1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

Merga Yonas Bula
ሐሙስ፣ ግንቦት 3 2009

የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ስድስት ቢሊዮን ብር በመመደብ «የኤኮኖሚ አብዮት» በተሰኘዉ እቅዱ ለወጣቶች አዲስ የስራ እድል ለመፍጠር እየተንቀሳቀሰ መሆኑን በተደጋጋሚ አስታዉቋል።

https://p.dw.com/p/2cp4u
Äthiopien, Adama
ምስል DW/M. Yonas Bula

Oromia Economic Revolution - MP3-Stereo

ከሁለት ወር በፊት ይፋ የሆነዉ ይህ እቅድ ወጣቶች ተደራጅተዉ ለኢንዱስትሪ ግበዓት የሚሆነዉን የማዕድንና የእርሻ ዉጤቶች መቅረብ እንዲችሉ የክልሉ ባለስልጣኖች ሲናገሩ ይሰማል። የመኖርያ ቤት ችግር ላለባቸዉም መንግስት ቤት ገንብቶ እንደሚሰጣቸዉና ባለዉ የኤኮኖሚ ስርዓት ዉስጥ የበለጠ ተሳትፎ በማድረግ «የገንዘብ አቅማቸዉን» እንድያጎለብቱም የክልሉ መንግስት እቅድ እንዳለዉ ተጠቅሰዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ለማ መገርሳም በቅርቡ ለወጣቶች ባደረጉት ንግግር ይሕንኑ አስታዉቀዉ ነበር።«በእጃችን ያለ ኃብት ዛሬ ነዉ። መስራት ካለብኝ ዛሬ ነዉ። ለነገ የማስቀምጠዉ የለኝም። አቅሜ የፈቀደዉን ያህል ዘሬ ነዉ መስራት ያለብኝ። ዛሬ ነዉ መስራት ያለብኝ ለወደፊት ኑሮዬ፣ በተለይም የኛ ትዉልድ፤ የታሪክ ኃላፊነት ያለብን ትዉልድ፣ ወጣቱን ጨምሮ፣ የኦሮሞን ሕዝብ ጨምሮ ጠንካራ አብዮት መሎከስ አለብን። እሱም በኤኮኖሚ ላይ የሚደረግ አብዮት። ቀንም ሆነ ማታ የምናስበዉ ስለ ኤኮኖሚ፣ ስለ ገንዘብ፣ መሆን አለበት። ሕልማችን ስለ ገንዘብ መሆን አለበት። በኤኮኖሚ  ያልጠነከረ መኅበረሰብ ተላላኪ ነዉ የሚሆነዉ፣ ቁጥር ብቻ ነዉ፣ የትም ሊደርስ አይችልም። ገንዘብ ያለዉ ነዉ ወደ ፈለገዉ የሚነዳዉ።»

የአቶ ለማ መገርሳን ንግግር ተከትሎ የኦሮሚያ ክልል ወጣቶች ተደራጅተዉ ለኢንዱስትሪዎች ግብዓት የሚሆኑ ዉጤቶችን እንድያቀርቡ ለማድረግ ወደ ስራ መግባቱን የአገር ዉስጥ ዘገባዎች ያመለክታሉ። የኢንዱስትሪዎቹ ስራ አስካያጆች መንግስት ለወጣቶቹ የስራ እድል ለመፈጠር የያዘዉን እቅድ ባይቃወሙም «አፈጻጸሙ» እንደሚያሳስባቸዉ ዘገባዉ ጠቅሶአል። «ወጣቶች ማሽኖች የሏቸዉም፣ ፋብሪካዉ ደግሞ ያልተቋረጠ ግብዓት ይፈልጋል» ሲሉም የሲሚንቶ ፋብሪካ ስራ አስካያጆች መናጋራቸዉን ሪፖርተር ጋዜጣ ጠቅሶ ዘግቦታል።

የፋብሪካዎች መናኸሪያ እየሆነች መምጣቷ የሚነገርላት የሰበታ ከተማ ወደ 400 የሚሆኑ ፋብሪካዎች እንደሚገኙባት የከተማዋ የኮምዩንኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ወርቁ ዳባሌ ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል። ፋብሪካዎቹ አብዛኞቹ ወጣትና ሴቶች ለሆኑ፣ ከ50,000 በላይ ሰራተኞች፣ የስራ እድል መፍጠር እንደቻሉ አቶ ወርቁ ገልፀዋል። በከተማዋ አካባቢ በግለሰቦች የተያዙትን የተፈጥሮ ሃብቶች፣ ለምሳሌ እንደ ድንጋይ ማምረቻ ቦታዎችን ከግለሰቦች አስለቅቀን ወጣቶች ቦታ እንዲይዙ እያስደረግን ነዉ ብለዋል። በአፈጻፀሙ ቅሬታ የሚያነሱትን እንዲህ  ሲሉ  መልስ ሰተዋል፣ «በዚህ ሂደት፤  በፊት በማይገባ መንገድ ጥቅም ስያገኝ የነበረ ግለሰብ፣ ጥቅሙን ስያጣ ልያኮርፍ ይችላል። አንደኛ ይህ ኃብት አንድ ግለሰብ ሲጠቀም ነበር። ይህ ግለሰብ ምንም የጨመረዉ ነገር የለም። ግን አሁን ብዙ ወጣቶች እየተጠቀሙ ነዉ። እነሱም ለሌላ ወጣቶች አዲስ የስራ እድል እየፈጠሩ ነዉ። በአጠቃላይ አሁን ስናይ ወጣቶች በተሰባቸዉን ማስተዳደር ችለዋል። ይሁን እንጂ ወጣቶች ተደራጅተዉ ወደ እዚህ ለመግባት  አሁንም ችግሮች እንዳሉ ከወጣቶች መስማት ችለናል። የአዳማ ነዋሪ የሆነዉ ግን ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ ግለሰብ፣ ለዶይቼ ቬሌ እንዲህ ሲል ይናገራል፣ «በአሁኑ ጊዜ አንድ አንድ ስልጠናዎች ይሰጣል። ከዛ ዉጭም ወጣቶች እንዲደራጁ እየተደረገ ነዉ፣ እናም ገንዘብ ተሰቷቸዉ፣ ወደ ስራ ሊገቡ የሚችሉበት መንገድ ይመቻችላቸዋል  እያሉ ይናገራሉ።  ግን በተጨባጭ  የተደራጁም ወጣቶች ወደ ስራ የገቡበት ሁኔታ የለም። የሚያደራጀዉም አካል ከመናገር ዉጭ በተጨባጭ ሰርቶ መሬት ላይ ያለ ነገር የለም።»

በኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ ተቃዉሞ እንደነበረ ይታወሳል። የስራ ፈጠራም ሆነ «የኢኮኖሚ አብዮት» ስለ የክልሉ መንግስት ይዞ የመጣዉ እቅድ የወጣቶች ቅሬታ «ለማብረድ» የታለመ ነዉ ሲሊ የሚተቹም አልጠፉም።

መርጋ ዮናስ

አዜብ ታደሰ