1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ፀረ ዚምባብዌ መንግሥት ተቃውሞ

ቅዳሜ፣ መጋቢት 16 2009

ዚምባብዌን እጎአ ከ1980 ጀምሮ በመምራት ላይ ያሉት የ93 ዓመቱ ፕሬዚደንት ሮበርት ሙጋቤ አንጻር ተቃውሞ እየጠናከረ መጥቷል። ለብዙ ዓመታት በዋነንነት ሲደግፉዋቸው የነበሩት አርበኞች እንኳን በወቅቱ ይህንኑ ድጋፋቸውን ነፍገዋቸዋል።

https://p.dw.com/p/2ZvOx
Simbabwe
ምስል DW/C. Mavhunga

zimbabwe 25032017 - MP3-Stereo


እነዚሁ አርበኞች በሚቀጥለው ዓመት በሀገሪቱ በሚካሄደው ምርጫ በፕሬዚደንት ሙጋቤ አንጻር የሚፎካከሩ  እጩዎችን፣ የተቃዋሚ ፓርቲ ተወዳዳሪዎችን ሳይቀር ለመደገፍ መወሰናቸውን ከጥቂት ቀናት በፊት በመዲናይቱ ሀራሬ በተካሄደ አንድ ስብሰባ ላይ  አስታውቀዋል። እስከጥቂት ጊዜ በፊት ድረስ የፕሬዚደንት ሙጋቤ ደጋፊ የነበሩት እጎአ በ1970 ዓም የነፃነት ጦርነት ላይ የተዋጉ የዚምባብዌ አርበኞች ማህበር ሊቀ መንበር ክሪስ ሙትስቫንግዋ ዴሞክራሲያዊ መመሪያዎችን አይከተልም በሚል ገዢው የዛኑ ፒ ኤፍ ፓርቲ በመውቀስ፣ አሁን ዛኑ ፒ ኤፍ እንደ ጠላት ከሚመለከታቸው ፖለቲከኞች ጋር፣ ብቁ እስከሆኑ ድረስ፣ አብረው እንደሚሰሩ ነው ያስታወቁት። 
የተቃዋሚ ፖለቲከኞች ፣ የመብት ተሟጋቾች እና የቤተ ክርስትያን መሪዎች የዚምባብቄ አስመራጭ ኮሚሽን  የሚቀጥለውን ዓመት ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ለማጭበርበር ከሀገሪቱ መንግሥት ጋር ተባብሯል በሚል ተቃውሞ በዚህ ሳምንት አጋማሽ በሀራሬ አደባብባይ ወጥተው ነበር። 
የሀራሬ ፖሊስ ተቃዋሚዎች ቅሬታቸውን ለማሰማት ወደ አስመራጩ ኮሚሽን እንዳይሄዱ ቀደም ሲል ያሳረፈውን እገዳ ካነሳ በኋላ ነበር አደባባይ መውጣት የቻሉት። 
13 የፖለቲካ ፓርቲዎች የተጠቃለሉበት «ብሔራዊ የምርጫ ሕግ ማሻሻያ አጀንዳ» በሚል መጠሪያ የተቋቋመው ቡድን  አስመራጩ ኮሚሽን  ባዮሜትሪክ የመራጮች መመዝገቢያ ማሽንን ለመግዛት በያዘው እቅዱ ከገዢው ፓርቲ ጋር ተመሳጥሮ እየሰራ ነው በሚል ብርቱ ወቀሳ ሰንዝሯል።   ይህ የአስመራጭ ኮሚሽን ውሳኔ ዛኑ ፒ ኤፍ የመራጮችን ዝርዝር ለራሱ እንደሚመች አድርጎ መለዋወጥ ያስችለዋል የሚል ስጋት መኖሩን  የዋነኛው እና የትልቁ ተቃዋሚ ፣ የዴሞክራሲያዊ ለውጥ ንቅናቄ» ፓርቲ ፣ በምህፃሩ የ«ኤም ዲ ሲ»  ዋና ጸሐፊ ዳግላስ ሞንዙራ የተቃዋሚዎቹን አቤቱታ ለአስመራጩ ኮሚሽን ፣ በምህፃሩ ለ«ዜክ» ካቀረቡ በኋላ ለጋዜጠኞች ገልጸዋል። 
