1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጋምቤላ ክልል ፀጥታ ከአደባባይ ተኩስ በኋላ

ሐሙስ፣ መጋቢት 12 2016

በጋምቤላ ከተማ ሰኞ መጋቢት 9 ቀን፣ 2016 ዓ.ም ጠዋት አራት ሰዓት ገደማ በአንድ የትራፊክ ፖሊስ ላይ ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ በከተማው ተቋማት ዝግ ሆነው መቆየታቸውን ያነጋገርናቸው የከተማ ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡

https://p.dw.com/p/4dyu3
የጋምቤላ ከተማ ከፊል ገጽታ
የጋምቤላ ከተማ ከፊል ገጽታ ። ፎቶ፦ ከክምችት ማኅደርምስል Negassa Desalegn/DW

አንድ የትራፊክ ፖሊስ ላይ ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ ውጥረት ነበር

ጋምቤላ ክልል ውስጥ በዜጎች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች አሁንም መቀጠላቸውን የጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ ።  ሰኞ ዕለት በከተማው ዋና አደባባይ ላይ በተከፈተው ተኩስ አንድ የትራፊክ ፖሊስ በጥይት ተመቶ  ከፍተኛ ጉዳት እንደ ደረሰበት ነዋሪዎች ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል ። ከጉዳቱ በኋላ ለአንድ ቀን ተቋማት ዝግ ሆነው መቆየታቸውንም  ገልጸዋል፡፡ ከትናንት በስትያ ጀምሮ ደግሞ ሁሉም ተቋማት ወደ ሥራ መግባታቸውን ተነግረዋል፡፡ ከኢታንግ ልዩ ወረዳም ባለፈው ሳምንት በአንድ ገጠራማ ስፍራ በሁለት ሰዎች ላይ የመቁሰል አደጋ መድረሱን ጠቁመዋል፡፡ በዚህ አካባቢ አልፎ አልፎ የሚከሰቱ ጥቃቶችና ግጭቶች በነዋሪው የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ስጋትና ተጽእኖ ማሳደሩን ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡ 

በጋምቤላ ከተማ  ሰኞ መጋቢት 9 ቀን፣ 2016 ዓ.ም ጠዋት አራት ሰዓት ገደማ በአንድ የትራፊክ ፖሊስ ላይ ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ በከተማው ተቋማት ዝግ ሆነው መቆየታቸውን ያነጋገርናቸው የከተማ ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡ በዕለቱ ጥቃቱ የደረሰው  በዋና የከተማ አደባባይ ላይ ብዙ ሰዎች ሲንቃቀሱ በነበረበት ሰዓት ድንገት እንደሆነም ስሜ አይጠቀስ ያሉን አንድ ነዋሪ አመልክተዋል፡፡  በከተማው መሰል ጥቃቶች የተለመዱ መሆኑን የሚናገሩት ነዋሪው ባለፈው ሳምንት በአካባቢው ባልታወቁ ሰዎች ሁለት ጊዜ ጥቃት መድረሱን ጠቁመዋል፡፡

ሌላው የከተማው ነዋሪም በጋምቤላ ከተማ ሰኞ የደረሰው ጥቃት ሕገ ወጥ የጦር መሳሪያ በታጠቁ ሰዎች እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ በጥቃቱም አንድ የትራፊክ ፖሊስ በጥይት ተመተው ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰበት አመልክተዋል፡፡ በሞተር እና በባለሦስት እግር ተሽከርካሪ ባጃጅ ውስጥ  ግለሰቦች ላይ ተደጋጋሚ ጥቃቶች እየደረሱ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡ በአካባቢው ሰዎች ከስጋት ነጻ ሆኖ መንቀሳቀስና መስራት አለመቻላቸውን ገልጸው  በከተማው የግል እና የመንግስት ተቋማት አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን አስታውቋል፡፡ በክልሉ በኢታንግ ልዩ ወረዳም አልፎ አልፎ በሰው እና ንብረት ላይ ጉዳት እየደረሱ እንደሚገኝ ነዋሪ ተናግረዋል፡፡ በወረዳው ትናንትም የተኩስ ድምፅ መሰማቱንና የደረሰ የጉዳት መጠን አለመታወቁን አብራርተዋል፡፡

ጋምቤላ ክልል ውስጥ በዜጎች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች አሁንም መቀጠላቸውን የጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ ። 
ጋምቤላ ክልል ውስጥ በዜጎች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች አሁንም መቀጠላቸውን የጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ ። ፎቶ፦ ከክምችት ማኅደርምስል Negassa Desalegn/DW

በጋምቤላ ከተማ ደርሰዋል ስለ ተባለው ጥቃትና ፀጥታን በተመለከተ ከተማው ከንቲባ ከማክሰኞ ዕለት ጀምሮ በተደጋጋሚ ስልክ ብንደውልም ስብሰባ ላይ በመሆናቸው ስለጉዳዩ ማብራሪያ መስጠት እንደማይችሉ ተናግረዋል፡፡ ከክልሉ ኮሙኒኬሽንም ተጨማሪም መረጃ መረጃ ለማግኘት ያደረኩት ተደጋጋሚ ጥረት እንዲሁ አልሰመረም፡፡ በጋምቤላ ክልል  በኢታንግ ልዩ ወረዳና በጋምቤላ ወረዳ ከግንቦት 2015 ዓ.ም እስከ መስከረም 2016 ተደጋጋሚ ግጭቶች መከሰታቸውንና በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወት ማለፉን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የካቲት 20/2016 ዓ.ም ባሰራጨው ዘገባው አመልክተዋል፡፡ በተለያየ ወቅት የተከሰቱ ግጭቶችን ለማስቆም በክልሉ አበረታች የሆኑ እርምጃዎች እየተወሰደ እንደሚገኝ ኮሚሽኑ በዘገባው ጠቁመዋል፡፡

ነጋሣ ደሳለኝ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ታምራት ዲንሳ