1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 14 2010

ከሰሞኑ የወጣ አንድ ጥናት የአየር ብክለትን ጨምሮ በአካባቢ ብክለት እና ንፅህናዉ ባልተጠበቀ ዉኃ ምክንያት በመላዉ ዓለም በየዓመቱ የሚሞተዉ ሰዉ ቁጥር ጦርነት እና የተፈጥሮ ቁጣ ከሚያስከትለዉ የሟቾች ቁጥር እንደሚበልጥ ያመለክታል። በተለይም የአየር ብክለቱ ለልብ እና ለመተንፈሻ አካላት የጤና ችግር እንዲሁም ለደም ግፊት መዘዝ መሆኑ ተገልጿል።

https://p.dw.com/p/2mQt6
China Smog in Shenyang
ምስል picture-alliance/dpa/Imagechine/J. Xu

የአየር ብክለት የበርካቶች ሞት ዋና ምክንያት እየሆነ ነዉ፤

በመላዉ ዓለም በዉኃ እና አየር ብክለት ምክንያት የሚሞተዉ ሰዉ ቁጥር ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ መሄዱን ላንሰት የተሰኘዉ ጤናን የሚመለከት የምርምር ሥራዎች የሚወጡበት መጽሔት ከሰሞኑ ባወጣዉ ጥናት ዘርዝሯል። የጥናቱ ማጠቃለያ እንደሚያሳየዉ ላለፉት አስርት ዓመታት ብክለት እና በሰዎች ጤናም ሆነ በአካባቢ ተፈጥሮ እንዲሁም በምድሪቱ ላይ የሚያስከትለዉ አሉታዊ ተፅዕኖዎች በመንግሥታት እና በዓለም አቀፍ የልማት አጀንዳዎች ተዘንግቶ ቆይቷል። ይህም ዛሬ ብክለት በአካባቢ ተፈጥሮ ላይ በሚከሰት ችግር ሰበብ ለሚፈጠሩ በሽታዎች እና የሰዎች ሞት ዋነኛዉ ምክንያት እንዲሆን እንዳበቃዉም ያስረዳል። ጥናቱ እንደሚለዉም በአሁኑ ወቅት በየዓመቱ ከብክለት ጋር በተያያዙ የጤና እክሎች ምክንያት ዘጠኝ ሚሊየን ሰዉ ሕይወቱን ያጣል። እንደጥናቱ በተለይም ከመጓጓዣና ኢንዱስትሪዉ አንስቶ የቤት ዉስጥ ማገዶ ሳይቀር በሚያስከትለዉ በአየር ብክለት ምክንያት የሚሞተዉ 6,5 ሚሊየን ሕዝብ ነዉ። ከሟቾቹ 92 በመቶ የሚሆነዉ የሚገኘዉ ደግሞ በድሃ እና መካከለኛ ገቢ ባላቸዉ ሃገራት ነዉ። በተለይ የልብ ችግር፣ የደም ዝዉዉር መታወክ ማለትም ስትሮክ፤ እንዲሁም የሳንባ ካንሰር በብክለቱ ምክንያት የሚመጡ የጤና ችግሮች እና የሞት መንስኤዎች መሆናቸዉን ጥናቱ ያሳያል። ከተጠቀሰዉ ቁጥር ግማሽ የሚሆነዉ ኢንዱስትሪያቸዉ በፍጥነት እያደገ በሚገኘዉ ቻይና፣ ሕንድ፣ ፓኪስታን፣ ባንግላዴሽ እና ኬንያ መሆኑም ተዘርዝሯል። ጥናቱን ያካሄዱት 40 ዓለም አቀፍ ሳይንቲስቶች ሲሆኑ ብክለት ሊያስወግዱት የሚቻል ሰዉ ሰራሽ ችግር መሆኑን በመግለጽ ለቀጣዩ ትዉልድ ጽዱ የአካባቢ ተፈጥሮን የማስረከብ ኃላፊነት የሁሉም እንደሆነ አሳስበዋል።

Kühltürme Braunkohlekraftwerk Jänschwalde
ምስል picture-alliance/R4200

አብዛኞቹ በማደግ ላይ የሚገኙ ሃገራት ራሳቸዉን ለመቻል እና ካደገዉ ዓለም ጋር ተወዳዳሪ ሆነዉ ለመገኘት በየበኩላቸዉ በተለያዩ የልማት እንቅስቃሴዎች መጠመዳቸዉ ይነገራል። ከእነሱ መካከልም ከሰሃራ በስተደቡብ ከሚገኙ ሃገራት በዚህ ረገድ ፈጣን ርምጃ ላይ መሆኗ የሚነገርላት ኢትዮጵያ ትገኛለች። አቶ አለባቸዉ አደም በኬር ኢትዮጵያ የምሥራቅ አፍሪቃ የተስማሚ ግብርና እና የአየር ንብረት ለዉጥ ከፍተኛ አማካሪ ናቸዉ። ኢትዮጵያ ከኢንዲስትሪም ሆነ ከግንባታ እና ከሌሎች የልማት ሥራዎች ጋር በተገናኘ የሚመጡ ብክለቶችን ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ግልፅ ፖሊሲዎች እንዳሏትም ይናገራሉ።

