1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የካቢኔ ሹመትና የድምጻዊ ታምራት ደስታ ኅልፈት

ዓርብ፣ ሚያዝያ 12 2010

ድምጻዊ ታምራት ደስታ ድንገት ሳይታሰብ ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱ በርካቶችን አስደንግጧል። በጠቅላይ ሚንሥትር አቢይ አህመድ  ቀርቦ የጸደቀው የካቢኔ ሹመትም አነጋጋሪ ነበር። ሹመቱን በተመለከተ የድጋፍ እና የተቃውሞ አስተያየቶች የተሰነዘሩ ሲኾን፤ ወትሮ በፖለቲካ ጉዳዮች ላይ በብዛት አስተያየት የሚሰጡ ሰዎች ዝምታ መመረጣቸውም ተስተውሏል።

https://p.dw.com/p/2wMJH
Äthiopien Amtseinführung neues Kabinett durch  Premierminister Abiy Ahmed
ምስል Reuters/T. Negeri

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የሣምንቱ አበይት መነጋገሪያ

ድምጻዊ ታምራት ደስታ ድንገት ሳይታሰብ ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱ በርካቶችን አስደንግጧል። እንደቀልድ ለጉረሮ ኅመም ሐኪም ቤት ሄዶ ድንገት ሞተ መባሉ ብዙዎችን አሳዝኗል። በጠቅላይ ሚንሥትር አቢይ አህመድ  ቀርቦ የጸደቀው የካቢኔ ሹመትም አነጋጋሪ ነበር። ሹመቱን በተመለከተ የድጋፍ እና የተቃውሞ አስተያየቶች የተሰነዘሩ ሲኾን፤ ወትሮ በፖለቲካ ጉዳዮች ላይ በብዛት አስተያየት የሚሰጡ ሰዎች ዝምታ መመረጣቸውም ተስተውሏል። በትዊተር፣ በፌስቡክ እና በዋትስአፕ የተሰጡ አስተያየቶችን አሰባስበናል።

ሐሙስ እለት ይፋ የኾነውን በኢትዮጵያ የካቢኔ አባላት ሹመት መጽደቅን በተመለከተ የድጋፍ እና የትችት አስተያየቶች መሰንዘር የጀመሩት ዜናው በተሰማ ቅጽበት ነበር። «አቢይ አህመድ ጥሩ የለውጥ አራማጅ ለመኾን ገና ከመነሻው ሙሉ ለሙሉ ወድቀዋል። ምንም የወደፊት እቅድ የላቸውም፤ በአዲሱ ካቢኔያቸው እንደሚታየውም ለብሔር ከማዘንበል ነጻ አልኾኑም። ሲጀመር ከኢሕአዴግ ለውጥ መጠበቅ ስህተት ነበር። የሞሰነ ሥርዓትን መቀየር አይቻልም፤ መለወጥ እንጂ» ሲል ትዊተር ገጹ ላይ በእንግሊዝኛ የጻፈው ፋሲለደስ ነው።

ይርጋለም ኃይሌ ከፋሲለደስ በተቃራኒ የጠቅላይ ሚንሥትር አቢይ ተግባርን በትዊተር ጽሑፉ አድንቋል እንዲህ ሲል፦ «ጠቅላይ ሚንሥትር አቢይ የካቢኔ እጩዎቻቸውን ብሔር አልተናገሩም። ያ ኢትዮጵያ በዚህ ወቅት እጅግ የሚያስፈልጋት የፖለቲካ መግባባት ነው። ሀገርን በመገንባቱ ሒደት ተግባቦት የላቀ ድርሻ ይወስዳል። አድንቀናል» ብሏል።

Äthiopien Amtseinführung neues Kabinett durch  Premierminister Abiy Ahmed
ምስል Reuters/T. Negeri

