1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የደኅንነት ምክር ቤቱ መግለጫ እና የተሰጡ አስተያየቶች

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 17 2016

የሰላም ጥሪ ምንጊዜም ተቀባይነት ያለው ሀሳብ መሆኑን የገለፁ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች፤ ይልቁንም ፓርቲዎች መሰል ጥሪ ሲያደርጉ መቆየታቸውን በመግለጽ ሰሚ እንዳላገኙ ገልፀዋል። ይህ የመንግሥት ጥሪ እውነተኛ እና ለዘላቂ መፍትሔ ታምኖበት የተደረገ ስለመሆኑ ጥርጣሬ እንዳላቸውም አብራርተዋል።

https://p.dw.com/p/4fBgt
የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በሐገሪቱ አበይት ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ዉይይት የሚደረግበት ነዉ
የገዢዉን የብልፅግና ፓርቲን ጨምሮ የፖለቲካ ፓርቲዎችን የሚያስተናብረዉ ምክር ቤት ጉባኤ (ፎቶ ከክምችታችን)ምስል Solomon Muche/DW

ብሔራዊ የደኅንነት ምክር ቤት በወቅታዊ ሀገራዊ የደህንነትና ፀጥታ ጉዳዮች ዙሪያ ትናንት ባወጣው መግለጫ "የውስጥ አንድነት እጅግ ወሳኝ" መሆኑን በመጥቀስ መከፋፈል የሀገር ህልውናን አደጋ ላይ ይጥላል ሲል የአንድነት ጥሪ አድርጓል።"ዘላቂ ሰላምና ዘላቂ ብልጽግና ለማምጣት አዲስ የፖለቲካ ባህል የግድ ነው" ያለው ብሔራዊ የደኅንነት ምክር ቤቱ ችግሮች በሁሉን አካታች ሀገራዊ ምክክር፣ በሽግግር ፍትሕ እና በተሐድሶ ተግባራት እንደሚፈቱ ገልጿል።

የሰላም ጥሪ ምንጊዜም ተቀባይነት ያለው ሀሳብ መሆኑን የገለፁ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች፤ ይልቁንም ፓርቲዎች መሰል ጥሪ ሲያደርጉ መቆየታቸውን በመግለጽ ሰሚ እንዳላገኙ ገልፀዋል። ይህ የመንግሥት ጥሪእውነተኛ እና ለዘላቂ መፍትሔ ታምኖበት የተደረገ ስለመሆኑ ጥርጣሬ እንዳላቸውም አብራርተዋል። የፖለቲከኞች፣ የጋዜጠኞች፣ የያገባናል ባዮች እሥር በበዛበት ፣ጦርነትና ግጭት ባየለበት ፣ በተቋማት ላይ የገለልተኝነት ጥያቄ በሚነሳበይ ሁኔታ የአንድነት ፣ የሰላም ጥሪዎች በጎ ምላሽ የማግኘታቸው እድል ላይም አስተያየት ሰጪዎቹ ጥያቄ 

አንስተዋል።

ከተሰጡ አስተያየቶች መካከል ጥቂቱ 

"እንደ ሀገር ሰላም እንዲኖር ፣ ሀገሪቱ ወደተረጋጋ ሁኔታ እንድትመጣ ኢሕአፓ ይሻል። በተለይ አሁን ላይ በመንግሥት በኩል ፣ በገዢው ብልጽግና በኩል ያለው ነገር እውነተኛ ሰላም እንዲሆን የመፈለግ አይደለም""ግጭቶች አሉ፤ በነዚህ ግጭቶች ምክንያት የሰው ሕይወት ይጠፋል፣ ንብረት ይወድማል፣ ዜጎች ከቦታቸው ይፈናቀላሉ፣ እና በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ነው ያለችው ሀገራችን። ጦርነት የሚቆምበት ጥሪ እናደርግ ነበር፤ ያሰብነው ነገር አልሆነም"

መንግስት በቅርቡ ያደረገዉን የአንድነት ጥሪ ብዙ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ዉድቅ አድርገዉታል
የኦሮሞ ፌደራሊስ ኮንግረስ ፕሬዝደንት ፕሮፌሰር መረራ ጉዲያ የመንግስትን ጥሪ አልተቀበሉትምምስል DW/S. Wegayehu

"ጦርነቱ'ኮ አልቆመም።የተሳካ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ አልተካሄደም። ከየት ነው የሽግግር ፍትሕ የሚመጣው?ማን ነው የሽግግር ፍትሑን የሚያመጣው"?"ግጭቶች በሰላም እንዲወገዱ ፣ ውይይት እንዲካሄድ እያልን ያደረግናቸው ጥሪዎች ሁሉ አሁንም ቢሆን መልስ አላገኙም። ጦርነቱ እንዲያውም ተባብሶ ብዙ ሰው እየተጎዳ ነው፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቱም የከፋ ሁኔታ ላይ ነው ያለው። በመንግሥት በኩል ለሰላም ዝግጁ ነን፣ ሰላም እንፈልጋለን የሚሉ ድምፆች ብንሰማም ግን ያንን በተግባር ሊያሳይ የሚችል ጠቅላላ ብሔራዊ የሰላም መድረክ የማዘጋጀት ነገር ብዙም ጠንከር ብሎ አይታይም""ጋዜጠኞች ፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ፣ ፖለቲከኞች ካልተፈቱ ሀገራዊ ምክክሩ ላይ አንሳተፍም፤ መሳተፍም የለብንም። ምክንያቱም ከማን ጋር ነው እውነተኛ ምክክር ማድረግ የሚቻለው? ከማን ጋርስ ነው መነጋገር የሚቻለው ታሥረው"?

ሰለሞን ሙጬ

ነጋሽ መሐመድ

አዜብ ታደሰ