1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኩላሊት ተግባር መዳከም ምንነት

ማክሰኞ፣ መጋቢት 25 2010

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ብዙዎች ለኩላሊት ህመም ስለመዳረጋቸው በሰፊዉ ሲወራ ይሰማል። ለህክምና ከመድረስ በፊት ኩላሊት ሥራው እንዲዳከም ወይም እንዲቆም የሚያደርገው ምን ይሆን? አስቀድሞ መደረግ የሚገባው ጥንቃቄስ?

https://p.dw.com/p/2vP41
Symbolbild Menschliche Niere Grafik
ምስል Colourbox

ድንገተኛ እና በጊዜ ሂደት የሚከሰት የጤና ችግር ነው፤

ደምን የማጣራት ብሎም በምግብ ሆነ በመድኃኒት ምክንያት የወደሰዉነት የገቡ መርዛማ ነገሮችን የማስወገድ ታላቅ ኃላፊነት ያለበት የሰውነት አካል ነው ኩላሊት። ኩላሊት ሥራውን አቆመ ወይም ኪድኒ ፌለር የሚባለው ችግር በህክምናው አገላለፅ የጤናው ችግር ከመጨረሻ ደረጃ ደረሰ ማለት እንደሆነ ነው መጣጥፎች የሚያመለክቱት። በጥቁር አንበሳ ሀኪም ቤት የዉስጥ ደዌ ከፍተኛ ሃኪም እና  መምህር ሆነው ያገለገሉት እና አሁን በግላቸው ክሊኒክ በሙያቸው በመሥራት ላይ የሚገኙት ዶክተር ቶሌራ ወልደየስ ኩላሊት ጠቅላላ አገልግሎቱን አቆመ ሲባል ወትሮ ከሚያከናዉነው በደቂቃ 15 ሚሊ ሊትር ብቻ የማጣራት አቅም ሲኖረው እንደሆነ ነው የሚያስረዱት። እዚህ ደረጃ ለመድረስም አራት ደረጃዎችን ማለፍ ይኖርበታል።

የኩላሊት ዋናዉ ሥራ ይላሉ ዶክተር ቶሌራ በማያያዝ፤ «ኩላሊት ዋናዉ ነገር ፈሳሽን ከሰዉነታችን ውስጥ ያስወግዳል። ለምሳሌ አሁን ሰው ይበላል፤  ይጠጣል፣ ፈሳሹን ይወስዳል ያ የሚወጣው በኩላሊት ነው። ሌላው ነገር መርዛማ ነገሮች በሙሉ ከመድኃኒትም ሆነ ከምግብ የሚመነጩ ሰውነታችን ውስጥ የሚለወጡ ነገሮች ፤ መርዝ የሆኑትን ነገሮች ኩላሊት ነው የሚያወጣዉ። ኩላሊት ደከመ ማለት እነዚህን መርዛማ ነገሮች ሰውነት ውስጥ ተጠራቀሙ ማለት ነው።»

የእነዚህ መርዛማ ነገሮች መጠራቀም ደግሞ ልብ እንዳይሰራ፤ ሳንባ እንዳይሰራ ጭንቅላትም በአግባቡ ተግባሩን እንዳያከናውን ስለሚያደርጉ ኩላሊትም ሥራው ይስተጓጎላል። ያኔም ነው ኩላሊት ተነቃቅቶ እንደወትሮ እንዲሠራ ዲያሊሲስ ወይም የህክምናው የኩላሊት ጽዳት የሚደረግለት። ዶክተር ቶሌራ እንደሚሉትም ይህ የህክምና ሂደት መሸጋገሪያ ብቻ ነው።

ኩላሊት በድንገተኛ ወይም በጊዜ ሂደት ለእንዲህ አይነቱ የጤና እክል ሊዳረግ ይችላል። ችግሩም ዕድሜ የሚገድበው አይመስልም። ኩላሊትን በድንገት አገልግሎቱን እንዲያስተጓጉል የሚያበቁ ምክንያቶችን ዶክተር ቶሌራ እንዲህ ይዘረዝራሉ።

