1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የየካቲት 24 ቀን 2016 ዓ/ም የዓለም ዜና

Tamirat Geletaእሑድ፣ የካቲት 24 2016

https://p.dw.com/p/4d7Z6

 

 

የሊቢያ የባህር ሰርጥ ጠባቂዎች በሜድትራንያን ባህር የህይወት አድን ተግባሬን እንዳልከውን አስተጓጉለውኛል ሲል አንድ  የጀርመን ህይወት አድን የግብረሰናይ ድርጅት ከሰሰ

ኤስ ኦ ኤስ የተሰኘው የግብረሰናይ ድርጅቱ እንዳለው በሜድትራንያን ባህር ለአደጋ የተጋለጡ ስደተኞችን በመታደግ ላይ ሳለ ከሊቢያ የድንበር ጥበቃ የእርምታ ተኩስ ተከፍቶበታል። በዚህም ከሊቢያ ተነስተው በሶስት አነስተኛ ጀልባዎች ወደ አውሮጳ በመጓዝ ላይ የነበሩ በርካታ ስደተኞች ወደ ባህር ለመዝለል ተገደዋል። ወደ ባህር ከዘለሉት ስደተኞች ውስጥ 77ቱን መታደጉን ያስታወቀው ድርጅቱ አንድ ሰው የደረሰበት ሳይታወቅ ቀርቷል ብሏል። ስድስት የአንድ ቤተሰብ አባላት ደግሞ ተጠፋፍተዋል። የሊቢያ የድንበር ጠባቂዎች ለቀረበባቸው ወቀሳ እና ክስ መልስ እንዳልሰጡ አሶሽየትድ ፕረስ ዘግቧል ።  የአውሮጳ ህብረት ከጎርጎርሳውያኑ 2015 ጀምሮ ከሊቢያ የሚነሱ ስደተኞችን ለመግታት ለሊቢያ የድንበር ጥበቃ የገንዘብ ድጋፍ ያደርጋል። በስምምነቱ መሰረት የሊቢያ የድንበር ጠባቂዎች በባህር ላይ የሚያገኟቸውን ስደተኞች ወደ ሊቢያ የመመለስ ግዴታ አለባቸው።

 

በየመን የሁቲ አማጽያን በብሪታንያ መርከቦች ላይ ያነጣጠረው ጥቃታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታወቁ ።

አማጽያኑ ይህን ያሉት  በኤደን ባህረሰላጤ ስትቀዝፍ የነበረች እና  ንብረትነቷ የብሪታንያ ዩየሆነች  ሬቢማን የተሰኘች ግዙፍ መርከብ መትተው ካሰጠሙ በኋላ ነው። ባለፈው የካቲት 9 ቀን 2016 ዓ/ም በኤደን ባህረ,ሰላጤ ስትቀዝፍ የጸረ መርከብ ክሩዝ ሚሳኤል ጥቃት የደረሰባት መርከቧ መስጠሟን  የአሜሪካ ጦር ኃይል አረጋግጧል። በየመን አማጽያኑ የሚመሩት መንግስት ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሁሴን አል ኤዚ በኤክስ ገጻቸው ባጋሩት መረጃ  « የመን ተጨማሪ የብሪታንያ መርከቦችን ማስጠሟን ትቀጥላለች ፤ ለዚህ የሚመጣ ምላሽ ካለም ሂሳብ ማወራረዳችን ይቀጥላል» ብለዋል። የሁቲ አማጽያን በቀይ ባህር እና በኤደን ባህረ ሰላጤ የሚቀዝፉ የእስራኤል እና አሜሪካ እንዲሁም አጋሮቻቸው በሆኑ ሃገራት መርከቦች ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች መሰንዘር ከጀመሩ ሰነበቱ ። አማጽያኑ በመርከቦች ላይ ካደረሷቸው ጥቃቶች በኋላ አንድ ግዙፍ መርከብ ሲሰጥም ግን የብሪታንያው መርከብ የመጀመሪያው ነው ተብሏል።

 

ሰሜናዊ ቡርኪና ፋሶ ባለፈው  ሳምንት በትንሹ ለ170 ያህል ሰዎች ህልፈት ምክንያት የሆነ ግጭት ከተፈጠረ በኋላ በወታደራዊ ሁንታ በምትመራው ሀገር ሌላ ቀውስ እንዳይከተል አስግቷል።

ባለፈው የካቲት 17 ቀን 2016 ዓ/ም በምስራቃዊ ቡርኪና ፋሶ መስጊዶዝ እና የካቶሊክ ቤተክርስትያንን ኢላማ ያደረጉ የተለያዩ ጥቃቶች በርካቶችን ለሞት እና የአካል ጉዳት መዳረጋቸውን የአካባቢው አቃቤ ህግ ገልጿል። በጥቃቱ ከደረሰው የህይወት እና የአካል ጉዳት ባሻገር ብርቱ የንብረት ውድመት መድረሱን ያመለከተው የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘገባ በጥቃቱ በተለይ ሴቶች እና ህጻናት ሰለባ መሆናቸውን ገልጿል ። የሀገሪቱ በጥቃቶቹ አሁንም ድረስ የተረጋገጠ የጉዳት ዘገባ አለማውጣቱ ምናልባትም ጉዳቱ ከዚህ የከፋ እንዳይሆን አስግቷል። ይህንኑ ተከትሎም ቀደም ሲል ከ20 ሺ በላይ ሰዎች ህልፈት እና ለሚሊዮኖች መፈናቀል ምክንያት የነበረው ግጭት እንዳይባባስ ስጋት አጭሯል። ቡርኪና ፋሶ ከአልቃኢዳ ጋር ግንኙነት ካላቸው እና ራሳቸው እስላማዊ መንግስት ብለው ከሚጠሩ ጂሃዲስቶች ጋር መፋለም ከጀመረች ሰነበተች።

