነት እና ኮሚዩኒኬሽን ትምህርት ቤት መምህር አቶ ዳግም አፈወርቅ ተመሳሳይ አስተያየት አላቸው፡፡ 

Social Media - Facebook
ምስል picture-alliance/dpa/T. Hase

“በማህበራዊ መገናኛውም፣ በመገናኛ ብዙሃኑም ከተዘገበም በጥንቃቄ ነው፡፡  አንዳንዱ ደግሞ ሊዘገብም የማይገባው ጉዳይ አለ፡፡ በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ባለ የብሔር ተዋጽኦው በጣም ብዙ በሆነበት ሀገር እና አንድ ግለሰብ ከሌላ ግለሰብ ጋር ሲጋጭ ወደ ብሔር ግጭት የመሔድ አዝማሚያ ባለበት ሀገር ላይ አንድ ግለሰብም ሆነ መገናኛ ብዙሃን እንደዚህ አይነት ነገሮችን ሲዘግብ በጣም በጥንቃቄ መሆን አለበት፡፡ አንዳንዴ እኮ እንደውም ለማህበረሰቡ ጥቅም ከታሰበ ጉዳዩ ሊዘለልም የሚችልበት አግባብ አለ፡፡ ግን ደግሞ ከተዘገበ እጅግ በጣም በጥንቃቄ ሊዘገብ የሚገባው ጉዳይ ግጭት ነው፡፡ የማህበረሰቡን ሰላም በሚያመጣ እንጂ የበለጠ ሰላሙን በሚያደፈርስ መልክ መዘገብ የሌለበት ጉዳይ ግጭት ነው፡፡ አንዳንድ መገናኛ ብዙሃን የራሳቸው ፍላጎትም ስላለ፣ ራሳቸው የሚመሩበትም የኤዲቶሪያል ፖሊሲ ወይም የስነ ምግባር ደንባቸው ጭምር ስላለ እንደዚህ አይነት ነገሮችን ዝም ብለው ሲዘግቡ ታያለህ፡፡ ይሄ በጣም ስህተት ነው” ሲሉ ሙያዊ አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ አካፍለዋል፡፡ 

የብዙዎች ትችት በብዙሃን መገናኛዎች ላይ ይበርታ እንጂ ግጭቱን አስመልክቶ የማህበራዊ መገናኛ ተጠቃሚዎች በሚጽፏቸው ጽሁፎች እና በሚያሰራጯቸው ፎቶዎች ላይ ነቀፌታቸውን የሰነዘሩም አሉ፡፡ “በኢሉባቡሩ ግጭት የተገደለች ሴት ናት” በሚል በማህበራዊ መገናኛዎች ሲሰራጭ የነበረ አሰቃቂ ፎቶ ከአንድ የኤርትራ ልብ ወለድ ፊልም ላይ የተወሰደ መሆኑ ወዲያውኑ መጋለጡ ለወቀሳው በማስረጃነት አገልግሏል፡፡ አበበ ለማ የተባሉ የፌስ ቡክ ተጠቃሚ በማክሰኞ ጽሁፋቸው ትዝብታቸውን እንዲህ አካፍለዋል፡፡ “ገና በጠዋቱ ከአልጋዬ ሳልወርድ ዛሬስ አለም እንዴት አደረች? በተለይ ሀገሬ ብዬ ሞባይል ስልኬን ሳብ አድርጌ ይሄን መከረኛ ፌሰ ቡክ በደመነፍስ ስከፍተው ዘግናኝ ዘግናኝ ፎቶዋች ታጭቀዋል፡፡ የሚገርመው ደሞ ፎቶውን ልክ ነው ብሎ ከለጠፈው የሚያስተባብለው አስር እጥፍ ይበልጥ ነበር፡፡ ‘ይሄ ፎቶ የውሸት ነው ከፊልም ላይ ነው የተወሰደው’ እያለ ያንኑ አሰቃቂ ፎቶ መልሶ መላልሰው የለጠፉት ብዛታቸው፡፡ ብቻ እኔን በጣም ዘገነነኝ፡፡”  

