1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኬንያ ምርጫ እና አስተምሕሮቱ

ነጋሽ መሐመድ
ሰኞ፣ ነሐሴ 1 2009

ኬንያዎች ከ2007ቱ ጥፋት ተምረዉ የጎሳ ልዩነታቸዉን ካጠበቡ የቀድሞዉ የጋና ፕሬዝደንት ድራማኒ ማሐማ እንዳሉት ዴሞክራሲ ለማያዉቀዉ ለምሥራቅ አፍሪቃ አብነት፤ ለመላዉ አፍሪቃም ምሳሌ የማይሆኑበት ምክንያት የለም።

https://p.dw.com/p/2hq41
Bildkombo Kandidaten Wahlen Kenia 2017

የኬንያ ምርጫና ላካባቢው ያለው አንደምታ

 

በአባቶቻቸዉ መራሩን የነፃነት ትግል እንደ ጥሩ ወዳጅ በጋራ አስተባበሩ።ለድል በቁ።በ1964 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ነፃ መንግሥት ሲመሠረት እንደ ፕሬዝደንትና ምክትል ፕሬዝደንት ነፃ ሐገራቸዉን መሩ።ግን ብዙ አልቆዩም።በ1966 ተጣሉ።ጆሞ ኬንያታ ፕሬዝደንት የቀድሞ ምክትላቸዉ ጃርሞጊ ኦዲንጋ ኦዲንጋ ዋነኛ ተቃዋሚ ሆኑ።ኬንያታ «ኡሑሩ» ነፃነት በሚል መርሐቸዉ ሲቀጥሉ፤ ኦዲንጋ not yet Uhurru ይሉ ገቡ።ነፃነት ገናነዉ-አይነት።ሁለቱ ሲወዳጁም፤ ሲጣሉም መከታ ጋሻቸዉ ከየጀርባቸዉ ያለዉ ጎሳ ነዉ።ኩኩዩና ሉዎ።ዘንድሮ-ልጆቻቸዉ ይፎካከራሉ።ኬንያ ነገ ትመርጣለች።
                            
ፕሬዝደንት ኡሑሩ ኬንያታ እና ዋና ተቀናቃኛቸዉ ራይላ ኦዲንጋ  ከዘር-ደም ዉርስ በተጨማሪ በፖለቲካዉም በርግጥ የየአባቶቻቸዉ ልጆች ናቸዉ።የፖለቲካ አንድነት ልዩነታቸዉ  ምክንያት ግን ከተለወጠዉ ዓለም-ዘመን ጋር ተለዉጧል። እንደአባቶቻቸዉ ነፃነት «አለ የለም አይከራከሩም።የምጣኔ ሐብት ዕድገት፤ የዲሞክራሲ ሥርፀት፤ ሙስና እና ድሕነት እንጂ።
                                    
«በናንተ ላይ እንተማመናለን።እስካሁን የሠራነዉን በግልፅ አይታችኋል።ይሕ ልማትና ዕድገት እንዲቀጥል እንፈልጋለን።»
ፕሬዝደንት ኡሑሩ ኬንያታ ናቸዉ።ኬንያታ ሥልጣን የያዙት በ2013 በተደረገዉ ምርጫ ነዉ።ከ2014 ጀምሮ የኬንያ ምጣኔ ሐብት በየአመቱ ባማካይ አምስት ከመቶ ያድጋል።ከሁለት ወር በፊት የመረቁት ናይሮቢን ከወደብ-ምዝናኛ ከተማይቱ ጋር የሚያገናኘዉ ረጅም ዘመናይ የባበሩን መስመር ለኬንያታ መስተዳድር ትልቁ የሥራ ዉጤት ነዉ።
በ1966 የኡሁሩ ኬንያታን እና የራይላ ኦዲንጋን አባቶች ካጣሉት ልዩነቶች ዋናዉ የካፒታሊስት-ኮሚንስቶች ፖለቲካዊ ሽኩቻ ነበር።የያኔዉ ፕሬዝደንት ጆሞ ኬንያታ መንግሥታቸዉ የቀድሞዋ የኬንያ ቅኝ ገዢ ብሪታንያን ጨምሮ ከምዕራባዉን ጋር  ያለዉን ግንኙነት ማጠናከር አለበት ባይ ነበሩ።ኦዲንጋ ኦዲንጋ ባንፃሩ ከምዕራቦቹ ጋር ያለዉን ግንኙነት ላላ አድረገን ከምሥራቆች በተለይም  ከሕዝባዊት ቻይና ጠንከር ያለ ወዳጅነት እንመስርት ይሉ ነበር።