እንደሌሎች ሃገራት ሁሉ ኢትዮጵያ ዉስጥም የከተሞች አካባቢ አየር የብክለት ምንጭ ፋብሪካዎች እና ተሽከርካሪዎች መሆናቸዉን የገለጹት የአካባቢ ተፈጥሮ ጥበቃ ባለሙያዉ፤ ከመሬት አጠቃቀም እና ከከተሞች መስፋፋት ጋር በተገናኘ የሚለቀቀዉ የካርበን መጠን ከፍተኛ እንደሆነም አብራርተዋል። የብክለት መንስኤዎቹ መኖራቸዉ ታዉቆም ኢትዮጵያ ያወጣቻቸዉ እና በወረቀት ላይ ሲታዩም ተገቢነት ያላቸዉ፤ ተስማሚ የሆኑ ፖሊሲዎች እና ስልቶች መኖራቸዉንም አቶ አለባቸዉ ገልጸዋል።

በተሽከርካሪዎች ምክንያት የሚመጣዉን የአየር ብክለት ለመቀነስ የተለያዩ ሃገራት የየራሳቸዉን ቁጥጥር እና ዘዴ ሲጠቀሙ ይታያል። አብዛኞቹ የአዉቶሞቢል አምራቾችም ታዳሽ ኃይልን በመጠቀም የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ለገበያ ማቅረብ እና ማስተዋወቁን ተያይዘዉታል። ኢትዮጵያ ዉስጥ ያሉ የተሠሩበት ዘመን የከረመዉ ተሽከርካሪዎች በከባቢዉ አየር ላይ የሚያስከትሉትን ብክለት ሊቀንስ ይችላል የተባለ አንድ ቴክኒዎሎጂን ለገበያ ለማቅረብ የሙከራ እንቅስቃሴዎቹን የጀመረ አንድ ድርጅት ጥቆማዉን ለዶቼ ቬለ አድርሷል። ኢዙኩን ትሬዲንግ ይባላል፤ ዋና ሥራ አስኪያጁ አቶ አብዱልአዚዝ ከማል ለከባቢ አየር ብክለት መፍትሄ ይህ ብክለትን ይቀንሳል ስለተባለዉ ቴክኒዎሎጂ ምንነት ገልጸዉልናል። አቶ አብዱልአዚዝ በኃላፊነት የሚመሩት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያቸዉ ለከባቢ አየር ብክለት መፍትሄ ይዞ መጥቷል ብለዉም ያምናሉ።

Symbobild rauchender Auspuff
ምስል picture-alliance/blickwinkel/McPHOTOs

በአሁኑ ወቅትም የተወሰኑ ተቋማት እና ድርጅቶች ቴክኒዎሎጂዉን ተሽከርካሪዎቻቸዉ ላይ መግጠማቸዉንም አክለዉ ገልጸዋል። ሱፐር ቴክን የሚያመርተዉ የኢጣሊያዉ ኩባንያ በድረ ገጹ እንዳሰፈረዉ ቴክኒዎሎጂዉ ከነዳጅ መቆጠብ አንስቶ ወደሞተር የገባዉ ነዳጅ በአግባቡ ተቃጥሎ ኃይል የሚሆንበትን መንገድ የሚያመቻች መሆኑን ይዘረዝራል። የአየር ብክለትን ከሚያባብሱት ምክንያቶች ዋነኛዉ ሙሉ በሙሉ ሳይቃጠል ወደከባቢ አየር የሚገባዉ ከነዳጁ ዉስጥ የሚገኘዉ የካርቦን እና ናይትሮጂን ጋዝ መሆኑን የተለያዩ ጥናቶች ያመለክታሉ። በነገራችን ላይ በየዓመት በአየር ብክለት ምክንያት በሚመጡ ተያያዥ የጤና ችግሮች በመላዉ አዉሮጳ በየዓመቱ ከ500 ሺህ ሕዝብ በላይ ሕይወቱን እንደሚያጣ የአዉሮጳ ኅብረት የአካባቢ ተፈጥሮ ጥበቃ ባለስልጣን አመልክቷል። ለዚህም ግንባር ቀደም ተጠያቂዉ ከተሽከርካሪዎች የሚወጣዉ ጭስ ነዉ።

ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