« የመራጮች መመዝገቢያ ማሽን ግዢ ጉዳይ የሚመለከተው አስመራጩን ኮሚሽን «ዜክ»ን ብቻ ነው። እና ይህንን ኃላፊነቱን ለመንግሥት አሳልፎ መስጠት የገለልተኛነቱን ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ ያስገባዋል።  የዚምባብዌ ሕዝብ በሕገ መንግሥቱ እንዳስቀመጠው «ዜክ» ገለልተኛ መሆን አለበት። ግን ሆኖ አያውቅም።»
ሞንዙራ የምርጫው ሕግ እንዲሻሻል፣  ኮሚሽን  የመራጩ የመምረጥ መብት እና የምርጫውም ውጤት እንዲከብር ፣ባጠቃላይ ገለልተኛ የሆነ  አስመራጩ ኮሚሽን ለሀገሪቱ እንደሚያስፈልግ ነው  እንዳለበት በአጽንዖት አስታውቀዋል። ቡድኑ «አስመራጩ ኮሚሽን እንዲበተን እና በሌላ ገለልተኛ አካል እንዲተካ ጠይቋል።
«አስመራጩ ኮሚሽን « ዜክ» እንዲበተን እንፈልጋለን፣ በአንድ በደቡባዊ አፍሪቃ የልማት ድርጅት፣ በምህፃሩ በ«ሳዴክ» ወይም በአፍሪቃ ህብረት ወይም በተመድ በሚመራ አንድ የምርጫ አስፈጻሚ ቡድን መተካት ይኖርበታል። »
 የአስመራጩ ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሪታ ማካራው ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ከተገናኙ በኋላ በሰጡት መግለጫ፣ ኮሚሽኑ ከገዢው ፓርቲ ጋር ተባብሮ ስለሚሰራ ገለልተኛ አይደለም በሚል የቀረበውን ወቀሳ ሀሰት ሲሉ በማስተባበል፣ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ወቀሳ ገሀዱን የማያንጸባርቅ ነው  በሚል አጣጥለውታል። 
የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር እና የ«ኤም ዲ ሲ» ሊቀ መንበር ሞርገን ቻንጊራይ ቀጣዩ የዚምባብዌ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ እንደበፊቶቹ ሊጭበረበር እንደማይገባ ቀደም ሲል ተናግረዋል።  እንግዲህ ተቃዋሚዎች ያላቸው ምርጫ የአስመራጩን ኮሚሽን ምላሽን መጠበቅ ሆኗል። ይህ ሁሉ የሚጠቁመው ጊዜ ግልጽ የሆነ ጉዳይ ቢኖር የ2018 ዓም ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ም እንደ ካሁን ቀደሞቹ አወዛጋቢ መሆኑ እንደማይቀር ነው።  
ከ1980 ዓም ወዲህ በስልጣን ላይ የሚገኙት ፕሬዚደንት ሙጋቤ ቀደም ባሉ ምርጫዎችም ወቅት ግዙፍ የማጭበርበር ተግባር ፈጽመዋል በሚል ብዙ ጊዜ ወቀሳ ቀርቦባቸዋል። ወቀሳዎቹን ተከትሎ የአውሮጳ ህብረት ምርጫ ማጭበርበር እጎአ በ2002 ዓም  በፕሬዚደንት ሙጋቤ ላይ የጉዞ እና ንብረታቸው እንዳይንቀሳቀስ እገዳ ማሳረፉ ይታወሳል።   

Simbabwe
ምስል DW/C. Mavhunga
Simbabwe
ምስል DW/C. Mavhunga

አርያም ተክሌ

ማንተጋፍቶት ስለሺ