Kenia Wahlen Raila Odinga
ምስል picture alliance/AP Photo/B. Curtis

ናይሮቢን ከሞባሳ ጋር የሚያገናኘዉን የባቡር ሐዲድ የዘረጉት ጆሞ ኬንያታ ይጠሏቸዉ የነበሩት ቻይኖች ናቸዉ።የጆሞ ኬንያታ ልጅ ኡሁሩ ኬንያታ ዘመናዊዉን የባቡር ሐዲድ ማዘርጋታቸዉን የኬንያታ ምጣኔ ሐብት የማሳደጋቸዉ ጉሉሕ ምሥክር አድርገዉ ለምርጫ ይቀሰቀሱበታል።
በ1960ዎቹ የሕዝባዊት ቻይናን ወዳጅነት በመፈገላቸዉ ከምክትል ፕሬዝደንትነት ሥልጣን የተወገዱት የጃራሞጊ ኦዲንጋ ኦዲንጋ ልጅ ራይላ ኦዲንጋ የምጣኔ ሐብቱን ዕድገት፤ የባቡር ሐዲድ ግንባታዉንም በሙስና የተለወሰ ይሉታል።
                                    
«ባሁኑ ጊዜ በሥራ ላይ በሚዉለዉ በያንዳዱ ሽልግ ልክ ሌላ ሽልግ ይሠራቃል።እግለሰቦች ኪስ ዉስጥ ይገባል።»
አለቅጥ የናረዉ የቦቆሎ ዱቄት ዋጋም ኦዲንጋ ኬንያታን ለመተካት አንዱ ምክንያት አድርገዉታል።ከማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች እስከ ቴሌቪዥን ክርክር፤ ከቤት ለቤት ቅስቀሳ አስከ አደባባይ ሰልፍ ፉክክር ደምቆ፤ ዓለም አቀፍ መገናኛ ዘዴዎችን ስቦ የሰነበተዉ የምርጫ ዘመቻ ተጠናቅቋል።ከ2007ቱ  ምርጫዉ ዉጤት በኋላ ከደረሰዉ ደም አፋሳሽ የጎሳ ብጥብጥ በቅጡ ያላገገመዉ ኬንያዊ ያሁኑን የምርጫ ዘመቻዉ በሥጋት-ፍርሐት ሲከታተለዉ ነዉ የሰነበተዉ።

Kenia Wahl Uhuru Kenyatta
ምስል AFP/Getty Images

ባለፈዉ ሳምንት አንድ የምርጫ ኮሚሽን ባለሥልጣን ሞተዉ መገኘታቸዉ የቀሰቀሰዉ ቁጣ የተፈራዉ እንዳይከተል አስግቶ ነበር።ኢትዮጵያዊ የፖለቲካ ተንታኝ አቶ ፍቅረማርያም መኮንን እንደሚሉት መወጋገዝ እና መወነጃጀል፤ የደመቀበት የተፎካካሪዎች ክርክር፤ ቁጣና ስሜታዊነት ያጠለባት የየደጋፊዎች ሰልፍ እና ቅስቀሳ የከፋ ሊከተል ነዉ የሚል ስጋት አጭሮ ነበር።ግን ዘመቻዉ በሰላም አበቃ።
                                             
ታሕሳስ ማብቂያ 2007  የተደረገዉ የምርጫ ዘመቻም ልክ እንደዘንድሮዉ ሲያሰጋ ቆይቶ በሰላም ነበር የተጠነቃቀዉ።የምርጫዉ ዉጤት ሲታወጅ ግን የበረዉ ሁሉ እንዳልነበር ሆነ።ኢትዮጵያዊ ጋዜጠኛ ብሩክ ተስፋዬ ያኔ እዚያዉ ኬንያ ነበር።
                                
