1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጠቅላይ ሚንሥትር አብይ ጉዞና ኤች አር 128 

ዓርብ፣ ሚያዝያ 5 2010

በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች እና መልካም አስተዳደር ላይ የሚያተኩረው ኤች አር 128 በዩናይትድ ስቴትስ ሕግ መምሪያ ምክር ቤት መጽደቁ የሳምንቱ አቢይ መነጋገሪያ ነበር። የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት ጥንቅራችን ርእስ ነው። የጠቅላይ ሚንሥትር አቢይ አህመድ የአምቦ ጉብኝት እና የኅብረተሰቡ የለውጥ ተማጽኖንም ይዳስሳል።

https://p.dw.com/p/2vygU
USA Kapitol in Washington
ምስል Getty Images/AFP/S. Loeb

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ጠቅላይ ሚንሥትር አቢይ አህመድ የአምቦ ጉብኝት እና የኅብረተሰቡ የለውጥ ተማጽኖን ይዳስሳል። በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች እና መልካም አስተዳደር ላይ የሚያተኩረው ኤች አር 128 በዩናይትድ ስቴትስ ሕግ መምሪያ ምክር ቤት መጽደቁም የሳምንቱ አቢይ መነጋገሪያ ነበር። 

ጠቅላይ ሚንስትር አቢይ አህመድ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን እንዲያነሱ፤ የለውጥ አቅጣጫቸውንም እንዲያመላክቱ የሚወተውቱ ጥያቄዎች በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች እየተነሱ ነው። ከተለያዩ የማኅበረሰቡ አባላት ጋር ከጀመሩት ንግግር ባሻገር ሌሎች ጉዳዮችን ለመመልከት ጊዜ ያስፈልጋቸዋል ሲሉ የሚሞግቱም አሉ። አስተያየቶቹን አሰባስበናል። በዚህ ሳምንት የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ላይ ጎልቶ የወጣው ሌላኛው ርእስ በዩናይትድ ስቴትስ ባለሥልጣናት ለሕግ መምሪያ ምክር ቤት ቀርቦ የጸደቀው ኤች አር 128 የተባለው ረቂቅ ውሳኔ ነው። ረቂቁ  በኢትዮጵያ፤ ገዢው መንግሥት ሰብአዊ መብቶችን እንዲያከከብር ብሎም ለመልካም አስተዳደር ትኩርት እንዲሰጥ ይጠይቃል። ቃኝተናዋል፤ አብራችሁን ቆዩ!

በሳምንቱ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች መነጋገሪያ ከኾኑ ጉዳዮች መካከል የጠቅላይ ሚንሥትር አቢይ አህመድ በአንቦ ከተማ ያደረጉት ንግግር ይገኝበታል። በሺህዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች የጠቅላይ ሚንሥትሩ ንግግርን በሥፍራው ተገኝተው ያደመጡ ሲኾን፤ ይኽን መልእክት የያዘው የቪዲዮ ምስልም በትዊተር እና ፌስቡክ ተንሸራሽሯል። በጠቅላይ ሚንሥትሩ ንግግር በመደመም አድናቆት የሰጡም ትችት እና ተቃውሞ የሰነዘሩም ነበሩ። 

በትዊተር፣ እና በፌስቡክ ብሎም በዋትስአፕ ከተሰጡት የድጋፍ እና የትችት አስተያየቶች የትዊተሮቹን እናስቀድም። የቀድሞ የአዲስ ነገር ጋዜጣ አዘጋጅ አቢይ ተክለማርያም በትዊተር ገጹ ቀጣዩን መልእክት በእንግሊዝኛ አስፍሯል። «አቢይ ሰዎችን ማነጋገር ይወዳል» በማለት ይንደረደራል አቢይ ጠቅላይ ሚንሥትር አቢይን ሲገልጣቸው። «በተመሳሳይ ጸረ-ሽብር ሕጉን፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ሕጉን፣ የሚዲያ ሕጉን ምክር ቤቱ እንዲያነሳ ሊጠይቅ እና ሀገሪቱ ለፖለቲካዊ ፉክክር መድረኩን ክፍት ስለማድረጓ ዝግጁነቷን ሊያመላክት ይችላል» ያለው አቢይ ያን ለማድረግ ከ1997 በፊት ወደነበረው መመለስ  ብሏል። 

Äthiopien Premierminister Dr. Abiy Ahmed
ምስል Oromia Government Communication Affairs Bureau

