1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመን እና የናሚቢያ ድርድር፤

ሐሙስ፣ ሐምሌ 7 2008

የጀርመን መንግሥት በይፋ የቀድሞ ቅኝ ግዛት የነበረችዉ ናሚቢያን ይቅርታ ሊጠይቅ መዘጋጀቱን አስታዉቋል። በደቡብ ምዕራብ አፍሪቃ የምትገኘዉ ናሚቢያ የጀርመን ቅኝ ተገዢ በነበረችበት ወቅት ከምዕተ ዓመት በፊት የተጀመረዉን የአመፅ እንቅስቃሴ ለመግታት የዘር ፍጅት መፈፀሙን ጀርመን አምናለች።

https://p.dw.com/p/1JP0X
Herero
ምስል picture alliance/akg-images

[No title]

ጀርመን የደቡብ ምዕራብ አፍሪቃ አካባቢን ከጎርጎሪዮሳዊዉ 1884 እስከ 1915ዓ,ም ደረስ በቅኝ ገዥነት ይዛ ቆይታለች። በወቅቱ ናሚቢያ ዉስጥ ጀርመናዉያን ሰፋሪዎች በመበራከታቸዉ እና መሬታቸዉን፣ ከብቶችና ሴቶቻቸዉን በመዉሰዳቸዉ የሄሬሮ ጎሳ አባላት በዚሁ የዘመን ቀመር በ1904ዓ,ም ቅኝ ገዢዎቻቸዉ ላይ በአመፅ ተነሱ። ለረዥም ቀናት በዘለቀዉ አመፅም 123 ጀርመናዉያንን ገደሉ። የናማ ጎሳም በቀጣዩ ዓመት ማለትም በ1905ዓ,ም ተመሳሳይ አመፅ አነሳ። የቅኝ ገዢዎቹ ምላሽ የከፋ ነበር። ጀነራል ሎታር ፎን ትሮታ ሄሬሮዎች እንዲፈጁ ፈርሞ ትዕዛዝ አስተላለፈ። በየእስር ቤቶች የታጎሩ የናማ እና ሄሬሮ ጎሳ አባላት በምግብ እጥረት እና በከፋዉ የአየር ጠባይ ምክንያት ለሞት ተዳረጉ። በርካቶችም ከሞቱ በኋላ አንገታቸዉ እየተቀላ ለሳይንሳዊ ምርምር እና ሙከራ ወደበርሊን ተላከ። ናሚቢያ ዉስጥ አመፁ ሲቀጣጠል 80ሺህ የነበሩት የሄሬሮ ጎሳ አባላት ከዘር ፍጅቱ በኋላ 15 ሺህ ብቻ መቅረታቸዉን ዘገባዎች ያስረዳሉ። ጀርመን ካለፈዉ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 2011 ጀምሮ ለምርምር የመጡትን የራስ ቅሎች ወደናሚቢያ መመለስ ጀምራለች። ሆኖም ግን ለድርጊቱ ካሣ ለመክፈል በርሊን ፈቃደኛ አልሆነችም። በምክንያትነት የምታቀርበዉም ናሚቢያ ከደቡብ አፍሪቃ ተገንጥላ ራሷን የቻለች ሀገር ከሆነችበት ከዛሬ 27ዓመት አንስቶ ለልማቷ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዩሮ መስጠቷን ነዉ። የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ሳዋሳን ቼፕሊ በቀጣይ ካሣ ስለመክፈል ስለሚኖረዉ ዉሳኔ ሲናገሩ፤

«ይህን ማለታችን ምን ዓይነት ካሣ አያስከፍልም ሕጋዊ መዘዝም አይኖረዉም። ታሪኩን እንዴት መያዝ ይኖርብናል ወይም መሰየም ይጠበቅብናል ለሚለዉም እስካሁን ብዙ ጊዜ ተናግረነዋል። አሁንም የተቀየረ መሠረታዊ ነገር የለም።»