የያኔዉ ፕሬዝደንት ምዋይ ኪባኪ እንደ አሁኑ ፕሬዝደንት ኡሑሩ ኬንያታ ወይም እንደ አባታቸዉ ሁሉ የኩኩዩ ጎሳ አባል ናቸዉ።ያኔ ቀስተደመና፤ ዘንድሮ ደግሞ ልዕለ-ጥምረት የሚል ሕብረት የፈጠሩትን  ተቃዋሚ ፓርቲዎችን በ2007ትም፤ በ2013ትም፤ ዘንድሮም የሚመሩት ራይላ ኦዲንጋ የሉዎ ጎሳ አባል ናቸዉ።የ2007ቱ ምርጫ ዉጤት እንደታወጀ በሁለቱ ጎሳዎች መካካል በተቀሰቀሰዉ ግጭት በትንሽ ግምት ከ1300 መቶ በላይ ሰዉ ተገድሏል።በብዙ ሺሕ የሚቆጠር ቆስሏል ተፈናቅሏልም።
በግጭቱ ላይ ተመስርቶ ዘ-አልትሜት ቻሌጅ የሚል ኖቤላ ያሳተመዉ ብሩክ እንደሚለዉ የያኔዉ ጥፋት በይፋ ከሚዘገበዉ በላይ ዘግናኝ ነበር።
                                       
በ2013ቱ ምርጫ የ2007ቱ እልቂት አልተደገገመም።የዘንድሮዉ ደግሞ ከሁለቱም ጊዜ የተሻለ ይሆናል የሚል ተስፋ ተጥሎበታል።እንዲያዉም የጋራ ብልፅግና ሐገራት ማሕበርን የታዛቢዎች ቡድን የሚመሩት የቀድሞዉ የጋና ፕሬዝደንት ጆን ድራማኒ ማሐማ  ምርጫዉ «የኬንያ ዴሞክራሲ መብሰሉ የሚታይበት ነዉ» ይላሉ።
                              
«ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጠዉ ምርጫ ነዉ።ወሳኝ ምርጫ ነዉ።እኔ ልዩ እመርታ የሚታይበት ምርጫ እለዋለሁ።የኬንያ ዴሞክራሲ መብሰሉ የሚታይበት ምርጫ ነዉ።ኬንያ በአሐገሪቱ ከሚገኙ ዴሞክራሲያዊ ሐገራት አንዷ መሆንዋ የሚመሰከርበት ነዉ።»ተቃዋሚዎቹ መሪ ራይላ ኦንዲጋንዳ በ2007ቱም፤ በ2013ቱም ምርጫ ተቃዋሚዎችን ወክለዉ የተፎካከሩ ናቸዉ።ፕሬዝደንት ኡሁሩ ኬንያታ በ2013 የተመረጡ፤ ከ2007ቱ ምርጫ በኋላ ለተቀሰቀሰዉ ደም አፋሳሽ ግጭት ተጠያቂ ተብለዉ የተከሰሱ ነበሩ።ኡሁሩ ኬንያታ በ2013ቱ ምርጫ እንዳይወዳደሩ ለማገድ የሞከሩ የያኔዉ የፍትሕ ሚንስትር ሞተዉ ተገኝተዋል።

Kenia Ezra Chiloba Leiter der Wahlkommission
ምስል Getty Images/AFP/T. Karumba

የፖለቲካ ተንታኝ ፍቅረማርያም መኮንን እንደሚሉትም ዋና ፖለቲከኞቹ ከዚሕ ቀደም የነበሩት ናቸዉ።የኬንያ ፖለቲካም ልክ እንደከዚሕ ቀደሙ ሁሉ ከጎሳ ተፅዕኖ አልተላቀቀም።የተቃዋሚዉ መሪ ራይላ ኦዲንጋ እንደሚሉት ሥጋቱ በሕዝቡ ዘንድ በርግጥ አሁንም አለ።ይሁንና በኦዲንጋ እምነት ሕዝቡ ካለፈዉ ጥፋት ብዙ በመማሩ ሰላማዊ ነዉ።በሥልጣን ላይ ያለዉ መንግሥት ግን «የምርጫዉን ዉጤት ለራሱ ለማድረግ የፈጠራ ፍራቻ በሕዝቡ ዘንድ እያሰራጨ ነዉ።» ይላሉ
                                
« መንግሥት በሕዝቡ ዘንድ አርቴፊሻል ፍራቻ እየነዛ ነዉ።ለብጥብጥ የተዘጋጁ ሰዎች አሉ ይላሉ።እነዚያ ሰዎች እነማን እንደሆኑ ግን አይናገሩም።ሰላም ነዉ።ሐገሪቱ በጣም ሰላም ናት።ሁሉም ኬንያዊ ድምፁን ለመስጠት ተዘጋጅቷል።መንግሥት ግን በምርጫዉ ሒደት ጣልቃ መግባት እንዲያስችለዉ በሕዝቡ ዘንድ ፍርሐት እየነዛ የፀጥታ አስከባሪዎች በየሥፍራዉ የሚያሰፍርበትን ምክንያት እየፈጠረ ነዉ።ሕዝቡ በነፃነት ፍላጎቱን እንዳይገልፅ ለማገድ ነዉ።»

