1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የድርቅና የረሐብ ዑደት፤ ቃለ መጠይቅ

ማክሰኞ፣ የካቲት 15 2014

ኢትዮጵያ ግን ዛሬም ጦርነት ላይ ናት።ኢትዮጵያዉያን ዛሬም ለረሐብ ተጋልጠዋል።የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንደሚለዉ ኢትዮጵያን፣ ሶማሊያንና ኬንያን በመታዉ ድርቅ 13 ሚሊዮን ሕዝብ ለረሐብ ተጋልጧል።ከግማሽ የሚበልጠዉ ኢትዮጵያዊ ነዉ።6.8 ሚሊዮን።ቦረና፣ደቡብ ኦሞ፣አጋዴንናሌሎችም አካባቢዎች የሕዝቡ ሕልዉና መሰረት የሆኑት ከብቶች እየረገፉ ነዉ።

https://p.dw.com/p/47Qcr
Äthiopien I Der Hunger und die Reaktion der Welt auf die Hilfe in den Jahren 1984-85
ምስል Dawit Weldegiorgis

ከቀድሞዉ የኢትዮጵያ የርዳታ ማስተባበሪያና ማቋቋሚያ ኮሚሽነር ጋር የተደረገ ቃለ መጠይቅ

አርዶ ሐሰን ከሞት የተረፉ ፍየልና በጎችዋን እየነዳች፣ አራት ልጆችዋን አስከትላ፣ ነባር አካባቢዋን ጥላ ቀብሪ ዳሕር አጠገብ ደሳ ቀልሳለች።«ዝናብ ካልሰጠን ምን እንሆናለን?» ትጠይቃለች።ከብቶቹ ገሚሱ ታመዋል-ሁሉም ተርበዋል።ልጆቹ ደክመዋል። ድርቅ። ኢትዮጵያ። በ1965-እና 66 እንዲያ ነበር።በ1977 ሚሊዮኖች አለቁ።በ1985፣ በ1992፣ በ2003ም ብዙ ሚሊዮኖች ተራቡ።ዛሬም የከብት ሐብቷ እየረገፈ፣ ሕጻናትዋ እየተራቡ፣ 6.8 ሚሊዮን ዜጋዋ ምፅዋት እየተጠበቀ ነዉ።

 የዛሬ 3 ዓመት ግድም የኢትዮጵያ ባለስልጣናትን ቅንጡ መኪኖችን እናግዳለን ሲባል ሰምተን ነበር።ዛሬ የኢትዮጵያ ሹማምት ካንዱ ክልል ርዕሠ-ከተማ ወደ ሌላዉ ለመጓዝ ትልቁ፣ፈጣኑ፣ ይታገዳል ተብሎ የነበረዉ ምቹ መኪና አልመች ብሏቸዉ ልዩ የኮንትራት አዉሮፕላን ያዛሉ ማለትን ሰማን።ዕዉነት ይሆን? «እሳት በሌለበት አይጤስም» ብለን የሆነዉን እናዉሳ።

ወይዘሮ አርዶ ሐሰን ሞትን ሽሽት ከትዉልድ መንደሯ ብዙ ኪሎ ሜትሮች በዕግሯ ተጉዞ ቀብሪ ዳሕር አጠገብ ደርሳለች።ሰባ ከብቶችዋ፣ በጣሙን 4 ልጆችዋን ማትረፍ አለማትረፏን ግን ለፈጣሪ ከመስጠት ባለፍ እርግጠኛ አይደለችም።

Äthiopien I Der Hunger und die Reaktion der Welt auf die Hilfe in den Jahren 1984-85
ምስል Dawit Weldegiorgis

                                  

«በጣም ተጨንቄያለሁ።የሚበላና የሚጠጣ ምንም የለኝም።ቀጥሎ የሚሆነዉን አላዉቅም።በጣም የሚያሳስበኝ የልጆቼ ጉዳይ ነዉ።ልጆቼ እየተራቡ ነዉ።»

መስከረም 1፣ 1967 በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የተራጨዉ የዮናታን ዲምብልቢ ፊልም ንጉሠ ነገስት አፄ ኃይለ ስላሴ ለልደታቸዉ ከዉጪ ያስመጡትን ኬክ ከሚያሳየዉ ፊልም ጋር የተቀናበረ  ነበር።

