1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስ

“ኢትዮጵያ ኢንተርኔትን ለመዝጋት ሶስት መንገዶች ትጠቀማለች”

ረቡዕ፣ ግንቦት 30 2009

በኢትዮጵያ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ መደበኛ የኢንተርኔት አገልግሎት ተቋርጧል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ እስከ መጪው በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚሰጠው የዩኒቨርስቲ መሰናዶ እና መግቢያ ፈተና እንደሆነ በመንግሥት ባለስልጣናት ተገልጿል፡፡ ከኢንተርኔት ጋር ሥራቸው የተቆራኘ ግለሰቦች አገልግሎቱን በውስን መልኩ ወደሚያገኙ ተቋማት መሄድ ግድ ብሏቸዋል፡፡

https://p.dw.com/p/2eHjU
Äthiopien Addis Abeba Universität Kommunikation Internetsperre
ምስል DW/J. Jeffrey

ዳግም የተዘጋው የኢንተርኔት አገልግሎት

ኢትዮጵያ እና ኢንተርኔት እምብዛም ስማቸው በበጎ ተያይዞ ሲነሳ አይሰማም፡፡ በዓለም ዝቅተኛ የኢንተርኔት ሽፋን አላቸው ከተባሉ ሃገራት የምትመደበው ኢትዮጵያ ቀርፋፋ እና ዘገምተኛ የኢንተርኔት አቅርቦት አላት፡፡ ይህንኑ ለማግኘት የምታስከፍለው ዋጋ ከምሥራቅ አፍሪካ ሃገራት እንኳ ሲወዳደር ከሁለት እጥፍ በላይ ውድ ነው፡፡ በዚህ መልክ የምታቀርበውን የኢንተርኔት አገልግሎት መገደብ እና ማቋረጥም ሥራዬ ብላ ተያይዛዋለች፡፡

በጉዳዩ ዙሪያ ጥናት የሚያካሄደው ፍሪደም ሀውስ የተሰኘው ተቋም ባለፈው ኅዳር ወር ባወጣው ዓመታዊ ዘገባ ኢትዮጵያን የኢንተርኔት ነጻነት ከሌለባቸው ሃገራት መድቧታል፡፡ በመቶዎች የሚቆጠሩ ድረ-ገጾችም በሀገሪቱ እንዳይታዩ እቀባ እንደተጣለባቸው በዘገባው ጠቁሟል፡፡ ባለፈው ዓመት በኢትዮጵያ ተቀስቅሶ ከነበረው ሕዝባዊ ተቃውሞ ጋር በተያያዘ የኢንተርኔት አገልግሎት በተደጋጋሚ መቋረጡን በማንሳት በሀገሪቱ ያለው ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ መምጣቱን አትቷል፡፡ 

Infografik Karte Internet shutdowns 2016

ከተቃውሞው ሌላ ለኢንተርኔት መቋረጥ በምክንያትነት የተጠቀሰው ለዩኒቨርስቲ መግቢያ የሚሰጥ ፈተና በማኅበራዊ ድረ-ገጾች መሽሎክ ነው፡፡ በዚህ ዓመት ተመሳሳይ ዛቻም ሆነ አመላካች ነገሮች በማኅበራዊ ድረ ገጾች ባያስተዋሉም ብሔራዊ ፈተናዎች ከሚጀምሩበት ከግንቦት 22 ጀምሮ መደበኛ የኢንተርኔት አገልግሎት በኢትዮጵያ ተቋርጧል፡፡ መንግሥት ዘግይቶም ቢሆን የኢንተርኔት አገልግሎት “በከፊል” መቋረጡን ያመነ ሲሆን ምክንያቱ ባለፈው ዓመት የተከሰተውን አይነት የፈተና መሽሎክ ለመከላከል ነዉ የሚል ነዉ፡፡ ይህም እስከመጪው ሐሙስ ሰኔ አንድ ድረስ ሊቀጥል እንደሚችል ፍንጭ ሰጥቷል፡፡