Nierensteine
ምስል picture alliance/Klaus Rose

«አክዩት የተባለው ወይም በድንገት ኩላሊት ሲደክም ወይም ደግሞ ሥራውን መስራት ሲያቅተው ያለውን በዋናነት በሶስት ነው የምንከፍለው፤ አንደኛው ከኩላሊት ውጪ የሚከሰቱ ነገሮች ኩላሊት በዚያን ጊዜ የሚጎዳበት ሲሆን ነው ከሌሎች በሽታዎች አጋጣሚ ኩላሊት እንዳይሰራ ኩላሊት ላይ የሚያመጡት ችግር ማለት ነው። ይሄ ማለት ለምሳሌ አንድ ሰው የደምዝዉዉሩ ቢቀነስ ያ የደም ዝውውር ወደኩላሊት ሳይሄድ ኩላሊት ይታመማል።»

 ሰውነት ውስጥ ያለው ፈሳሽ በተለያዩ ምክንያቶች ሲቀንስ ተገቢው መጠን ያለው ፈሳሽ ኩላሊት ሲያጣ ድንገት ሥራው ሊዳከም ይችላል ነው የሚሉት ባለሙያው። ከዚህም ሌላ የልብ ህመምተኛ የሆነ ሰው ልቡ በሰውነቱ ውስጥ ደሙን በትክክል የማያሰራጭ ከሆነ ከሆነ እና ወደኩላሊት የሚሄደው ደም የሚያንስ ከሆነ በቂ የሆነ የደም ዝውውር ስለማይኖረው ይህም ኩላሊትን ለህመም እንደሚዳርገውም ያስረዳሉ። ይህ ብቻም አይደለም። ኢንፌክሽኖች እና አንዳንድ የሚወሰዱ መድኃኒቶችም ኩላሊትን ለድንገተኛ የአገልግሎት ማቋረጥ ሊዳርጉት እንደሚችሉም አመልክተዋል።

እንዲህ አይነቱ ችግር በዕድሜ ገፋ ያሉ ሰዎችን ሲያጋጥም ከመጀመሪያው በቂ የሆነ ክትትል እና ፈሳሽ የመውሰድ ልማዱ ከሌለ ይበልጥ ሊያጠቃቸው እንደሚችል ነው ዶክተር ቶሌራ ያስረዱት።

Milchpulver-Skandal in China
የምርመራዉ ሂደት አንዱ ክፍልምስል AP

በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ኩላሊት ሥራውን እንዲዳከም የሚያደርጉት በጊዜ ሂደት በዚህ የሰውነት ክፍል ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ ህመሞች ናቸው። እንዲህ ያለው የጤና ችግር ልጆች ላይ የሚከሰትበት ዋናዉ ምክንያት ደግሞ ይላሉ ዶክተር ቶሌራ።

«ልጆች ላይ የሚታየው ብዙዉን ጊዜ በኢንፌክሽን የሚመጣ ነው። የጉሮሮ ኢንፌክሽን አለ ወይም ደግሞ የቆዳ ኢንፌክሽን አለ፤ ያ ልክ ልብ ላይ ችግር እንደሚያመጣው ሁሉ ኩላሊትም ላይ ችግር ያመጣል፤ በልጆች ላይ በአብዛኛዉን ጊዜ።»

ኩላሊት ከነአካቴው አገልግሎቱን ለማቆም እስኪደርስ ደረጃ በደረጃ የሚያሳያቸው መዳከሞች ይኖራሉ። ኩላሊት አገልግሎቱ በሚዳከምበት ጊዜ ታማሚዉ የማቅለሽለሽ፣ የእግር እብጠት፤ የድካም፤ የምግብ ፍላጎት የመቀነስ እና የመሳሰሉት ተያያዥ ምልክቶች እንደሚያጋጥሙት መረጃዎች ያመለክታሉ።

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