ንጉሱ አንዴ ለልደታቸዉ ዉድ ኬክ ሲቆርሱ፣ ሌላ ጊዜ ለሞተ-ዉሻቸዉ የዕብነ በረድ መቃብር ሲያሳንፁ፣ ሌላ ጊዜ መሳፍንቱና መኳንንቱ ሲንደላቀቁ ሕዝብ መራቡ ያስቆጣዉ ኢትዮጵያዊ ለገዢዎቹ የሚራራ ልብ አልነበረዉም።

Äthiopien I Der Hunger und die Reaktion der Welt auf die Hilfe in den Jahren 1984-85
ምስል Dawit Weldegiorgis

ጋዜጠኛ ዲምብልቢ «ድብቁ ረሐብ» ያለዉ መቅሰፍት ከበሽታ ጋር ተዳብሎ አንድ መቶ ሺሕ ያሕል ሰዉ ገድሏል።ከ2500 ሺሕ በላይ አስርቧል።በመቶ ሺሕ የሚቆጠር አፈናቅሏል።ረሐቡ እንደ አልጋወራሽም፣ እንደ ንጉሠ፣ እንደ ንጉሠ-ነገሥትም ለ58 ዘመን ኢትዮጵያን የገዙትን አፄ ኃይለ ሥልሳን ከስልጣን ለማስወገድ አንዱ ምክንያት ሆነ።

 

ድርቅና ረሐቡ በኢትዮጵያዉያን ዘንድ ያሳደረዉ ንዴትና ቁጭት ጳዉሎስ ኞኞና ብጤዎቹን ብዕራቸዉን አስቀምጠዉ የልመና ኮሮጆ ሲያነሳሳ፣ የብርሐኑ ዘሪሁን ድርሰት፣ የፀጋዬ ገብረ መድሕን ቅኔ ይፈስ፣ የነ ጥላሁን ገሠሠ ሙዚቃን ያንቆረቁር ገባ።የፖለቲካ ለዉጥ ግርግር ፣ የተራዉ ሕዝብ ሐዘኔታ፤ የጋዜጠኛ፣ ደራሲ፣ ገጣሚ፣ ሙዚቀኞቹ ቁጭት ከአፍላ የአብዮት-አድሐሮት፣ ከሰሜን፣ከሁሉም በላይ ከምሥራቅ ጦርነት ጋር ተዳምሮ የፈጠረዉ ሆይ-ሆይታ ገለል-ቀለል-ከፈል ከማለቱ ኢትዮጵያ በሌላ ድርቅ ተመታች።በሌላ ረሐብ ተቃወሰች።1977።የከፋ ነበር።

አንዳድ ዘገቦች እንደሚጠቁሙት ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ ሰዉ በረሐብና ረሐብ በሚያስከትለዉ በሽታ ሞቷል።ከ6 ሚሊዮን የሚበልጥ ሕዝብ ተርቧል።ሻለቃ ዳዊት ወልደ ጊዮርጊስ ረሐብ እንደገና ፖለቲካዊ ሆነ ይላሉ።

የቀድሞዉ የኢትዮጵያ የርዳታ ማስተባበሪያና ማቋቋሚያ ኮሚሽነር ዳዊት ወልደ ጊዮርጊስ እንደሚሉት እንደ 1966ቱ ሁሉ 1977ቱ ረሐብም ፖለቲካዊ ሆነ።የምሥራቅ-ምዕራቦች ኃያላን መሻኮቻም ጭምር።

 ከኤርትራ እስከ ኦጋዴን፣ ከትግራይ እስከ እስከ ቦረና ሕዝብ ሲራብ ኢትዮጵያ ጦርነት ላይ ነበረች።የመንግስት ጦርና የያኔዎቹ የኤርትራ፣ የትግራይና የሌሎች አካባቢዎች ነፃ አዉጪዎች የሚያደርጉት ዉጊያ የሺዎችን ሕይወት፣ የሚሊዮኖችን ሐብት ንብረት ያጠፋ-ያጋይ ነበር።ጦርነቱ በረሐብ ለተጎዳዉ ሕዝብ ርዳታ እንዳይደርስ እንቅፋትም ነበር።