በኢትዮጵያ ብቸኛ የቴሌኮምኒኬሽን አገልግሎቶች አቅራቢ የሆነው ኢትዮ-ቴሌኮም ኢንተርኔትን ለማቋረጥ የተለያዩ መንገዶችን እንደሚከተል የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ መቀመጫውን በአዲስ አበባ ያደረገ እና ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያ “ሦስት ዓይነት የኢንተርኔት መዝጊያ መንገዶች አሉ” ይላል፡፡ 

“የመጀመሪያው አዘጋግ ምንድነው? የተወሰኑ ፕሮቶኮሎች ወይም ምሥጢራዊ መልዕክቶችን መዝጋት እና የተለያዩ ድረ ገጾችን ለምሳሌ እነ ፌስቡክን፣ እነ ቫይበርን እነርሱን አድራሻዎች ነጥሎ መዝጋት ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ የተወሰኑ ድረ ገጾችን ነጥሎ ከፍቶ ሌላውን ሙሉ ለሙሉ መዝጋት ነው፡፡ የሆኑት ብቻ ተደራሽ እንዲሆኑ አድርጎ ሌላውን በሙሉ ማጥፋት ነው፡፡ ሶስተኛው አዘጋግ ደግሞ ሙሉ ለሙሉ አዘጋግ ነው፡፡ ይህ ማለት ምንም ዓይነት ግንኙነት፣ አገልግሎት፣ ኔትወርክ የለም ማለት ነው፡፡ በመጀመሪያው ሁለት መንገድ ከተዘጋ የተለያዩ መንገዶችን ተጠቅመህ የምትፈልጋቸውን ነገሮች ማግኘት ትችላለህ፡፡ በሶስተኛው ዓይነት መንገድ ከተዘጋ፣ ምንም መስመር ከሌለ ግን ያው ምንም ማድረግ አይቻልም፡፡ ሁላችንም ተዘግቶብን ቁጭ ማለት ነው ያለን ዕድል” ሲል ስለ ሶስቱ መንገዶች ያብራራል፡፡

Äthiopien Addis Abeba Universität Kommunikation Internetsperre
ምስል DW/J. Jeffrey

በኢትዮጵያ የኢንተርኔት መቋረጥ ሲከሰት አገልግሎት ሰጪው ድርጅት መጀመሪያ ይጠቀምበት የነበረው መንገድ እንደ ፌስ ቡክ አይነት ማኅበራዊ ድረ-ገጾችን እና ምሥጢራዊ የመልዕክት መለዋወጫ ዘዴዎች የሆኑትን እንደ ዋትስ አፕ አይነቶችን መገናኛዎች በመዝጋት እንደነበር ባለሙያው ያስታውሳል፡፡ በስተኋላ ግን ህዝባዊ ተቃውሞ በተባባሰበት ጊዜ ሙሉ ለሙሉ የመዝጋት መንገድ መከተሉን ይናገራል፡፡ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ መላ ሀገሪቱን ያዳረሰው የመደበኛ ኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጥስ በየትኛው መንገድ የተተገበረ ይሆን? የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያ ምላሽ አለው፡፡

“አሁን የተዘጋው አዘጋግ ለተወሰኑ ድርጅቶች እና ተቋማት ብቻ ኢንተርኔት ተለቅቆ  ሌላው ገመድ አልባ ግንኙነት ሙሉ በሙሉ ነው የተዘጋው፡፡ 2ጂ፣ 3ጂ፣ 4ጂ በሙሉ ነው የተዘጋው፡፡ አሁን ሀገር ውስጥ ምንም ዓይነት ገመድ አልባ ግንኙነት የለም፡፡ ስለዚህ የኢንተርኔት አገልግሎት ማግኘት የሚችሉበት ብቸኛ መንገድ ፋይበር ኦፕቲክስ ወይም ኤዲኤስኤል ያላቸው ሰዎች ጋር በመሄድ ወይም ደግሞ እንደዚህ አይነት አክሰስ ያላቸው ሰዎች ናቸው መጠቀም የሚችሉት” ይላል፡፡

