1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዳዳብ የስደተኞች መጠለያ አገልግሎት መስጠት አቁሟል

ማክሰኞ፣ ኅዳር 26 2010

በኬንያ የዳዳብ የሥደተኞች መጠለያ ጣቢያ ለስደተኞች የሚሰጠው ግልጋሎት ተስተጓጉሏል ተባለ። ችግሩ የተፈጠረው በመጠለያ ጣቢያው አስተዳደር እና በዙሪያው በሚገኙ ማሕበረሰቦች መካከል በተፈጠረ አለመግባባት ነው። በጣቢያው የሚገኙ ስደተኞች እንደሚሉት በየወሩ የሚደረገው የምግብ እደላም አልተደረገም።

https://p.dw.com/p/2onyp
Kenia Flüchtlingslager Dadaab
ምስል Getty Images/AFP/T. Karumba

ለስደተኞች ወርኃዊ የምግብ ዕደላ አልተፈጸመም

በኬንያ ዳዳብ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ አስተዳደር እና በዙሪያው በሚኖር ማህበረሰብ አባላት መካከል በተፈጠረ አለመግባባት ሰበብ ለስደተኞች የሚሰጡ አገልግሎቶች በአሁኑ ወቅት ተቋርጠዋል፡፡መጠለያ ጣቢያውን አሌንታ ያደረጉ ስደተኞች ከመሰራታዊ አቅርቦቶች እጥረት እና ደህነነት ጉዳይ ጋር በተገናኘ በችግር እና ስጋት ውስጥ ስለመሆናቸውም ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል፡፡
ባለፈው ሳምንት አጋማሽ ላይ ተባብሶ ጣቢያው የእለት ተዕለት ግልጋሎቶቹን እንዳይሰጥ ያገደው ተቃውሞና አለመግባባት የቅርብ ጊዜ ምክንያት በጣቢያው ውስጥ ተቀጥረው ይሰሩ ከነበሩ የማህበረሰቡ አባላት መካከል በርከት ያሉት ከስራ ከመቀነሳቸው ጋር የተገናኘ ነው፡፡
አቶ አለማየሁ ሆርዶፋ ለበርካታ ዓመታት በዳዳብ ውስጥ የኖሩ ስደተኛ ናቸው፤ ተቃውሞ የሚያሰሙ የማህበረሰብ አባላትና የመጠለያ ጣቢያው ባለስልጣናት እንደምን ለግጭት እንደበቁ የሚያውቁትን አጋርተውናል፡፡
ጄን ቦስኮ ሩሻትሲ የዳደብ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ የክንውን ሃላፊ ናቸው፡፡ ኬቲኤን በተባለ የሀገሪቱ ቴሌቭዥን ብቅ ብለው-በአቶ ዓለማየሁ ምስክርነት ውስጥ የሰማነው ዓይነት የሰራተኞች ቅነሳሳ በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል ፡፡የውሳኔውን ምክንያታዊነት ለማሳየት ጥረዋል፡፡
‹‹አሁን ካሉን ስደተኞች ቁጥር ጋር ስናነጻጽረው 50 በመቶ ሊሞላ ጥቂት የቀረው በእጃችን ያለው የስደተኞች ጉዳይ መዝገብ ነው ከ2011 የጎረጎሳዊያኑ አቆጣጠር ወዲህ ወደ ሶማሊያ የተመለሰው ከለጋሽ ማህበረሰቦች ይሰጡን የነበረውም ድጋፍ እየቀነሰ ነው፤ እኛም ካለው አቅርቦት ጋር በሚመጣጠን መልኩ ብቻ መዋቀር እና ማገልገል ይኖርብናል››  ነው ያሉት፡፡
በዳዳብ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ዙሪያ ሚኖሩ የጋሪሳ ግዛት ነዋሪዎች ቀደም ባሉት ጊዜያት ‹‹ስደተኞችና የስደተኞች መጠለያ ጣቢያው አስተዳዳር ደን መጨፍጨፍ እና ከሰል ማክሰልን በመሰሉ ስነምህዳር አውዳሚ ስራዎች እየተሳተፉ ነው ፡፡›› በሚል ጣቢያው ይዘጋ ስደተኞችም ወደ ሌላ ቦታ ይሸጋገሩ ዘንድ ሲጠይቁ ነበር፡፡
 ዳዳብ በሰሜን ምስራቅ ኬንያ ከሶማሊያ ድንበር 80 ኪሜ ርቆ የሚገኝ 26 ዓመታትን ያስቆጠረ በስፋቱም ከዓለም የስደተኛ መጠለያዎች ሁሉ የገዘፈ ጣቢያ ነው፡፡የኬንያ መንግስት ጣቢያው አልሸባብን ለመሰሉ ሃይሎች መሸሸጊያ ሆኗል በሚል በተደጋጋሚ ለመዝጋት መሞከሩን ተከትሎ በ100ሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ቦታውን ለቀው ወደ ሀገራቸው ገብተወል፡፡ገሚሱ ደግሞ ካኩማ ወደሚባለው በሀገሪቱ ሰሜን ምራብ ወደሚገኝ መጠለያ ጣቢያ ተሸጋግረዋል፡፡ሆኖም አሁንም 230ሺ ያክል ስደተኞች በካኩማ ይኖራሉ፡፡
የመጠለያ ጣቢያ አስተዳዳር አሁን ለተፈጠረው ችግር መፍትሄ ለማበጀት በዙሪያው ካሉ የማህበረሰብ ተወካዮች ጋር ውይይት መጀመሩን የሀገሪቱ የዜና ተቋማት እየዘገቡ ነው፡፡ሆኖም መጠለያው መደበኛ ስራውን ዳግም አለመጀመሩ የእኒህ ስደተኞችን ጭንቀት ጨምሯል፡፡የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከፍተኛ ኮሚሽን ለስደተኞቸ የኬንያ ቅርንጫፍ ጉዳዩን በተመለከተ ማብራሪያ እንዲሰጠን ቃል አቀባይዎ ሚስ ኢቮን ዲጌ ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም፡፡
 ሀብታሙ ስዩም

Kenia Flüchtlingslager für Flüchtlinge aus Somalia
ምስል picture-alliance/AP Photo/J. Delay
Kenia Dadaab-Flüchtlingslager UNHCR
ምስል Getty Images/S. Maina

ነጋሽ መሐመድ