ለ1965-66ቱ ረሐብ  አፄ ኃይለ ስላሴንና አገዛዛቸዉን ተጠያቂ ያደረገዉ ደርግ ለ1977ቱ ድርቅና ረሐብ ተወቃሽ ተከሳሽ ሆነ።በተለይ ረሐቡ በጠናበት ወቅት የኢትዮጵያ ሠራተኛ ፓርቲን (ኢሠፓን) ለመመስረት ይጣጣር የነበረዉ ደርግ፣ የመሰብሰቢያ አዳራሽ አስገንብቷል፣ 3 መቶ ሺሕ ዶላር የሚያወጣ ዉስኪ ከዉጪ አስመጥቷል የሚለዉ ወቀሳና ትችት ሶሻሊስታዊዉን ሥርዓት ለማሳጣት ለሚፈልጉ ኃይላት ስብ የፕሮፓጋንዳ ቀለብ ነበር የሆነዉ።

Äthiopien I Der Hunger und die Reaktion der Welt auf die Hilfe in den Jahren 1984-85
ምስል Dawit Weldegiorgis

                                    

የዋሽግተን-ለንደን፣ የኦታዋ-ቦን-ሮም መሪዎች ሕዝባቸዉ ኢትዮጵያን እንዲረዳ  ተማፀኑ።የእነ መሐመድ ዓሚን ካሜራዎች ኢትዮጵያ ላይ አነጣጠሩ፣የእነ ቦብ ጊልዶፍ፣ የእነ ቦኖ Do they know it is Christmas፣ የእነ ማይክል ጃክሰን፣ የነ ሊዮንድ ሪቼ፣ የነስቲቭ ወንደር----የብዙዎች WE ARE THE WORLD ሙዚቃ ፈሰሰ።ርዳታዉም ጎረፈ።

                                

ድርቅ-ረሐቡ ግን እያሰለሰ ቀጠለ።በ1977 ድርቅና ረሐብ-ሰበብ ደርግን ሲወቅሱ፣ ሲከሱ፣ ሲያወግዙ የነበሩት ኃይላት የአዲስ አበባና የአስመራ አብያተ መንግስታትን ከያዙ በኋላም፣  ተደጋጋሚ ረሐብ ነበር።በ1985 እና በ1992 የደረሰዉ  በ10 ሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዉያንን ለረሐብ አጋልጧል።

የቀድሞ ወቃሽ፣ ከሳሽ አዉጋዞች በዘመናቸዉ ለደረሰዉ ተመሳሳይ ችግር ፈጥነዉ መልስ አለመስጣቸዉ እንዳስተዛዘበ፣ በተራቸዉ እንደተወቀሱ፣ እንደተወገዙ ከረሐብተኛዉ ሕዝብ በቀሙት ሐብት አንዴ ከቀድሞ ወዳጆቻቸዉ ከኤርትራ ገዢዎች ጋር፣ ሌላ ጊዜ «አማፂ» ካሏቸዉ ኃይላት ጋር ሲዋጉ መቶ ሺዎችን አስፈጅተዉ ሲንደላቀቁ ኖረዉ ሄዱ።

Äthiopien I Der Hunger und die Reaktion der Welt auf die Hilfe in den Jahren 1984-85
ምስል Dawit Weldegiorgis

ሌሎች መጡ።

ኢትዮጵያ ግን ዛሬም ጦርነት ላይ ናት።ኢትዮጵያዉያን ዛሬም ለረሐብ ተጋልጠዋል።የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንደሚለዉ ኢትዮጵያን፣ ሶማሊያንና ኬንያን በመታዉ ድርቅ 13 ሚሊዮን ሕዝብ ለረሐብ ተጋልጧል።ከግማሽ የሚበልጠዉ ኢትዮጵያዊ ነዉ።6.8 ሚሊዮን።ቦረና፣ ደቡብ ኦሞ፣አጋዴንና ሌሎችም አካባቢዎች የሕዝቡ ሕልዉና መሰረት የሆኑት ከብቶች እየረገፉ ነዉ።

የቀድሞዉ የኢትዮጵያ የርዳታ ማስተባበሪያና ማቋቋሚያ ኮሚሽነር ሻለቃ ዳዊት ወልደ ጊዮርጊስ በየጊዜዉ የሚከሰተዉን የድርቅና የረሐብ ዑደት ምክንያት፣ ፖለቲካዊ እድምታዉንና መፍትሔዉን ይጠቁማሉ።ሙሉ ቃለ መጠይቁን በድምፅ ለመስማት የሚከተለዉን ይጫኑ።

ነጋሽ መሐመድ

አዜብ ታደሰ