የጀርመን ምክር ቤት ቱርክ አርመን ዉስጥ ፈፅማዋለች ያለዉን የዘር ጭፍጨፋ ለመወሰን ብዙም አልተቸገረም። የኦቶማኑን ሥርወ መንግሥት ያወገዘዉ እና ይህን ያሳለፈዉ በብዙሃኑ ድምጽ ነበር። የጀርመን ዉሳኔ ያበሳጫቸዉ የቱርክ ፕሬዝደንት ራሲፕ ጠይብ ኤርዶኻን፤ ከመቶ ሺህ በላይ ሄሬሮዎች ያለቁበትን ርምጃ አስቀድማ በርሊን ፈር እንድታስይዝ በወቅቱ ጠይቀዋል። በዚህ ጉዳይ ላይ ከጀርመን የተሰማ ተመሳሳይ ነገር ባለመኖሩም የጀርመን ምክር ቤት ማለትም ቡንደስታኽ ፕሬዝደንት ኖበርት ላመርት «ትንሽ ያሳፍራል» ብለዋል። ጉዳዩ ሲያነታርክ ቆይቷል። የዘር ማጥፋት የሚለዉ አገላለፅ በራሱ በተመድ ድንጋጌ ዉስጥ የገባዉ በጎርጎሪዮሳዊዉ 1951ዓ,ም ነዉ የሚለዉ የመንግሥት መከራከሪያም አሁን ተነስቷል። ከ12 ዓመታት በፊት የጀርመን የልማት ሚኒስትር የነበሩት ሃይደማሪ ቪቾሪክ ሶይል ያለቁት የሄሬሮ እና ናማ ጎሳዎች በታሰቡበት ስነሥርዓት ላይ ተገኝተዉ ድርጊቱ «የዘር ማጥፋት» በተለሳለሰ ቃል በመግለፅ በፌደራል መንግሥቱ ስም ይቅርታ ጠይቀዋል። ይህም ከፍተኛ ትችት አስከትሎባቸዋል። በወቅቱ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩትዮሽካ ፊሸር የወይዘሮዋ ይቅርታ የካሣ ክፈሉን ጥያቄ ሊያስከትል ይችላል የሚል ስጋታቸዉንም አሰምተዋል። ዉሎ አድሮ ግን ሁኔታዉ ተቀይሯል። ከአራት ዓመታት በፊት የአሁኑ የጀርመን የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር በዚሁ ኃላፊነት ላይ በነበሩበት ወቅት «ከ1904 እስከ 1908 ናሚቢያ ዉስጥ የተካሄደዉ ጦርነት የጦር ወንጀል እና የዘር ጭፍጨፋ ነዉ» ሲሉ አረጋግጠዋል። ይህም የጀርመን መንግሥት ፖሊሲ ነዉ፤ እና ከናሚቢያ ጋርም ለእርቅ እና ለካሣ ዉይይት ዝግጁነቱን አሳይቷል። በቅርቡም የጀርመን ልዩ ልዑክ ሩፕረሽት ፖለንዝ እና በዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪቃ ጉዳይ ተጠፊ ጊዮርግ ሽሚት ዊንድሆክ ዉስጥ ከናሚቢያ ባለስልጣናት ጋር ተነጋግረዋል። በእኩልነት የሚካሄደዉ ንግግራቸዉም ባለፈዉ ጉዳይ ላይ ሳይሆን የወደፊቱ ላይ ያነጣጠረ ነዉ። የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይዋ በሁለቱ ሃገራት መካከል ድርድሩ ከተጀመረ ቆየ ይላሉ።

«ስለየዘር ማጥፋት በይፋ ከተናገርን መቆየታችን ይታወቃል። ከ2014 ጀምሮን የፌደራል መንግሥት ከናሚቢያ ጋር ይህን የቅኝ ግዛት ዘመን አሳዛኝ ታሪክ በተመለከተ እየተነጋገረ ይገኛል። ከ2015 ጀምሮም ሁለቱም ወገኖች የናሚቢያ ልዩ ልዑካንንም ሰይመዋል።»

ይህንን ናሚቢያዉያኑም ይጋሩታል። ድርድሩ በያዝነዉ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት ማለቅ ይኖርበታል። ቢራዘም እንኳ ቀጣዩ የጀርመን ምርጫ በመጪዉ ዓመት ከነሐሴ እስከ ጥቅምት ወር ማለት ነዉ ከመካሄዱ አስቀድሞ እንደሚያልቅ ይገመታል።

ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