     

ሩሲያ ስድስት የአይ ኤስ ተዋጊዎች መግደሏን አስታወቀች፡፡

ታጣቂዎቹ  ትናንት ቅዳሜ በካውከሰስ ግዛት በተደረገ ድንገተኛ አሰሳ መገደላቸውን   የሩስያ ባለስልጣናት ገልጸዋል።

የሩሲያ  የፌዴራል ደህንነት አገልግሎት አደረኩ ባለው በዚሁ አሰሳ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የደረሰ ጉዳት የለም።  በግዛቲቱ ውስጥ በምትገኘው  የካራቡላክ ከተማ አንድ ህንፃ ውስጥ ታጣቂዎቹን ማግኘቱን የገለጸው የሩስያ የጸረ ሽብር ኮሚቴ ከተገደሉት ስድስቱ ተጠርጣሪዎች መሃከል ሶስቱ በጎርጎርሳውያኑ 2023 በፖሊስ ጣቢያ ላይ ጥቃት በመፈፀምና ሶስት የሩሲያ ፖሊሶችን በመግደል ይፈለጉ የነበሩ ናቸው ። በተጨማሪም በግዛቲቱ  በደረሱ ተደጋጋሚ የሽበር ጥቃቶች ላይ በመሳተፍ  በሽብር ወንጀል ሲፈለጉ የነበሩ መሆናቸውን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል፡፡

ምንም እንኳን ሩሲያ  በአይ ኤስ የሽብር ቡድን ጥቃት እምብዛም ተጋላች ሀገር ባትሆንም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን በተለይም የእስልምና ተከታዮች በብዛት በሚገኙባት ካውካሰስ ግዛት ስር በሚገኙ ከተሞች የሽብር ጥቃቶች ስለመፈጸማቸው መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ይፋ  የሆኑ አሃዛዊ መረጃዎች እንደሚያሳዩት  በተለይም በካውካሰስ ግዛት የሚገኙ ወደ 4,500 የሚጠጉ  ሩሲያውያን  ከአይ ኤስ ጋር ሲዋጉ ቆይተዋል።

 

በቶክዮ ጃፓን ዛሬ ማለዳ በተደረገ ማራቶን ኢትዮጵያዊቷ ሱቱሜ አሰፋ የስፍራውን ክብረወሰን በማሻሻል ጭምር አሸነፈች ።

ሱቱሜ ውድድሩን ለማሸነፍ 2:15:55  የወሰደባት ሲሆን የራሷን ምርጥ ሰዓት ከ2 ደቂቃ በላይ ማሻሻል ችላለች። በውድድሩ አምና አሸናፊ የነበረችው ኬንያዊት ሮዝመሪ ዋንጂሩ ሁለተኛ ስትሆን የዓለም ሻምፒዮናዋ ኢትዮጵያዊት አማኔ በሪሶ ሶስተኛ ሆኖ ገብታለች። በውድድር ትልቅ ግምት ተሰጥቷት የነበረችው ትውልደ ኢትዮጵያዊት ኔዘርላንዳዊቷ ሲፈን ሀሰን አራተኛ በመሆን ውድድሯን አጠናቃለች።   የኬንያውያን የበላይነት ጎልቶ በታየበት የወንዶች ምድብ ቤንሰን ኪፕሩቶ አሸናፊ ሆኗል። የገባበትም ሰዓት 2 ሰዓት ከሁለት ደቂቃ ከ16 ሰከንድ ሲሆን ለራሱ ምርጥ ሰዓት በውድድሩ ታሪክ ደግሞ ሶስተኛው ምርጥ ሰዓት ሆኖ ተመዝግቧል። የሀገሩ ልጆች ቲሞቲ ኪፕላጋት እና ቪንሰት ኪፕኬሞይ ሁለተኛ እና ሶስተኛ ሆነው ሲገቡ ለውድድሩ ከፍተኛ ግምት ተሰጥቶት የነበረው እና በርቀቱ የቀድሞ የክብረወሰን ባለቤት ኪፕ ቾጌ 10ኛ በመውጣት ውድድሩን አጠናቋል። በውድድሩ ላይ የተሳተፉት ኢትዮጵያውያን

ትናንት ምሽት በተካሄደው የግላስጎ የዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮና በሴቶች 3 ሺህ ሜትር ፍፃሜ ጉዳፍ ፀጋይ ሁለተኛ ወጥታ የብር ሜዳሊያ ስታሸንፍ  በተመሳሳይ ርቀት በወንዶች  ሰለሞን ባረጋ በ7:43.64 በመግባት 3ኛ ደረጃን በመያዝ የነሐስ ሜዳልያ ተሸላሚ ሆኗል፡፡ ውድድሩ ዛሬ ምሽትም ቀጥሎ ሲከናወን ኢትዮጵያውያን ለሜዳሊያ የሚጠበቁበት ውድድሮች ይካሄዳሉ።