«አካሄድ አካሄድ!» ስትል ጽሑፏን የጀመረችው ሐና ጫላ፦ «የቀድሞው ሰርዐት ስትሉ፤ ከዶክተር አብይ በፊት የነበረውን ኢህአዴግ ነው የምናስገባው ወይስ ደርግን ነው? ግራ ተጋባን እኮ» ብላለች። 

በፌስቡክ ወደተሰጡ አስተያየቶች እንሻገር። «እናመሰግናለን ክቡር ጠቅላይ ምኒስትር አሁን ከሁሉም ነገር በላይ የሆነው አንድነትና ሰላም እየሸተተን ነው» በሞገስ ሀረጎት የተሰጠ አስተያት ነው። 

ዘለኒውም አጄ በሚል የፌስቡክ ስም የቀረበ ጽሑፍ፦ «ከዚህ በፊት በነበረው ሰው ድክመት ላይ ተነስቶ የራሱን ተወዳጅነት /ጥንካሬ ለመገንባት የሚታትር ሰው ብዙ እርቀት እይጓዝም» ሲል ይነበባል። «አብይ የበፊቱን በሚያወግዝ መልኩ "ከአሁን በኃላ " በሚሉ ቃላቶች የታጨቀ ንግግር ነው የሚናገረው። በከዚህ በፊቱም አመራር ላይ እኮ እሱም ነበረ፣ አሁን መቼስ አዲስ ጭንቅላት አላስገጠመ» ብሏል። 

ማንኩሳ አዲስ ደግሞ፦«የውስጥ አርበኛ ባንሆን ጥሩ ነው ገና ጠቅላይ ሚ/ትሩ ስራቸውን እንኳን በወጉና በአግባቡ ሳይጀምሩ እንደዚህ ነው እንደዝያ ነው ባንል ጥሩ ነው» የሚል አስተያየት ሰጥቷል። 

ሣላኅዲን ሰኢድ አኅመድ በአጭሩ፦«...."ያው በገሌ ነው አለች ድመት» ሲል፤ ብርሃን ኃይለ ሥላሴ በበኩሉ፦«አትፍረድ ይፈረድብሀል,,, ይቅር ለፈጣሪ ማለት ግን ሰላም ፍቅር ያነግሳል በደልን ያስረሳል» ብሏል። «ጨዋታው ተጀመረ» የአቢይ ሙሉጌታ አስተያየት ነው። 

ኤች አር 128 የተባለው የውሳኔ ሐሳብ በዩናይትድ ስቴትስ ሕግ መምሪያ ምክር ቤት መጽደቁ በሣምንቱ ዋና የመነጋገሪያ የነበር ርእሰ-ጉዳይ ነበር። ውሳኔ ሐሳቡ በኢትዮጵያ የተፈጸሙ ግድያዎች እንዲጣሩ፣ የታሰሩ እንዲፈቱ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲነሳ እና አፋኝ የተባሉ ሕግጋት እንዲሻሩ ይጠይቃል፡፡

የውሳኔ ሐሳቡ ከመጽደቁ ቀደም ባሉት ጊዜያት በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የምክር ቤት አባላቱን ለማሳመን ከፍተኛ ዘመቻ ተከናውኗል። የዘመቻው ተሳታፊዎች በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኙ የኮንግሬስ አባላትን የትዊተር አድራሻ በማያያዝ ድጋፍ እንዲሰጡ በተደጋጋሚ ወትውተዋል። የውሳኔ ሐሳቡ መጽደቁ የዘመቻው ተሳታፊዎችን እና ሌሎች የውሳኔው ደጋፊዎችን እጅግ አስደስቷል። የውሳኔው ተቃዋሚዎችን በዛው መጠን አበሳጭቷል።  

Äthiopien - Parlament
ምስል DW/Y. Gebregziabher

በዩናይትድ ስቴትስ ሕግ መምሪያ ምክር ቤት ውሳኔው እንዲጸድቅ ድጋፋቸውን ለገለጡት አባላት በተለይ በትጋት ለተሳተፉት ማይክ ኮፍማን እና ክሪስ ስሚዝ ለተባሉት የኮንግሬስ አባላት ከፍተኛ ምሥጋና አቅርበዋል። ማይክ ኮፍማን፦ በኮሎራዶ  ግዛት የስድስት የምርጫ ወረዳዎች ተወካይ ሲኾኑ፤ ክሪስ ስሚዝ የኒው ጄርሲ አራተኛውን የምርጫ ወረዳ ይወክላሉ። እነዚህ ሁለት የዩናይትድ ስቴትስ የሕግ መምሪያ ምክር ቤት አባላትን ኢትዮጵያውያን «ውለታችሁን መቼም አንረሳም» ሲሉ አወድሰዋል።  