ጉዳይ በተመሳሳይ የከነከነው የሚመስለው አገኘሁ አሰግድ በማህበራዊ መገናኛ ተጠቃሚዎች ዘንድ የሚታየውን ጥድፊያ ተችቷል፡፡ “ዘመናዊ ስልኮቻችን (ስማርት ፎኖቻችን) ድንቅ አድርገው ከሰሩት ስራ አንዱ አስተውሎታችንን በሚሞሪያቸው ከርስ መስረቃቸው ነው። ያው እንደምታውቁት፣ የስማርት ሰዎች ቁጥር እየቀነሰ ስማርት ስልኮች ያሻቅባሉ። እና ይሄ የዘመናዊ ስልክ ተጠቃሚ ትውልድ አንዱ ባህሪው ያገኘውን ሁሉ ወደኢንተርኔት ዓለም ይዞ መቻኮል ነው። ማንም ሳይለጥፈው በፊት ዳይ! ዳይ! ወደ ፌስቡክ… ወደ ቲውተር። ሎግ ኢን፣ ሎግ ኢን! ብርርር…! ፖስት ፖስት! ቲዊት ቲዊት! ስታተስ ይተኮሳል። ቀጣይ ልጆቻችን ሶሻል ሚዲያ ዳር ተወልደው፣ ሶሻል ሚዲያ ላይ ድኸው፣ ሶሻል ሚዲያ ላይ አድገው። ሶሻል ሚዲያ ላይ ይሆናል መሞታቸው የሚሰማው” ሲል ተሳልቋል። 

Symbolbild Facebook
ምስል picture-alliance/dpa

ታዋቂው ደራሲ በዕውቀቱ ስዩምን ይበልጥ ያሳሰበው የፎቶው ሳይሆን በተወሰኑ አራማጆች (አክቲቪስቶች) የሚሰራጨው ጽሁፍ ነው፡፡ ባለፈው ረቡዕ በፌስ ቡክ ካጋራው ጽሁፉ ክፍል ሽራፊውን እነሆ፡፡ “አንዳንዱ የፌስቡክ አክቲቪስት ዳግም አረቄ እንደጠጣ አብሿም የቆሎ ተማሪ የዞረበት ነው፡፡ ለምሳሌ አንዱ ምላሱን አድጦት ይሁን አስቦበት አንድ ዘረኛ ነገር ይፅፋል ወይም ይናገራል፡፡ ዘረኛውን ፅሁፍና ንግግር አይተህ እንዳላየህ ካለፍከው የትም አይደርስም፡፡ በራሱ ጊዜ ይከስማል፡፡ ዘረኝነትን መዋጋት የሚቻለው ዘረኞች የሚስገበገቡለትን ትኩረት በመንፈግ ነው:: ግን የወሬ ሀራራ የሚያስፏሽከው ስፍር ቁጥር የለሽ አክቲቪስት ባለበት ሀገር ይህን ማድረግ ቀላል አይደለም፡፡  

ባገራችን የሆነ ቦታ ግጭቶች ይነሳሉ፡፡ ከዚያ ያካባቢ ሽማግሌዎች ጉዳዩን በሽምግልናና በእርቅ እያረጋጉት ነው የሚል ዜና ይወጣል፡፡ የግጭቱን ዜና እያጋጋለ የሚነዛ የመበርከቱን ያህል : የእርቁን ዜና ከመጤፍ የሚቆጥረው የለም፡፡ በጦርነት የኖርን ህዝቦች ስለሆን ገና የጦርነት አዚም( ሀንጎቭር ) አለቀቀንም፡፡ ስለ እርቅ ስለ ሰላም በስፋት መተንተን የሚያስችለን በቂ የቃል ክምችት የለንም፡፡ ደሞ ያክቲቪስት ነኝ ባዩ ትንታኔ ሁላ የሚጠናቀቀው ሌላውን በመወንጀል ነው፡፡ ሁሉም ሌላውን ለመውቀስ ከመሞከሩ በፊት የችግሩ አካል መሆኑን የሚገነዘበው መች ነው?” ሲል በዕውቀቱ ይጠይቃል፡፡   

ተስፋለም ወልደየስ

አርያም ተክሌ