1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

የውጭ ምንዛሪ እጥረት እና የጠቅላይ ምኒስትሩ መፍትሔዎች

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 10 2010

የኢትዮጵያ ኤኮኖሚ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ይፈትነው ይዟል። ጠቅላይ ምኒስትር አብይ አሕመድ የሹማምንቶቻቸውን የውጭ ጉዞ እና ብክነትን በመቀነስ መፍትሔ ለመሻት ሐሳብ አላቸው። ገንዘባቸውን በውጭ አገራት ያስቀመጡ አሊያም ያሸሹ እንዲመልሱ እስከ መማጸንም ደርሰዋል። የመፍትሔ ሐሳቦቻቸው ለውጥ ያመጡ ይሆን?

https://p.dw.com/p/2wHzs
Geldscheine
ምስል DW/E. Bekele Tekle

የውጭ ምዛሪ እጥረት ፈተና በኢትዮጵያ

የኢትዮጵያ መንግሥት የውጭ ምንዛሪ እጥረት ጠንቶበታል። አዲሱ ጠቅላይ ምኒስትር ችግሩ "ለሚቀጥሉት 15 እና 20 ዓመታት" የሚቀጥል መሆኑ አልጠፋቸውም። ጠቅላይ ሚንስትሩ ባለፈዉ ዕሁድ 500 ገደማ የኢትዮጵያ ባለወረቶችን ሰብስበው "በአጭር ጊዜ ውስጥ የምንፈታው ችግር አይደለም" ብለዋል። ጥቁር ተብሎ የሚጠራው የጎንዮሽ የውጭ ምንዛሪ ግብይት፤ የውጭ ንግዱ መዳከም፤ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የጀመሩት ዘመቻ፤ በመንግሥትም ሆነ በግሉ ዘርፍ ይታያሉ ያሏቸው ብክነቶች ለችግሩ መንስኤዎች መሆናቸውን ጠቅሰዋል። የችግሩ ብርታት ጠቅላይ ምኒስትሩ ገንዘባቸውን ከኢትዮጵያ ያሸሹ አሊያም በውጪ ያስቀመጡትን ወደ ሐገር እንዲያስገቡ እስከመማጸንም አድርሷቸዋል።

በእርግጥ ኢትዮጵያ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ወደ ውጪ ከሚሸሽባቸው የአፍሪቃ አገሮች አንዷ መሆኗን ከዚህ ቀደም የወጡ ዘገባዎች ይጠቁማሉ። በቀድሞው የደቡብ አፍሪቃ ፕሬዝዳንት ታቦ ምቤኪ የሚመራ እና ከአፍሪቃ የሚሸሸውን የገንዘብ መጠን የመረመረ የአፍሪቃ ኅብረት አጥኚ ቡድን ከጎርጎሮሳዊው 1970-2008 ባሉት አመታት ብቻ 16.5 ቢሊዮን ዶላር ከኢትዮጵያ ሳይሸሽ እንዳልቀረ ይፋ አድርጎ ነበር።

Abiy Ahmed Ali Ministerpräsident Äthiopien
ምስል Office of the Prime Minister-Ethiopia

ጠቅላይ ምኒስትር አብይ ከኢትዮጵያ ውጪ የተቀመጠው አሊያም የሸሸው የገንዘብ መጠን ምን ያክል እንደሆነ አልተናገሩም። «መልሱ» ብለው ሲማጸኑም ስም አልጠሩም። ጥያቄው የቀረበላቸው የውይይቱ ታዳሚዎችም በጭብጨባ ሲያጅቧቸው ለመመለስ መስማማታቸው ይሁን ጥያቄው በመቅረቡ በመደሰታቸው በእርግጥ የሚታወቅ ነገር የለም። የኢትዮጵያ የንግድ እና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዋና ፀሐፊ አቶ እንዳልካቸው ስሜ ጠቅላይ ምኒስትሩ ተማጽኗቸውን ሲያቀርቡ ጠንከር ያለ መረጃ እጃቸው ላይ ሊኖር እንደሚችል ይጠረጥራሉ። አቶ እንዳልካቸው "ከነበረው አለመረጋጋት፤ በቢዝነስ ስራው ውስጥ ካሉት ፈተናዎች፤ እምነት ከማጣት እና ደኅንነትን ከመፈለግ አኳያ እንዲህ አይነት ዝማሚያዎች አይኖሩም የሚል ድምዳሜ የለንም" ሲሉ ይናገራሉ። 