«ፕራውድ ኢትዮጵያ» በሚል የትዊተር አድራሻ ለማይክ ኮፍማን የቀረበ መልእክት እንዲህ ይነበባል። «በትጋት ላደረጉት በተጨቆነው የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ስም እጅግ በጣም አመሠግናለሁ ማለት እፈልጋለሁ። ኢትዮጵያ መቼም አትረሳዎም።»

በሁለቱ ፖለቲከኞች እና የውሳኔ ሐሳቡን ያጸደቁትን የዩናይትድ ስቴትስ ከፍተኛ ፖለቲከኞች ያወገዙም አሉ። የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ ውሳኔው «ወቅቱን ያልጠበቀ እና ያልተገባ ነው» ሲል ተችቷል። 

«እኔ ምለው..... እስከ ዛሬ የት ነበሩ??» ሲል የሚንደረደረው ሞሀመድ ዩሱፍ ነው በፌስቡክ መልእክቱ። «አሁን ገና የሰላም አየር መተንፈስ መጀመራችንን እንደሰሙ አፀደቅን ምናምን እሚሉን? ለምን አስፈለገ?» ሲል አጠይቋል። በውሳኔ ሐሳብ የተነሱትን ጥያቄዎች በተመለከተም ጽሑፉን ሲቀጥል፦ «የአሁኑ ጠ/ሚ እንደሚያደርጋቸው ባለሙሉ ተስፋ ነን። ያፀደቁት ነደን ካለቅን በኋላ ለምን ሆነ? ስንት ዓመት ግፍ ተሰራብን? ተገለልን? በዘር ተከፋፍለን አንዱ በይ ሌላው ተመልካች፣» የሚል አስተያየት አስፍሯል። 

ጉራቻ ጉማባሱ የተባለ አስተያየት ሰጪ፦ «ለወያኔዎቹ የመጨረሻዉ የራስ ምታትና ኮንትሮባንዳቸውን ዋጋ ያሳጣ ውሳኔ ስለሆነ ይወተውታሉ ግን ማምለጥ አይችሉም» ብሏል።

Äthiopien Regierung Soldaten ARCHIV
ምስል picture alliance/AP Photo/ltomlinson

«የኢትዮጵያ ችግር በኢትዮጵያውያን እንጂ በአሜሪካውያን ሊፈታ አይችልም» የወርቁ ዋንታላ አስተያት ነው። «ወያኔዎች ምንም አይነት በደል ካልሰሩ HR 128 የተሰኘውን ሕግ ለምን እንደዚ አጥብቀው ጠሉት ????» ኢትዮ ቡቹ በሚል የፌስቡክ አድራሻ የቀረበ ጽሑፍ። ማይክ ሐረር፦ «የኢትዮጵያ አለቃ አሜሪካ ሳትሆን ህዝቦቿ ናቸው ። ሰብአዊ መብት ካወቁ በሶርያ ምንም በማያውቁት ህፃናት ላይ ቦምቦችን ለምን ያዘንባሉ» ሲል ዮሴፍ ደሳለኝ፦ «መግለጫ ብቻ ከሆነ ለምን እንዳይፀድቅ ጣሩ??? ሀሀሀሀ ገና ይቀጥላል» የሚል አስተያየት ሰጥቷል። 
«ዶ/ር አብይ ካወቁበት አሁን የፀደቀውን HR128 ረቂቅ ሕግ እንደ ግባት ሊጠቀሙበትና የያዙትንም እቅድ ሊያሳኩበት የሚችሉበትን እድል ይዞላቸው መጥቶላቸዋል» ኦሮአማ በሚል የትዊተር አድራሻ የቀረበ ጽሑፍ ነው። 

ነጋሣ ኢብሣ የውሳኔው መጽደቅን የተቃወመው በዚህ መልኩ ነው። «HR128 ለማስፈፀም የምሯሯጡት ዲያስፖራዎች ፀባቸው ከኢህአዴግ ጋር ነዉ ወይስ ከኢትዮጲያ እስቲ ይንገሩን። HR128 ዓላማዉ የኢትዮጲያን መንግስት ስልጣንና ተግባር በመድፈቅ ሙሉ በሙሉ በምዕራባዉያን ሕግ ለመተካት ያለመ ተግባር ነዉ» ብሏል፡፡

ክሪስቶፈር መኮንን ደግሞ፦ «ኤች አር 128 ሕግ እንዲኾን ደግሞ እንግፋ» የሚል አስተያየት ሰጥቷል። 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