1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኮሪያዎች ስምምነት እና ዓለም

ነጋሽ መሐመድ
ዓርብ፣ ሚያዝያ 19 2010

የሰሜን ኮሪያዉ መሪ ኪም ጆንግ ኡን እና የደቡብ ኮሪያዉ ፕሬዝደንት ሙን ጄ-ኢን ያደረጉትን ስምምነት ከጃፓን እስከ ብሪታንያ፤ ከቻይና እስከ ዩናይትድ ስቴትስ የሚገኙ መንግሥታት በደስታ ተቀብለዉታል።

https://p.dw.com/p/2woN8
Korea-Gipfel 2018 Umarmung Kim und Moon
ምስል Reuters

የሰሜን ኮሪያዉ መሪ ኪም ጆንግ ኡን እና የደቡብ ኮሪያዉ ፕሬዝደንት ሙን ጄ-ኢን ያደረጉትን ስምምነት ከጃፓን እስከ ብሪታንያ፤ ከቻይና እስከ ዩናይትድ ስቴትስ የሚገኙ መንግሥታት በደስታ ተቀብለዉታል። የጃፓኑ ጠቅላይ ሚንስትር ሺንዞ አቤ ስምምነቱን ለአካባቢ ሠላም ተስፋ የሚሰጥ በማለት ደግፈዉታል። የዩናያትድ ስቴትሱ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ስምምነቱን ሰሜን ኮሪያን የኑክሌር ጦር መሣሪያ ትጥቅ ለማስፈታት ጠቃሚ ብለዉታል። የኮሪያ ልሳነ ምድር ዘላቂ ተኩስ አቁም ዉል መፈረም እንደሚገባዉም ትራምፕ አልሸሸጉም። ዩናይትድ ስቴትስ ሰሜን ኮሪያን የሚወጋ 30 ሺሕ ያክል ጦር ደቡብ ኮሪያ ዉስጥ አስፍራለች። የቻይና ዉጪ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ሁዋ ቹንዪግ እንዳሉት ደግሞ መንግሥታቸዉ ፓንሙንጆም ላይ የታየዉ ፈገግታ ጠላትን የሚያስወግድ ይሆናል ብሎ ያምናል።
«የዴሞክራቲክ ሕዝባዊት ሪፐብሊክ ኮሪያ እና የኮሪያ ሪፐብሊክ መሪዎች የወሰዱትን ታሪካዊ እርምጃ ከልብ እንደግፋለን። ፖለቲካዊ ፅናት እና ጥንካሬያቸዉን እናደንቃለን። ቻይና፤ ታሪካዊዉ ጉባኤ ቀና ዉጤት ያስከትላል ብላ ታምናለች። ቻይና አንድ ግጥም አላት፤ መጥፎዉን ጥፋት ሁሉ ወንድምነት ይበልጠዋል የሚል። ሁለቱ መሪዎች ፈገግታ ሲለዋወጡ ጠላት ጠፍቷል። በአዋስኝዋ መንደር ፓንሙንጆም የተደረገዉ ታሪካዊ ጉባኤ፤ ዘላቂ ሠላም ለማስፈን የሚደረገዉ አዲስ ጉዞ መጀመሪያ ነዉ።»
ሩሲያም የሁለቱን ኮሪያዎች መሪዎች ስምምነት ታሪካዊ እና ለአጠቃላይ ሠላም እጅግ ጠቃሚ ብላዋለች። ከክሬምሊን የወጣዉ መግለጫ እንደሚለዉ የኮሪያዎችን ጠብ ለማርገብ ሁለቱ ኮሪያዎች በቀጥታ እንዲወያዩ ሞስኮ ያላሳሰበችበት ጊዜ የለም። የብሪታንያዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ቦሪስ ጆንሰን ግን ከብዙዎቹ መንግሥታት መሪዎች እና ዲፕሎማቶች ጋር አልገጠሙም። የብሪታንያዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ስምምነቱን ያወደሱትን ወገኖች እንዲሕ አሏቸዉ «አትቸኩሉ፤ በጣም ተስፋ አታድርጉም።»

ነጋሽ መሐመድ 

አዜብ ታደሰ