እንደባለሙያው እማኝነት የመንግሥት ተቋማት፣ የእርዳታ ድርጅቶች፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተለያዩ ተቋማት እና የአፍሪካ ኅብረት የኢንተርኔት አገልግሎት አሁንም ያገኛሉ፡፡ በፋይበር ኦፕቲክስ መስመር እና በኤ.ዲ.ኤስ.ኤል ብሮድባንድ የኢንተርኔት አገልግሎት ሲያገኙ የቆዩ ድርጅቶች እና ግለሰቦችም ከጥቂት ዕድለኞች መካከል ናቸው፡፡ ሌላው ኢንተርኔት ፈላጊ እነዚህን ድርጅቶች እና ባለኮኮብ ሆቴሎች ደጅ ጠኚ ሆኗል፡፡ አብዛኛው ሥራቸው ከኢንተርኔት ጋር የተያያዘ የኢንፎርሜሽን እና ቴክኖሎጂ ባለሙያዎችም ቢሆኑ በዚህ መልኩ ሥራቸውን ለመስራት ይፍጨረጨራሉ፡፡ በእነዚህ ድርጅቶች እና ተቋማት ስላለው የኢንተርኔት ጥራት “እርሱም ቢሆን ውስን የሆነ ኮኔክሽን ነው፡፡ አንዳንድ ድረ ገጾች ለምሳሌ ጉግል፣ ጂሚይል ኤሜይል ለመመልከት እነርሱ ናቸው የተከፈቱት፡፡ ዩ-ቲዩብ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ይሰራ ነበር ዛሬ [ማክሰኞ] ተቋርጧል፡፡ ስለዚህ እነዚህ ድረ-ገጾች አክሰስ የሚደረጉት በvirtual private network ወይም VPN ነው” ሲል የታዘበውን ያጋራል፡፡

Symbolbild Facebook USA Börsengang Logo Startseite
ምስል Reuters

ከዓመታት በፊት በጥቂት ባለሙያዎች ዘንድ ብቻ ይታወቅ የነበረው VPN አሁን የበርካታ የሞባይልም ሆነ የኮምፒውተር ኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ቋንቋ ሆኗል፡፡ የ VPN አፕልኬሽኖችን ለማስጫን ወደ ሞባይል መሸጪያ እና መጠገኚያ ቤቶች ጎራ የሚሉ ተጠቃሚዎችም እየጨመሩ ነው፡፡  ለመሆኑ VPN ምንድነው? እንዴትስ ይሰራል? ባለሙያው ለዚህ ጥያቄ ምላሽ ከመስጠቱ በፊት ተያያዥ ከሆነው እና በእንግሊዘኛ ምህጻሩ DNS በመባል ስለሚታወቀው ምንነት ሙያዊ ፍቺ ይሰጣል፡፡  

