1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ግጭት አይሎባቸዉ የሰነበቱት የደቡብ ክልል ከተሞች

ዓርብ፣ ሰኔ 15 2010

የደቡብ ክልል የወላይታ ዞን 5 አመራሮችና የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ በፈቃዳቸዉ ስልጣን ለመልቀቅ መወሰናቸዉን የክልሉ መንግስት ገለፀ። አመራሮቹ ለመልቀቅ የወሰኑት ባለፈዉ ሳምንት ግጭት ተከስቶባቸዉ በነበሩ የክልሉ ከተሞች ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ ዉይይት ባደረጉበት ወቅት፤ ለደረሰዉ የሰዉ ህይወት መጥፋትና ንብረት ዉድመት

https://p.dw.com/p/306oQ
Karte Äthiopien englisch

South Region coniflict - MP3-Stereo

 የአካባቢዉን አመራሮች «በፈቃዳችሁ ከስልጣን ልቀቁ» ማለታቸዉን ተከትሎ መሆኑ ታዉቋል።የክልሉ መንግስት በግጭቱ ተጠያቂ ይሆናሉ ያላቸዉን ተጠርጣሪዎች ምርመራ መቀጠሉም ተገልጿል። ከጠቅላይ ሚንስትሩ ዉይይት ወዲህ በአንዳንድ አካባቢዎች የተሻለ መረጋጋት መፈጠሩንና በማህበረሰቡ ዘንድ የእርቅ ዉይይት መጀመሩንም አንዳንድ የአካባቢዉ ነዋሪዎች ገልፀዋል።
ከሳምንት በፊት በተቀሰቀሰ ሁከት የሰው ሕይወት መጥፋትና የንብረት ውድመት ተከስቶባቸው ከነበሩት ከሃዋሳ ፣ከወላይታ ሶዶና ከዉልቂጤ ከተሞች  አመራር አካላትና ከህብረተሰቡ ጋር ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)  በያዝነዉ ሳምንት መጀመሪያ  ዉይይት ማካሄዳቸዉ ይታወቃል።
በዉይይቱ ወቅትም ግጭቱ የተቀሰቀሰባቸዉ አካባቢዎች የዞንና የወረዳ አመራሮች ለደረሰዉ ጥፋት ሃለፊነት እንዲወስዱና በፈቃዳቸዉ ስልጣን እልዲለቁ  ጠቅላይ ሚንስትሩ በዉይይቱ ወቅት ማሳሰባቸዉ ሲዘገብ ቆይቷል። ይህንን ተከትሎም በትናንትናዉ ዕለት  የወላይታ ዞን አመራር አካላት ስልጣናቸዉን በፈቃዳቸዉ ለመልቀቅ መወሰናቸዉን የደቡብ ክልል ቃል አቀባይ አቶ ሶሎሞን ሀይሉ ለዶቼ ቬለ አረጋግጠዋል።
ዘግይቶ በደረሰን ዜናም በዛሬዉ ዕለት የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ለዴህዴን የመልቀቂያ ደብባቤ ማቅረባቸዉ ታዉቋል።እንደ አቶ ሶሎሞን ገለፃ የመልቀቂያ ጥያቄ ያቀረቡት እነዚህ አመራሮች  የለዉጥ ሀይል ለመሆን እንጅ ጥፋተኛ ስለሆኑ አይደለም። ይሁን እንጅ በማጣራቱ ሂደት ጥፋተኛ ሆነዉ ከተገኙ ከተጠያቂነት ሊያመልጡ እንደማይችሉ ነዉ ያስረዱት።
ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸዉ  አንድ ስማቸዉ እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የወላይታ ሶዶ ነዋሪ እንደሚሉት ግን በሃዋሳ ከተማ ከተነሳዉ ግጭት ጋር ተያይዞ «በወላይታ ተወላጆች ላይ ጥቃት ተፈፅሟል »በሚል ህዝቡ በሰላማዊ መንገድ ተቃዉሞዉን እንዳያሰማ የአካባቢዉ አመራር በመከልከሉ ግጭት መፈጠሩን ጠቅሰዉ አመራሩ ጥፋት ፈፅሟል ባይ ናቸዉ። ከዚህ አኳያ የስልጣን መልቀቂያ ጥያቄዉ ተገቢ ነዉ ያሉት።
አቶ ሶሎሞን እንደሚሉት በግጭቱ የተፈናቀሉ ሰዎችን ወደ ነበሩበት ለመመመለስና ለማቋቋም አመራሩ ከተፈናቃዮችና ከአካባቢዉ ህብረተሰብ ጋር ዉይይት እያደረገ ነዉ። ይሁን እንጅ አመራሩ ህዝቡን ለማረጋጋት ካደረገዉ ጥረት ይልቅ  የጠቅላይ ሚንስትሩ የተረጋጉ የቅድሚያ  መልዕክትና በኋላም በአካባቢዉ ተገኝቶ ዉይይት ማድረግ ሁኔታዉን የበለጠ  የተረጋጋ እንዳደረገዉ የሃዋሳና የወላይታ ነዋሪዎች በስልክ ለዶቼ ቬለ ገልፀዋል።
በሌላ በኩል  የጉራጌና የቀቤና ብሄሮችን ንብረትና ህይወት ጉዳት ላይ የጣለዉን የዉልቂጤ ከተማ ግጭት በዘላቂነት ለመፍታት«ዘርማ»በሚል መጠሪያ የሚታወቁት  የአካባቢዉ ወጣቶች የእርቅ ዉይይት መጀመራቸዉን ለዚህ ማሳያ መሆኑን የወልቂጤ ዩንቨርሲቲ መምህር የሆኑት አቶ ዳንኤል መኮንን ለዶቼ ቬለ ገልፀዋል።
ከግጭቱ ጀርባ« አሉ» የተባሉ ጥፋተኞችን ለመያዝ የፀጥታ ሀይሉ ምርመራ መጀመሩን የገለጹት አቶ ሶሎሞን  በአሁኑ ወቅት በሃዋሳ ከተማ ብቻ ወደ 600 መቶ የሚደርሱ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸዉን አብራርተዋል።
በግጭት ተቀስቅሶባቸዉ በነበሩት በሃዋሳ፣ በወላይታ ሶዶና በዉልቄጤ ከተሞች በአጠቃላይ የ17 ሰዎች ህይወት መጥፋቱን፣በርካቶች ለአካል ጉዳት መዳረጋቸዉንና 16 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ከቤት ንረታቸዉ መፈናቀላቸዉን ቃል አቀባዩ ጨምረዉ አመልክተዋል።

Äthiopien Industriepark Hawassa
ምስል Imago/Xinhua/M. Tewelde

ሙሉ ቅንብሩን የድምፅ ማዕቀፉን ከፍተዉ ያድምጡ።

ፀሐይ ጫኔ
አዜብ ታደሰ