በሳቅ ከሚያነባ ምስል ጋር የተደገፈው የፈቃዱ የትዊተር አስተያየት በአጭሩ፦ «ድንቄም ሹመት» ነው ሲል ይነበባል።  እሸቱ ሆማ ቄኖ እዛው ትዊተር ላይ ጽሑፉን የሚጀምረው በሳቅ ነው፦ «ሃሃሃ ቀጣዩ ዲስኩር ደግሞ ተገቢው ሰው በተገቢው ቦታ የተመደበበት "አግባብ" የህዝቡን ጥያቄ የፈታ መሆኑን አንዳንድ የ __ ነዋሪዎች ገለፁ የሚል ይሆናል» ሲል የጻፈው እሸቱ መልእክቱን «ካርታው ተፐውዟል» በማለት ከሳቅ ምልክት ጋር ያጠቃልላል።

«ጠቅላይ ሚንሥትር አቢይ በአገልግሎት አሰጣጥ እና ሙስና ላይ አንዳችም አይደራደሩም» ይላል አንተነህ ተስፋዬ የተባለ አስተያየት ሰጪ በትዊተር መልእክቱ።  ቀደም ሲል ጠቅላይ ሚንሥትሩ ባደረጉት ንግግር አንተነህ በጠቀሳቸው ጉዳዮች ላይ ለውጥ እንደሚያመጡ መግለጣቸውን በማስታወስ ይመስላል ያን ያለው። «ኾኖም» ሲል ይቀጥላል አንተነህ። «ኾኖም የሚንሥትሮችን ብቃት በተመለከተ ሁሉን ቅር ላለማሰኘት የተዘጋጁ ይመስላል። ከኢሕአዲግ ውጪም ቢኾን ብቃት ያላቸውን ሰዎች ይመለከታሉ ብዬ ተስፋ አረርጋለሁ» ብሏል።

«ግልጽ የኾነ ፍኖተካርታ እና አመላካቾች» አለመታየታቸውን በትዊተር ገጹ የጻፈው የአዲስ ነገር ጋዜጣ የቀድሞው አዘጋጅ መስፍን ነጋሽ ደግሞ የሚከተለውን ብሏል። «የአገልግሎት ሰጪውን ዘርፍ በማሻሻል እና ሙስናን በመዋጋት ብቻ ዲሞክራሲያዊ ለውጦች ፈጽሞ አይካካሱም።»

ቀጣዮቹ አስተያየቶች በፌስቡክ እና ዋትስአፕ የተሰጡ ናቸው። «ጠቅላይ ሚንሥትር አቢይ ያዋቀሩት ካቢኔ ተጨባጭ ለውጥ ያመጣ ዘንድ ምኞታችን ነው!።» አስተያየት ሰጪው ብርሃኑ ኦላን ባዳሰው ነው። ብሊሱማ ሲሜ የተባለ አስተያየት ሰጪ በበኩሉ፦ «በጣም ደስ ብሎኛል» ብሏል። ቀጠል አድርጎም፦ «አሁንም ግን የዘረፉና ያስገደሉ ካልተጠየቁ ለእኛም መመሪያ አይኾንም» ሲል አክሏል። አዲስ ተሿሚዎችን በተመለከተም «በቅንነት እና በታማኝነት መሥራት» እንዳለባቸው ጠቁሟል።

«ተመችቶኛል በተለይ የአሥቸኳይ ጊዜ አዋጁ አንዲታወጅ ከማስደረግ አንስቶ በዋናነት ሲመሩት የነበሩ ሹማምንቶች ሁሉም ከቦታቸው ተነሥተዋል» የጌታቸው ኢላላ የፌስቡክ አስተያየት ነው።

Äthiopien Vereidigung Premierminister Abiy Ahmed
ምስል picture-alliance/AA/M. W. Hailu