የምጣኔ ሐብት ልማት ጥናት ባለሙያው አቶ ብስራት ተሾመ "የውጭ ምንዛሪ እጥረት ስላለ ዱባይ ላይ አንድ የራስህን ድርጅት ታቋቁማለህ። እጅግ የተለመደው ጅቡቲ ላይ ነው። ከዚያ በኋላ ያ ድርጅት አገር ውስጥ ላለው ለራስህ ድርጅት እንደሸጠ ይደረግና የውጭ ምንዛሪውን ሌላ አገር የሚገኘው የራስህ ድርጅት ላይ እንዲቀር" የማድረግ አሰራር በባለወረቶች ዘንድ እንደሚታይ ያስረዳሉ። ባለሙያው ነጋዴዎች ችግር ውስጥ ሲገቡ የውጭ ምንዛሪውን ራሳቸው ጋር ለማስቀረት የሚጠቀሙበት ሥልት በሌሎች አገሮች የተለመደ እንዳልሆነ ታዝበዋል። 

የዓለም የገንዘብ ድርጅት IMF ባለፈው ጥር እንዳስታወቀው በጎርጎሮሳዊው 2016/17 መጨረሻ ኢትዮጵያ የነበራት ተቀማጭ የውጭ ምንዛሪ ተቀማጭ 3.2 ቢሊዮን ዶላር ነበር። ይኸ መጠን በሁለት ወራት ውስጥ ከውጭ ለሸመተቻቸው ሸቀጦች ካወጣችውም የገንዘብ መጠንም በታች ነው። በጎርጎሮሳውዊው የ2017/18 የበጀት አመት 8.5 በመቶ ገደማ ያድጋል ተብሎ ለተተነበየው የአገሪቱ ኤኮኖሚ ይኸው የውጭ ምንዛሪ እጥረት የከፋ ፈተና እንደሚሆንበት የዓለም የገንዘብ ድርጅት ገልጿል። ጫናው ደግሞ በተለይ በአምራቾች ላይ የጠና መሆኑን አቶ እንዳልካቸው ያስረዳሉ።ጠቅላይ ምኒስሩ የመፍትሔ ሐሳብ ብለው ያስቀመጧቸው እርምጃዎች አልጠፉም። የመንግሥት ሹማምንትን የውጭ ጉዞ እና የሐብት ብክነት መቀነስ የሚጠቀሱ ናቸው።

Bauboom in Addis Ababa, Äthiopien
ምስል picture alliance/dpa/D. Kurokawa

የኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ ግብይት እና ዝውውር ጥብቅ ቁጥጥር የሚደረግበት ነው። ከኢትዮጵያ ውጪ የሚደረጉ ክፍያዎች ሁሉ ፈቃድ የሚያስፈልጋቸው ሲሆን የምዛሪ አገልግሎት እንዲሰጡ ፈቃድ ያገኙ ተቋማት በብሔራዊ ባንክ ቁጥጥር ይደረግባቸዋል።የምጣኔ ሐብት ባለሙያዎችም ይሁኑ ዓለም አቀፍ ተቋማት የውጭ ምዛሪ እጥረቱ ሥር የሰደደው በውጪ እና ገቢ ንግድ መካከል ባለው መዛባት እንደሆነ ይስማማሉ። አገሪቱ የገጠማትን ፈተና በረዥም ጊዜ ለመወጣት ለዓለም ገበያ የምታቀርባቸውን ምርቶች በአይነትም ሆነ በብዛት ልታሰፋ እንደሚገባ በተደጋጋሚ ይመክራሉ። ጠቅላይ ምኒስትር አብይ ዘላቂ ላሉት የውጭ ምንዛሪ እጥረት መፍትሔ ይሆናሉ ብለው ባነሷቸው ሐሳቦች ችግሩን መቅረፍ የሚያስችሉ ሁነኛ መንገዶች አይደሉም ሲሉ ይተቻሉ። 

በሰኞው ውይይት የተካፈሉት  ወይዘሮ ጊዜሽወርቅ ተሰማ መጋበዝ የነበረባቸው ሰዎች ሳይጋበዙ መቅረታቸውን ታዝበዋል። ሸቀጦችን በማጓጓዝ ሥራ ላይ የተሰማራው «ጊዜ ኃላፊነቱ የግል ኩባንያ» ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ ወይዘሮ ጊዜሽወርቅ እንደሚሉት የግሉ ዘርፍ የገጠሙት አንገብጋቢ ጉዳዮች አልተነሱም ። መንግሥት በተሰማራባቸው የሥራ ዘርፎች ከግሉ ጋር እየተጋፋ መሆኑን የሚናገሩት ወይዘሮ ጊዜሽወርቅ የጠቅላይ ምኒስትር አብይ መንግሥት ሊሰራ ይገባል የሚሏቸው በርካታ ጉዳዮች አሉ። አቶ እንዳልካቸው ስሜ መንግሥት ከተወሰኑ የሥራ ዘርፎች እጁን ማውጣት አለበት በሚለው ሐሳብ ይስማማሉ። በቅድሚያ ግን «ፋታ የማይሰጡ» ላሏቸው ችግሮች መፍትሔ መሻት ያሻል።

ሙሉ ዘገባውን ለማድመጥ የድምፅ ማዕቀፉን ይጫኑ 

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