ኬንያዎች ከ2007ቱ ጥፋት ተምረዉ የጎሳ ልዩነታቸዉን ካጠበቡ የቀድሞዉ የጋና ፕሬዝደንት ድራማኒ ማሐማ እንዳሉት ዴሞክራሲ ለማያዉቀዉ ለምሥራቅ አፍሪቃ አብነት፤ ለመላዉ አፍሪቃም ምሳሌ የማይሆኑበት ምክንያት የለም።የፖለቲካ ተንታኝ ፍቅርማርያም መኮንን እንደሚሉት ደግሞ በጎሳዉ ልዩነት፤ በሥጋት ፍራቻዉ መሐል እንኳ አሁን የመገናኛ ዘዴዎች ነፃነት፤ የተቃዊ ፖለቲከኞች መብት፤ የመንግሥት ተቋማት ገለልተኝነት ለተቀሩት የምሥራቅ አፍሪቃ አስተማሪ ነዉ።
                                  
የሚማር ካለ።የነገዉ ምርጫ ዉጤት የምሥራቅ አፍሪቃን የእስካሁን ፖለቲካዊ መርሕ ሊቀይርም ይችላል።እርግጥ ነዉ ፕሬዝደንት ኡሁሩ ኬንያታ እንዳሉት በድጋሚ ቢመረጡ የመንግስታቸዉ የዉጪም ሆነ የዉስጥ መርሕr አይለወጥም።የሶማሊያዉን አክራሪ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን አሸባብን እንዲወጋ የዘመተዉ የኬንያ ጦርም ዉጊያዉን ይቀጥላል።ራይላ ኦዲንጋ ግን ጦሩን ወደ ሐገራቸዉ ለመመለስ ቃል ገብተዋል።ኬንያ ጦሯን ወደ ሶማሊያ ሥታዘምት ኦዲንጋ ጠቅላይ ሚንስትር ነበሩ።
ጦሩ በ2011 ሶማሊያ ከሰፈረ ወዲሕ የአሸባብ ታጣቂዎች በተደጋጋሚ ኬንያን አሸብረዋል።በ2013 ዌስትጌት በተባለዉ የገበያ አዳራሽ እና ጋሪሳ ዩኒቨርስቲ ላይ የተጣሉት ጥቃቶች የሚጠቀሱ ናቸዉ።የኬንያ ጦር ጥር 2016 የገጠመዉ ሽንፈት ደግሞ እጅግ ከባድ ነዉ።150 ወታደሮች ተገድለዋል።ብዙ ተማርከዋል።ሶማሊያም እስካሁን ሰላም አልሆነችም።
ኦዲንጋ ጦሩን ለማስወጣት የሰጡት ምክንያትም ሶማሊያም ሠላም ላትሆን፤ ኬንያም ሰላሟን እያጣች ወታደሮቻችን መገደል የለባቸዉም የሚል ነዉ።የፖለቲካ ተንታኝ ፍቅረማርያም መኮንን ግን ኦዲንጋ ቢመረጡ እንዳሉት ጦሩን ከሶማሊያ ማስወጣታቸዉን ይጠራጠራሉ።
                                      
በነገዉ ምርጫ ከ19,6 ሚሊዮን ሕዝብ ድምፅ ለመስጠት ተመዝግቧል።ሕዝቡ ፕሬዝደንቱን፤ 67 ሴናተሮች ወይም የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባላትን፤ 349 የሕግ መምሪያ ምክር ቤት አባላትን፤ 47 አገረ-ገዢዎችን ይመርጣል።ለሴቶችና ለወጣቶች የተመደቡ መቀመጫዎች አሉ። አባቶቻቸዉን ከተኩት ፖለቲከኞች ዋናዉን መቀመጫ የሚቆጣጠረዉ ማንነት ብዙ አጓጉታል። ግን ያዉ ነገ ይለያል። ቸር ያሰማን። 

Kenia Wahlen Wahlmaterial in Nairobi
ምስል Reuters/B. Ratner

ነጋሽ መሐመድ

ኂሩት መለሰ