“መጀመሪያ DNS - Domain Name Server ይባላል፡፡ ይሄ የሚሰራው ምንድነው? ለምሳሌ አንድ ሰው ጉግልን ማየት ከፈለገ ጉግል ብሎ መፈለጊያ ላይ ይጽፋል፡፡ ያንን ጉግል የሚለውን ስም ወደ አድራሻ ተቀይሮ ያን ገጽ የተቀመጠበትን ሰርቨር ፈልጎ አግኝቶ፣ ከዚያ ገጽ ላይ አምጥቶ ነው ስክሪን ላይ የሚያስቀምጥልህ፡፡ እያንዳንዱ የቴሌኮሙዩኒኬሽን [አገልግሎት ሰጪ] አድራሻን ወደ IP address የሚቀይር የራሱ የሆነ ሰርቨር አለው፡፡ ያንን የሚሰራው ሰርቨር ነው DNS የሚባለው፡፡ ማንኛውንም ድረ-ገጽ ጉግልም ይሁን ዩ-ቲዩብ ለመጠቀም መጀመሪያ ወደ DNS ሰርቨሩ የመግቢያ ፍቃድ እንልካለን፡፡ የቴሌኮሙዩኒኬሽንም ይሁን የምንጠቀምበት አገልግሎት ያንን ድረ-ገጽ ካለበት ፈልጎ ለእኛ ይልክልናል ማለት ነው፡፡ virtual private network ስትጠቀም ያንን የመመልከቻ ፍቃድ እና የምትልከውን መረጃ በሙሉ ተቆልፎ ነው ለአንድ ሰርቨር የሚላከው፡፡ ያ ሰርቨር ያንን የፍቃድ ጥያቄውንም ሆነ ፋይል ከፍቶ ፌስቡክን ማየት ከፈለግህ ወደ ፌስቡክ፣ ጎግልም ከሆነ ወደ ጉግል ይመራል፡፡ ስለዚህ  እዚህ ጋር ምስጢሩ ምንድነው? የምትልከው ማንኛውም ነገር ፋይልም ሆነ መረጃ ምን እንደሆነ ሳይታወቅ ተሸፍኖ በቀጥታ VPN ወዳለበት ሰርቨር ነው የሚሄደው፡፡ ያ ላንተ ያለው ጠቀሜታ ምንድነው?  የቴሌ ሰርቨር ጉግልን ተመልከት ወይም ፌስቡክን፤ የሚያውቀው ነገር የለም፡፡ የሚያውቀው ያንን ሰርቨር እንደተመለከተህ ብቻ ነው፡፡ ምን መመልከት ፈልገህ ፍቃድ እንደጠየቅህ፣ ምን ዓይነት መረጃ  እንደተቀበልክ አያውቅም፡፡ ለዚያ ነው VPN ሲሆን ሁሉንም ድረ ገጾች መመልከት የምትችለው፡፡ ምክንያቱንም ቴሌን ቀጥታ ፌስቡክን አገናኘኝ ብትለው ጥያቄህን ውድቅ ያደርግብሃል ምክንያቱም ድረ-ገጹ ስለተዘጋ ማለት ነው” ሲል ያብራራል፡፡

Indien Pornografie im Internet (Symbolbild)
ምስል M. Kiran/AFP/Getty Images

በኢትዮጵያ ገመድ አልባ የኢንተርኔት ግንኙነት ባለመኖሩ VPN ተጠቅመው የተዘጉ ድረ-ገጾችን መመልከት የሚችሉት የብሮድባንድ ኢንተርኔት አገልግሎትን እያገኙ ያሉ ብቻ መሆናቸውን ባለሙያው ይገልጻል፡፡ ሰፊ ቦታን ያካለለው የአሁኑ የመንግስት የኢንተርኔት መዝጋት እርምጃ የመጣው ተጠቃሚዎች በከፊል የሚደረግን የኢንተርኔት ክልከላ እንደ VPN ባሉ ዘዴዎች በማለፋቸው እንደሆነ ያስረዳል፡፡ “ቁጥጥሩ አንድ እርምጃ በተራመደ ቁጥር ሰውም አንድ እርምጃ ወደፊት ይራመዳል፡፡ ሙሉ ለመሉ መዝጋት ደረጃ ላይ የደረስነው ለዚያ ይመስለኛል” ይላል፡፡ ኢትዮጵያ ኮሽ ባለ ቁጥር የኢንተርኔት ግንኙነት ማቋረጥ ቀጥላለች፡፡ ጉዳዩን አስመልክቶ በቁም ነገርም ሆነ በዋዛ ምክር ያቀበሏት “የዝሆን ጆሮ ይስጠኝ” ብላለች ሲሉ ይተቿት ይዘዋል፡፡ 


ተስፋለም ወልደየስ

ሸዋዬ ለገሠ