«እኔ የተለየ ነገር አላየሁም መክንያቱም ሁሉም የበፊት ሰዎች ናቸው መመዘኛው ትምህርትን ነው ወይስ የፖለቲካ ወገንተኝነትን ነው። አቶ ሽፈራው ሽጉጤ በምን መመዘኛ ነው የግብርና ሚነስትር የሚሆኑት የትምህርት ሚስቴር እያሉ የሆነው ግልፅ ነው እንደገና ሌላ ስህተት» የሚል መልእክት የደረሰን ደግሞ በዋትስአፕ አድራሻችን ነው። «ይህ ጠቅላይ ሚኒስተር አካሄዱ በጣም የተመረጠ ነው አገር ሰላም እድትሆን በትክክል ሥልጣንን ማሻሻሉ ይቀጥልበት እላለሁ።» ይኼም በዶይቸ ቬለ የዋትስአፕ አድራሻ የተላከ መልእክት ነው።

ታዋቂው ድምጻዊ ታምራት ደስታ ረቡዕ ሚያዝያ 10 ቀን 2010 ዓም በድንገት ከዚህ ዓለም በሞት የመለየቱ ዜና በርካቶችን ያስደነገጠ ነበር። በዋትስአፕ ከተላኩልን መልእክቶች «በታምራት ሞት በጣም አዝነናል ነፍስ ይማር» የሚሉት ቀዳሚዎቹ ናቸው። «ዶቼበሌውች እዴት አመሻችሁ የታምራት ኅልፈት ያሳዝነናል። ነፍስ ይማር! ለቤተሰቡ መፅናናትን እመኝለሁ» በዋትስአፕ የደረሰን መልእክት ነው። «ነፍሱን ይማርው ታምራት። የሱ አልበሞች ብዙ ወጣቶች የተፋቀሩበት ነው፤ እና ሁላችንም አዝነናል» የሚሉ አስተያየቶችም ደርሰውናል።

የውጭ ጉዳይ ሚንሥትር ወርቅነህ ገበየኹ ይፋዊ በኾነው የፌስቡክ ገጻቸው ከሐዘንተኞች ጋር ከተነሱት ፎቶግራፍ ጋር ቀጣዩን መልእክት ሐሙስ እለት አስፍረዋል። «ድምፃዊ ታምራት ደስታ በትናንትናው እለት በድንገት ባጋጠመው ህመም ለህክምና በሄደበት ሕይወቱ በማለፉ የተሰማኝን ጥልቅ ሐዘን አገልፃለሁ፤ ለቤተሰቦቹና ለአድናቂዎቹ መፅናናትን እመኛለሁ።»

Symbolbild Tanzen Club Pop Musik Mikrophon Kopfhörer
ምስል Fotolia/U.P.images

«በድምጻዊ ታምራት ደስታ ሞት ጥልቅ ሐዘ ተሰምቶኛል ሁላችንም ወረፋ ጠባቂ ብንሆንም እንደዚህ ሳይታሰብ በድንገት ሲሆን ልብ ይሰብራልቢሆንም ታምራት በተወልን ራዎቹ እናስበዋለንለቤተሰቦቹና ለሙዚቃ አፍቃሪዎቹ ሁሉ መጽናናትን እመኛለሁ» ከሚል መልእክት ጋር ከአርቲስቱ ጋር የተነሳውን ፎቶግራፍ በቪዲዮ አቀናብሮ አያይዟል ታማኝ በየነ ነው።

ሐሙስ እለት በቅድሥት ሥላሴ ካቴድራል ቤተክርስቲያን ሥርዓተ-ቀብሩ የተፈጸመው ድምጻዊ ታምራት ደስታ ባለትዳርና የሦስት ወንዶች እና 2 ሴቶች ማለትም 5 ልጆች አባት ነበር። በ39 ዓመቱ ያረፈውን ድምጻዊ ታምራት ደስታ በተመለከተ ብርካን ፋንታ በትዊተር መልእክቱ፦ «ይኽ በጣም አስደንጋጭ ነው። በወጣትነቱ አለፈ። አፈሩን ያቅልልልህ ታምራት ደስታ» ብሏል። አብነት በበኩሉ ትዊተር ላይ፦ «ታምራት ደስታ ማረፉ ሊታመን የማይቻል» ሲል ጽፏል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